የዓለማችን ባለጸጋና ኃያላን አጋራት ማኅበር የሆነው የቡድን 7 መሪዎች በዩናይትድ ኪንግደም ኮርንዎል ውስጥ በሳምንቱ ማብቂያ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ በተለያዩ የዓለማችን ጉዳዮች ላይ መክረው አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።
በዋናነት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ጃፓን የሚገኙበት የቡድን 7 አገራት መሪዎች ከአርብ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ያካሄዱት ስብሰባ በወቅታዊ የዓለም ጉዳዮች ላይ መክረው 25 ገጾች ያሉት ባለሰባ ነጥብ መግለጫ አውጥተዋል።
ከእነዚህም ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ያለው ቀውስና የፖለቲካ ሁኔታን በሚመለከት አገራቱና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ሲያነሱ የነበሩትን ሐሳቦች በድጋሚ አንጸባርቀዋል። በዚሁ መሠረትም ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭትና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ አደጋ ያጋለጠውን ጨምሮ እየወጡ ባሉት ሪፖርቶች የሚጠቀሱ ዋነኛ የሰብአዊ ሁኔታ ቀውስ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
አክለውም “መጠነ ሰፊ ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ” በክልሉ ቀጥለዋል ያሏቸውን “እጅግ አሰቃቂ ድርጊቶችን” አውግዘው፤ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እያካሄደ ያለውን የመብቶች ጥሰት ምርመራን በአውንታዊ መልኩ እንደሚመለከቱት በመጥቀስ፤ በክልሉ ተፈጽመዋል ስለተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖርና ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ምርመራ እያደረገ መሆኑን እንዲሁም በድርጊቶቹ ተሳትፈው የተገኙትን ለፍርድ ለማቅረብ ቃል መግባቱ ይታወሳል። በቅርቡም የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንደተናገሩት በጾታዊ ጥቃቶች ውስጥ ተሳትፈው የተገኙ ከ50 በላይ ሰዎች በመርመራ እንደተደረገባቸውና ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
የቡድን 7 አባላቱ በመግለጫቸው እየተካሄደ ያለው ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ በሁሉም አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ ያልተገደበ ሁኔታ እንዲመቻች እና የኤርትራ ኃይሎች በአፋጣኝ እንዲወጡ ጠይቀዋል። በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተለያዩ ወገኖች ክስ የሚቀርብበት የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጣ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የቆየ ሲሆን ሁለቱ አገራትም በወታደሮቹ መውጣት ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ከወራት በፊት መገለጹ አይዘነጋም። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መውጣት መጀመራቸውን ገልጿል።
የቡድን 7 መግለጫ በተጨማሪም በአገሪቱ ለተከሰተው ቀውስ ብቸኛው መፍትሔ ሁሉም ወገኖች ተአማኒነት ያለው ፖለቲካዊ ሂደት እንዲከተሉ አሳስቦ፤ በዚህም “የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች የሚከበርበት ሁኔታን ለመፍጠር ሰፊ ሁሉን አካታች ፖለቲካዊ ሂደት እንዲፈጥሩና ብሔራዊ እርቅን እንዲያበረታቱ” ለኢትዮጵያ መሪዎች ጥሪ አቅርቧል።
በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በትክክል የሚታወቅ አሃዝ እስካሁን ባይኖርም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚጠብቁ የረድኤት ድርጅቶች መረጃ ያመለክታል። የተባበሩት መንግሥታትና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በአፋጠኝ የረድኤት አቅርቦት ማድረስ ካልተቻለ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ሁኔታ ወደ ሰብአዊ ቀውስ ተሸጋግሮ በርካቶች በረሃብ ሊሞቱ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ባለፈው ሳምንት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦት እንዲካሄድ መፍቀዱን በተደጋጋሚ ከማሳወቁ በተጨማሪ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች አስፈላጊውን እርዳታ ከአጋሮቹ ጋር እያቀረበ መሆኑን በመግለጽ፤ ረሃብ እንዲከሰት የሚያደርግ ሁኔታ የለም ብሏል።
የቡድን 7 ሌሎች ዋነኛ ጉዳዮች
ምንም እንኳን የአውሮፓ ሕብረት የቡድን 7 አባል ባይሆንም ዋነኛ የጉባኤው ተሳታፊ በሚሆንበት የኃያላኑ አገራት ስብሰባ ላይ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተነስተው እንደተወያዩና አባላቱ አቋማቸውንና የውሳኔ ሐሳባቸውን በማጠቃለያቸው ላይ ይፋ አድርገዋል። የቡድን 7 አገራት በመጨረሻ ላይ ባወጡት ሰነድ ላይ በዋናነት የጋራ አቋም የያዙባቸው ጉዳዮች የተባሉት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝኛ የክትባት አቅርቦት፣ በሽታውን ተከትሎ የተጎዳውን ኤኮኖሚ እንዲያገግም ማገዝ፣ ነጻና ፍትሃዊ ገበያን የተመለከተ፣ የአየር ጸባይ ለውጥን መዋጋትን እንዲሁም ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖርን ትብብር የተመለከቱ ናቸው።
በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ከመከላከል አንጻር ባለጸጋዎቹ የቡድን 7 አገራት ተጨማሪ አንድ ቢሊየን ብልቃጥ የመከላከያ ክትብት በሚቀጥለው አንድ ዓመት ውስጥ ለድሃ አገራት ለመስጠት ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት የማምረት አቅምን ለማጎልበት ከመወሰናቸው በተጨማሪ፤ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት ቀድሞ የማስጠንቀቂያ ሥርዓት ስለመዘርጋትና ክትባቶችን ለማግኘት የሚወስደውን ጊዜ ለማሳጠር ለሚደረግ ሳይንሳዊ ጥረት ድጋፍ ለማድረግም ተስማምተዋል።
ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘም የቡድኑ አባል አገራት መሪዎች የዓለምን ሙቀት መጨመር ከ1.5 ሴሊሺየስ በላይ እንዳይሆን ለማድረግ “አረንጓዴ አብዮት” ለማካሄድ ቃል ገብተዋል። እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2050 የበካይ ጋዝ ልቀት ዜሮ እንዲሆን፣ አሁን ያለው የብክለት መጠን በግማሽ እንዲቀንስ እና ቢያንስ የመሬትንና የውቅያኖሶችን 30 በመቶ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ