በትግራይ 33 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት በሞት አደጋ ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታወቀ።
በትግራይ ክልል ጦርነት ከተከሰተበት ከጥቅምት 24 ጀምሮ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውና ክልሉም በከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ መሆኑን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ መሠረትም ከ350 ሺህ በላይ የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ በሚባል ችግር ውስጥ ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ረሃብ አለ እየተባለ የሚወጣውን መረጃ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ከማስተባበሉም ባሻገር በክልሉ እርዳታ በበቂ እየተከፋፈለ ነው ብሏል። ሐሙስ ዕለት የወጣውና የክልሉን ሁኔታ የገመገመው ሪፖርት በክልሉ ያለው የምግብ ሁኔታን “ካታስሮፊ” በሚል ጉዳትን እንደሚያስከትል ፈርጆታል።
በዚህም ትርጉም መሰረት በአሁኑ ወቅት ቸነፈር (ረሃብ) እና ሞት እየተከሰተ ያለ ሲሆን ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ሊዛመት እንደሚችል ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስቀረት ዩኒሴፍ እርዳታ የሌላቸው አካባቢዎች የእርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች ጥሪ አቅርቧል።
“በአሁኑ ወቅት የዳሰሳ ጥናት ከተደረገባቸው 20 በመቶው ሕዝብ መካከል 350 ሺህ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ላይ መሆናቸውን ማሳየቱ ይፋዊ በሆነ መልኩ ረሃብ (ፋሚን) አለ ብሎ ለማወጅ ከተቀመጠው በታች ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሰዎች እየሞቱ በቃላት ባንጫወት ጥሩ ነው” በማለት የዩኒሴፍ ቃለ አቀባይ ጄምስ ኤልደር አርብ ዕለት ተናግረዋል። 33 ሺህ የሚሆኑ ህፃናትና ጨቅላዎች በከፍተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት በህመም አፋፍ ላይ ናቸው። በሞት አደጋም ላይ ናቸው በማለት ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ በባለፉት ሁለት ወራት ከ75 ሺህ የሚበልጡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ህፃናት ወደ ጤና ማዕከላትና ተንቀሳቃሽ የህክምና መስጫ ማዕከላት መምጣታቸውን ገልጸው ነበር። ከእነዚህም መካከል 4 በመቶዎቹ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን አስፈላጊው የህክምና እንክብካቤና አገልግሎት አግኝተዋል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን የሚሆነው የክልሉ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ የቀውስ ቋፍ ላይ የሚገኝ ነው በሚባል ደረጃ ተቀምጧል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በትግራይ ረሃብ ተከስቷል በማለት ቢናገሩም ኢትዮጵያ ይህንን አትቀበለውም። በክልሉ ያለውን ሁኔታ እንደገና ወደነበረበት ለመመለስ እየሰራ እንደሆነና የሰብዓዊ እርዳታም እየደረሰ እንደሆነ መንግሥት ተናግሯል።
አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በጥምረት በትግራይ ጦርነት የተሳተፉ አካላት በሙሉ ተኩስ እንዲያቆሙና በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ ሚሊዮኖች እርዳታ የሚደርስበት ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጥሪ አቅርበዋል። በክልሉ ክፉኛ የሚባል ረሃብ ከመፈጠሩ በፊት ይህ ሊፈፀም እንደሚገባ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ