የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እና ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በሁለት ዙር እንዲከናወን መወሰኑን ተከትሎ፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ይከናወናል ተብሎ የነበረው የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች የራሳቸውን ክልል ለመመሥረት የሚያደርጉት ሕዝበ ውሳኔ፣ ከሁለተኛ ዙር ምርጫ ጋር እንዲከናወን መወሰኑ በደቡብ ምዕራብ ዞኖች ቅሬታ ፈጠረ፡፡

ቦርዱ ካሁን ቀደም በፀጥታና በፍርድ ቤት ክርክር፣ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሳቢያ ምርጫው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የማይካሄድባቸው ቦታዎች እንደሚኖሩ ያስታወቀ ሲሆን፣ በሁለት ዙር ለሚከናወነው ምርጫ ሁለተኛ የድምፅ መስጫ ቀን ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲሆን መወሰኑ የተገለጸው፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በዲ ሊዮፖል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነበር፡፡

ሰብሳቢዋ በመግለጫቸው ካሁን ቀደም ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ኅትመት ላይ ስህተት በመፈጠሩና ዳግም ኅትመት በማስፈለጉ፣ የድምፅ መስጫ ቀናቸው እንዲራዘም የተደረጉ የክልል ምክር ቤቶችና የፓርላማ የምርጫ ክልሎች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር ጎን ለጎን የፀጥታ ችግር የታየባቸው ሕዝበ ውሳኔ ይደረግባቸው የነበሩ የደቡብ ምዕራብ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ዲዚ፣ ዘልማም፣ ማጀት መደበኛና ቀይ አፈር መደበኛ የተባሉ የምርጫ ክልሎች፣ በሕዝበ ውሳኔው መሳተፍ ስለሚኖርባቸውና ድምፃቸውም ወሳኝ በመሆኑ ሳቢያ፣ የሕዝበ ውሳኔው ድምፅ መስጫ ቀን ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል፡፡

‹‹ቀደም ሲልም ዲዚ፣ ዘልማም፣ ማጀት መደበኛና ቀይ አፈር መደበኛ የሚባሉ ቦታዎች፣ በአንድም በሌላም መልኩ ከድምፅ ሰጪዎቹ ወይም በውሳኔው ላይ ከሚወስኑት መራጮች ጋር የተያያዙ ስለሆኑ፣ እነዚያ ደግሞ በፀጥታ ምክንያት የቆዩ የምርጫ ክልሎች ስላላቸው፣ የእነሱም ድምፅ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ፣ እንደማናደርግና መደረግም እንደሌለበት መጀመርያ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ቦርዱ አምኗል፡፡ ነገር ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገር ስለነበረበት ውሳኔውን ለጊዜው ይዞት ነበር፡፡ ለዚህ ተብሎ በክልሉ የተቋቋመ የፕሮጀክት ማስተባበሪያ አለ፣ በዚያ አካባቢ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች አሉ፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሦስቴ አነጋግረናቸዋል፡፡ እነሱም ተመሳሳይ ሐሳብ ስላላቸው በዚያው [ቦርዱ] ተበረታቷል፡፡ ዕቅዳችንን የመጨረሻ አድርገን አፅድቀናል ማለት ነው፤›› ሲሉ ወ/ሪት ብርቱካን አብራርተዋል፡፡

ይሁንና የደቡብ ምዕራብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምትኩ በድሩ (ኢንጂነር)፣ ‹‹ይኼ የቦርዱ ውሳኔ ዱብ ዕዳ ነው የሆነብን›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው ካሁን ቀደም ከቦርዱ ጋር የተወሰኑ የፀጥታ ችግር አለባቸው በሚል ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅተች ቅሬታ የቀረበባቸውን ‹‹ሦስትና አራት የምርጫ ክልሎች›› በተመለከተ ውይይት ተደርጎ እንደነበር፣ ነገር ግን እነዚህም ቦታዎች ቢሆኑ ሕዝበ ውሳኔውን ይፈልጋሉ ከሚል መግባባት ተደርሶ በትብብር ለመሥራት ወስነው መለያየታቸውንም አክለዋል፡፡

‹‹አብረን ለመሥራት ነው ተነጋግረው የወሰኑት፣ ያንን ይመስለኛል፡፡ ባለፈው ረቡዕም ከምርጫ ቦርድ የፕሮጀክት ሥራ አስፈጻሚ ጋር ተነጋግረው ነበር፡፡ በዚያ ጉዳይ የተደረሰበትን ይመስለኛል እንጂ፣ ስለመራዘሙ ምንም ዕውቀት የለኝም ዕውነት ለመናገር፤›› ብለዋል፡፡ ሕዝበ ውሳኔው ለምን እንደተራዘመ ለማወቅና ከቦርዱ ጋር ለመነጋገር አዲስ አበባ እንደሚገኙ የጠቀሱት ምትኩ (ኢንጂነር)፣ የዞኖች አመራሮችም ሆኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ስለውሳኔው ያወቁ አይመስለኝም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ችግር አለባቸው የተባሉ የምርጫ ክልሎች ከአንዱ በስተቀር ሰላም መሆናቸውን፣ የዞኖቹ አመራሮችና የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ጉብኝት አድርገው ይኼንን እንዳረጋገጡም ጠቁመዋል፡፡ ለሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት ሲደረግባቸው የነበሩ ዞኖች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ግን ጥሩ ስሜት ውስጥ እንዳልሆኑና ለአገራዊው ምርጫም አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

‹‹ለረዥም ጊዜ የተጠየቀን ነገር ሰው በሌላ መንገድ ሊያየው ይችላል፡፡ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ አስገብተን ለመነጋገር ነው የመጣነው፤›› በማለትም አስታውቀዋል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በምርጫው በኃላፊነትና በአስፈጻሚነት ሲሠለጥኑና ሲያሠለጥኑ የቆዩ የምርጫ ሠራተኞች፣ ካሁን ቀደም በምርጫ ሒደት ሥልጠናና ቁሳቁስ ትውውቅ ወቅት ሕዝበ ውሳኔውን የተመለከተ ምንም ዓይነት ሥልጠና ባለማየታቸው ግር መሰኘታቸውንና ይኼንንም ቦርዱን ጠይቀው ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ የተለያዩ የደቡብ ምዕራብ ዞኖችና የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ የዳውሮ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር በተመሳሳይ ዕለት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ይደረግ የነበረውን የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል አደረጃጀት ሕዝበ ውሳኔ ቀን፣ ያለ በቂ ምክንያት ምርጫ ቦርዱ አራዝማለሁ ማለቱ ተቀባይነት የለውም፤›› ብሏል፡፡

የዞኑ መንግሥት በበኩሉ፣ ‹‹ስድስተኛ ዙር አገራዊ ምርጫና የደቡብ ምዕራብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ በሚመለከት የዞናችን ሕዝብና መንግሥት እስካሁን ድረስ ምርጫ ቦርዱ ባስቀመጠው ዲሲፕሊን መነሻ፣ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሒደት የምርጫ ምዝገባ በማጠናቀቅ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ካርድ ለመጣል እየተጠባበቀ ይገኛል፤›› በማለት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሰጠው መግለጫ የዞናችንን ነባራዊ ሁኔታ ፈጽሞ ያላገናዘበና ለአገረ መንግሥት ግንባታ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት በሞራልም ሆነ በሥነ ልቦና የተዘጋጁትን ሕዝቦቻችንን ቅሬታ ውስጥ ያስገባቸው ሆኖ አግኝተነዋል፤›› በማለት፣ ምርጫው አስቀድሞ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲካሄድ አሳስቧል፡፡

የቤንች ሸኮና የካፋ ዞኖችም በተመሳሳይ ውሳኔውን በመኮነን መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ ሁለቱም ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን መለስ ብሎ እንዲያጤንና በመጀመርያው ዕቅድ መሠረት እንዲያከናውን ጠይቀዋል፡፡ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተለያዩ ዘርፎች ፀጥታና መሰል ችግሮችን እያስተናገደ ከግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ሰኔ 14፣ ከዚያም ገሚሱ ወደ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የተራዘመ ሲሆን፣ አሁንም አዳዲስ ችግሮችን እያስተናገደ ነው፡፡

ከዚህም አንዱ ያለ ቦርዱ ዕውቅና የተከፈቱ 79 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው ሲሆን፣ ቦርዱ ዓርብ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቦርዱ ዕውቀውና ውጪ የተከፈቱ ሁለት፣ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ የተከፈቱ ስድስት፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ የተከፈቱ 71 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተደረጉ የመራጮች ምዝገባዎች ሕጋዊ አይደሉም ሲል ቦርዱ ወስኗል፤›› ብሏል፡፡

በቦርዱ የመራጮች ምዝገባ መሥፈርት መሠረት በአንድ የምርጫ ጣቢያ 1,500 መራጮች መመዝገብ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ሙሉ ምዝገባ አከናውነው ከሆነ 118,500 መራጮች ምዝገባ ከንቱ ሆኗል ማለት ነው፡፡ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮችን የድምፅ አሰጣጥ ሒደት አስመልክቶ ቦርዱ ከድምፅ መስጫ ቀን በፊት ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን በሶማሌ ክልል በቅሬታ ሳቢያ ታግደው ከነበሩ 14 የምርጫ ጣቢያዎች ውጪ፣ 37.4 ሚሊዮን መራጮች መመዝገባቸውንም አስታውቋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *