[ከግራ ወደ ቀኝ] ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ ጄፈሪ ፌልትማን፣ ሳማንታ ፓዎር እና ማርክ ሎውኮክ

በትግራይ ያለው ሰብዓዊ ቀውስን በተመለከተ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት በበይነ መረብ አማካእነት ዛሬ ሐሙስ ውይይት አድርጋዋል።

ይህ በይፋ በቀጥታ በተላለፈው የበይነ መረብ ውይይት ላይ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር፣ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ተገኝተዋል። በተጨማሪም የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌነርቼክ እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ተሳታፊ ሆነውበታል።

አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በትግራይ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የመፈተኛ ወቅት በማለት “በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል ወይም በሚዘገንን ሁኔታ ጥቃት ደርሶባቸዋል” ብለዋል። አምባሳደሯ ሆስፒታሎች፣ የእርሻ ቦታዎች እና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች ሆን ተብሎ እንዲወድሙ ከመደረጋቸው በተጨማሪ ሚሊዮኖች ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል ብለዋል።

“ክስተቱ ወደ ሰው ሰራሽ ሰብዓዊ ቀውስ ተሸጋግሯል” ሲሉ ሊንዳ ቶማስ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌነርቼክ በበኩላቸው፤ ጦርነቱ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ ተቋማቸው የአውሮፓ ሕብረት ግጭቱ እንዲቆም እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል። ጨምረውም የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ለቆ እንዲወጣ ማሳሳባቸውንም ገልፀዋል።

ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ስልታዊ የሲቪል ሰዎች ግድያ፣ ሰፊ ጾታዊ ጥቃት ብሎም የሲቪሎች ርሸና በትግራይ ክልል ተፈፅመዋል ብለዋል። “በአስርተ ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ብሎም ለማስቀረት የሚቻል የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳዩ መረጃዎች ከትግራይ እየወጡ ነው” ሲሉ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

“ንሑሃንን ለጦርነት አላማ ብሎ ማስራብ ትልቅ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በአስቸኳይ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ያሏቸውን ሦስት ነጥቦችን ዘርዝረዋል። የመጀመሪው የሰብዓዊ እርዳታን ማዳረስ ሲሆን፣ ሁለተኛው ነጥባቸው ንሑሃን ከየትኛውም አይነት ግጭት መካከላል ነው ብለዋል። በመጨረሻም “ከየትኛው ጊዜ በላይ የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ የሚሆን ፈንድ ማድረግ አሁን ያስፈልጋል” ብለዋል ኮሚሽነሩ።

የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይን ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው ችግር ለምሥራቅ አፍሪካ የሚተርፍ ጫና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል። “. . . የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረብናቸው ጥሪዎች መልስ በማጣታቸው በጣም አዝናለሁ” ብለዋል። “ሁላችንም ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ እንደማይመጣ እናውቃለን” ስለዚህም ጥረታችንን መጨመር ይገባናል ሲሉ ኮሚሽነሯ አሳስበዋል።

ሁለት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል። የመጀመሪያው በሚመከለታቸው አካላት ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረግ ሲሆን ቀጥሎም ድጋፍ የሚፈልጉትን መድረስ ይገባል ብለዋል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር “በትግራይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ የኢትዮጵያ ወታደሮች፣ የአማራ ክልል ኃይሎች ከኤርትራ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የጾታዊ ጥቃትን ስልታዊ በመሆነ መንገድ እንደ የጦርነት መሳሪያ መጠቀማቸውን የሚሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል” ሲሉ ሳማንታ ተናግረዋል።

“ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤሌክትሪክ እና የሞባይል ስልክ ቢያቋርጡም፣ የጤና ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ላይ ያደረሱትን ጉዳት እናውቃለን” ሲሉ አስተዳዳሪዋ ተናግረዋል።

“ዐቢይ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ሰላም በማምጣታቸው የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል። ነገር ግን ይህንን ጥቃት ካላስቆሙ እና የኤርትራ ሠራዊትን ካላስወጡ፤ የኢትዮጵያን የረሃብ ታሪክ በመድገም የሚታወሱ መሪ ይሆናሉ” ብለዋል።

የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ
የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ

በውይይቱ ማን ምን አለ?

የሲኤንኤን ጋዜጠኛዋ ኒማ ኤልባጊር በመራችው የፓናል ውይይት ላይ፤ የፓናሉ ተሳታፊዎች በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሠራዊት ተፈጽመዋል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አንስተዋል።

ፓወር፣ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ “በአሁኑ ወቅት በትግራይ ረሃብ አለ” ብለዋል።

ሎውኮክ ኢንተግሬትድ ፉክ ሴኪዩሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽንን ዋቢ አድርገው ለረሃብ የተጋለጡት ሰዎች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ኢኒሺዬቲቭ የሆነው አይፒሲ ከ5.5 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 350ሺህ የሚሆኑት ረሃብ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብሏል። ግጭት እና መፈናቀል ደግሞ ሰዎችን ለአደጋ የዳረጉ ጉዳዮች መሆናቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሎውኮክ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ሰብዓዊ እርዳታ ሰዎች ጋር እንዳይደርሱ እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል። “የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ የሚፈጸም ጥቃትን እንመዘግባለን። ጥቃቱን የትኛው አካል እንደሚያደርስም መዝግበን እንይዛለን” ያሉት ሎውኮክ፤ በፓናል ውይይቱ ላይ ወቅታዊ የሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ የሚደረግ ጥረት ሪፖርት ደርሶኛል ብለዋል።

“131 ክስተቶች ሪፖርት ተደርገዋል። ከእነዚህ መካከል 50ዎች በኤርትራ ሠራዊት፣ 54 በኢትዮጵያ ወታደሮች፣ 4 በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ወታደሮች ጥምረት፣ 21 በአማራ ሚሊሻዎች እንዲሁም 1 በህወሓት ታጣቂዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይስ ተደርጓል” ብለዋል።

ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው ሁሉም አካላት እንዲተባበሩት እና የሚደረገውን የሰብዓዊ እርዳታ ከፍ እንዲል ለዓለም አቀፍ ድጋፍ አድራጊዎች ጥሪ አቅርበዋል።

የኖርዌ ስደተኞች ካውንስል ዋና ጸሐፊ ያን ኢግላንድ በትግራይ እና በትግራይ ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅት ሠራተኞች አሉ ያሉ ሲሆን፤ የሰብዓዊ እርዳታውን ለማቅረብ ድርጅቶች ባይገደቡ ለበርካቶች ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የሰብዓዊ እርዳታውን ለማቅረብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አብሮ የመሥራት አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል። “ከኢትዮጵያ ተቋማት ጋር አብረን ተባብረን መስራት አለብን። በኢትዮጵያ እንግዶች ነን። ሁሉንም ለመድረስ ከመንግሥት ተቋማት ጋር አብረን መስራት አለብን” ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግጭት ውስጥ የሚከሰት የጾታዊ ጥቃት የዋና ጸሐፊው ልዩ ተወካይ ፕራሚላ ፓተን የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች፣ ሴቶች መሠረታዊ ቁሶች ለማግኘት ወሲብ ለመፈጸም እንደተገደዱ የሚያመለክቱ በርካታ ሪፖርቶች ሲወጡ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ፕራሚላ፤ “እጅግ አስቀያሚ ታሪኮችን እየሰማን ነው። እነዚሁ ሁሉ ሪፖርቶች በተመድ የተረጋገጡ ባይሆኑም የሚታለፉ ግን አይደሉም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የመዘገባቸው ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መኖራቸውን አስታውሰው ኢሰመኮ እና የባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ላይ ምርመራ ማድረግ መጀመራቸው ጥሩ ነገር ነው ብለዋል።

ጄፍሪ ፌልትማን

በውይይቱም መጨረሻ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል። ፌልትማን ነገ የቡድን ሰባት (ጂ7) አገራት ሰብሰባ እንደሚኖራው ገልጸው፤ ከጂ7 አገራት አጀንዳዎች መካከል የኢትዮጵያ ጉዳይ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ጉዳይም የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል። ፌልትማን ረሃብ የጦርነት መሳሪያ ተደርጎ መወሰዱ የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት አጀንዳ ያደርገዋል ሲሉም ተደምጠዋል።

ተኩስ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረስ እና የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ጫና ማድረጋችንን መቀጠል አለብን ብለዋል። የቡድን ሰባት አባል አገራት የሆኑት ካናዳ፣ ፍረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ 47ኛ መደበኛ ስበሰባቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደርጋሉ።

ፌልትማን አፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት መጓዛቸውን እንዲሁም ከጂ7 አገራት እና የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ጋር መነጋገራቸውን ተናግረው፤ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

 

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *