ልዩነት ማምጣት፣ ጥቂት የማሰላሰያ ጥያቄዎች ፡ ክፍል 3

 

3.2 ታሪኩ ትክክለኛ ነው?

ሁሉንም መረጃ በትክክል ተረድተነዋል? በታሪኩ የተካተቱ መረጃዎችን አጣርተናል? በእኛ እና በግጭቱ ተሳታፊዎች ያለ እውነት እና አስተያየትን መለየት ችለናል? የተነገረንን ሁሉ አምነን ተቀብለናል ወይስ እውነት የማይመስሉትን ሐሳቦች ለማጣራት ጥያቄ አቅርበናል? ሰዎች ሁኔታውን እንዲረዱ ለማስቻል ስለ ግጭቱ መነሾ በቂ መረጃ ሰጥተናቸዋል? ሁሉም ግጭቶች የተወሳሰቡ ስለሆኑ ዐውዳቸውን በማገናዘብ ሊዘገቡ ይገባል።

ትክክለኛ መሆን ሲባል የተነገረንን ሪፖርት ማድረግ ማለት አይደለም። የምናሰራጨው መረጃ በተቻለ መጠን የተረጋገጠ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ማለት ነው። ይህ ማለት ከምንጮቻችን የምናገኘውን መረጃ አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ በማድረግ የሚከተሉት ጥያቄዎችን አፅንኦት ሰጥቶ መመርመር።

ጥያቄዎች:

  • ምንጩ ታማኝ ነው? ምንጩ ስለጉዳዩ በቂ ዕውቀት ኖሮት በበላይነት ማስረዳት የሚችል ነው?
  • ምንጩ በጉዳዩ ላይ ልዩ ጥቅም አለው? ምንጩ መረጃውን ለራሱ ድብቅ አጀንዳ መጠቀሚያ እያደረገው ይሆን?
  • መረጃ ልናገኝባቸው የምንችል ገለልተኛ ምንጮች አሉ?
  • የተለያዩ ምንጮች የሚነግሩን ነገር ተመሳሳይ ነው?
3.3 ተፅዕኖ?

የምንሠራው ታሪክ ተፅዕኖ ምንድነው? ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት እንዴት ያዩታል? ታሪኩ የጠቀመው ግጭትን ለማባባስ ወይስ መግባባት እንዲኖር በማድረግ ነው? እርስዎ ከግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች አንዱ ቢሆኑ ታሪኩን እንዴት ያዩታል? ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች አማራጭ ሐሳቦችን እንዲያዩ አደረገ ወይስ ነውጥ እና ብጥብጥ ብቸኛ አማራጮች ሆኑ?

3.4  ኃላፊነት?

ታሪኩን የሠሩበት መንገድ የማንን ጥቅም አስጠብቋል? ቀዳሚ ዓላማዎች በተቻለ መጠን ተደራሾችዎን ማገልገል ነው ወይንስ ሌሎች በግጭቱ ተሳታፊ አካላትን ለመደገፍ ሞክረዋል? ለታሪኩ ተገቢ ጥንቃቄ ተወስዷል? በግጭት ውስጥ ትንሽ ድርሻ ባለው አካል የተሰጠ ፀብ-አጫሪ አስተያየት ጥሩ ታሪክ ቢወጣውም እሱን ተንተርሶ ሰፋ ያለ ታሪክ መሥራት ግን አሳሳች ሊሆን ይይላል። ይህ ሁኔታ በጥንቃቄ ልናስተውለው የሚገባ ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ አንድ ፀብ አጫሪ አስተያየትን ከተነገረበት ዐውድ ውጪ ለይቶ ማቅረብ ለተደራሾች የተዛባ መረጃ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

የሚሠሩት ዘገባ ለወደፊት ታማኝ የመረጃ ምንጭ መሆንዎ ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል? ታማኝነትዎን ባጡ ቅፅበት በግጭት ወቅት በጎ አስተዋፅዖ ማበርከት የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ለጋዜጠኞች የፍተኃትን መርሕ መጠቀም በጣም አሰፈላጊ ነው። በተለይም በማኅበረሰባቸው አካባቢ የሚገኝ አነስተኛ የሚዲያ ተቋም ለሚሠሩ ጋዜጠኞች። ተከታታዮቹ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ብዙኃን መገናኛዎችን በቅርበት በመከታተል ጋዜጠኞቹ ወይም መገናኛ ብዙኃኑ ከዚህ ወይም ከዚያ መወገን አለመወገናቸውን ማረጋገጫ ይፈልጋሉ።

ማስታወሻ

ይህ ሐሳብ ግጭት ይበልጥ እንዲባባስ ሊያደርጉ የሚችሉ አስተያየቶችን የሚመለከት ቢሆንም ሰላምን ስለሚደግፉ አስተያየቶችም ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል። በግጭቱ ተሳታፊ ቡድን አባል የሆነ አንድ ሰው የትብብር አካሔድን ስለመከተል ቢናገር፣ የሱ አመለካከት ሁሉም አካላት ይሥማሙበታል ማለት አይደለም። በሌላ በኩል፣ ከልክ በላይ አዎንታዊ ምስልን ማቅረብ በተመሳሳይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ምክንያቱም ሰዎች ሒደቱ የወደፊት ተስፋቸውን እንደሚያጨልምባቸው ሊገምቱ ይችላሉ። አዎንታዊውን ነገር ማጋነን፣ አሉታዊውን ነገር ከማጋነን እኩል አደገኛ ነው።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *