በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች “በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናገሩ።

ዋና ጸሐፊው እንዳስጠነቀቁት የእርዳታ ድጋፍና የረድኤት አቅርቦት ካልተሻሻለ በክልሉ ያለው ሁኔታ “የበለጠ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል” ብለዋል። “ችግሩን ለመቅረፍ አሁን የምንወስደው እርምጃ በበርካታ ሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ልዩነትን ይፈጥራል” ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ሳምንት የከፋው የ1977ቱ ረሃብ ሊደገም እንደሚችል አስጠንቅቛል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በትግራይ ክልል ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ እንደተጋለጡ በመግለጽ የከፋ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው የቃፍታ ሁመራ ነዋሪዎች የነበራቸው ምግብ በማለቁ በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በአካባቢው ያሉ ሽፍቶች ንብረታቸውንና ከብቶቻቸውን በመዝረፋቸው በአሁኑ ጊዜ በእጃቸው ላይ የሚበላ ነገር እንደሌላቸው ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ ጨምረውም ሰብዓዊ እርዳታ ለማግኘት ወደ ሽሬ ለመጓዝ ቢፈልጉም በአካባቢው በሚገኙ ታጣቂዎች ጉዞዎች የተገደቡ በመሆናቸውና የትራንስፖርት ችግር መኖሩንም አክለዋል።

ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ አንድ ነዋሪ “ምንም ዓይነት እርዳታ የሰጠን አካል የለም። ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ በሞት አፋፍ ላይ ነው። የዓይኖቻችን ቀለም እየተለዋወጡ ነው። ሁኔታው አደገኛ ነው” ሲል በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግሯል። ነዋሪዎቹ ጨምረውም የተከሰተው ችግር ተባብሶ የነዋሪውን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣሉ በፊት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለመንግሥትና ለእርዳታ ድርጅቶች ጥሪ አቅርበዋል።

በአካባቢያቸው የእርዳታ አቅርቦት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ሲያልፉ ማየታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ እነሱ ስላሉበት ሁኔታ ግን አስካሁን ለመጠየቅ የሞከረ የለም ብለዋል። ምዕራባዊው የትግራይ ዞን ከኅዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የተያዘ ሲሆን በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ በመጠቀም አካባቢውን ለመቆጣጠር ተጠቅመዋልም ተብሏል።

ቀደም ሲል አንድ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባል ለቢቢሲ እንደገለጹት የአማራ ክልላዊ መንግሥት የምዕራብ እና የደቡብ ዞኖችን አንዳንድ አካባቢዎች እያስተዳደረ በመሆኑ በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ ምንም እውቀት እንደሌላቸው ገልጸው ነበር።

በአማራ ክልል የተሾሙት የአካባቢው አስተዳዳሪ አቶ እሸቴ ደምለው የፌደራል መንግሥት ለአካባቢው ነዋሪዎች እርዳታ እየሰጠ አለመሆኑን ጠቅሰው ውስን ድጋፍ ከአማራ ክልል ብቻ እየተሰጠ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት ችግሩ በተጠቀሰው አካባቢ እንዳለ እንደሚያውቁ የተናገሩት አስተዳዳሪው፤ ነገር ግን ያለው ሁኔታ ከአቅማቸው በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አስተዳደር ግጭቱን ለመግታት እና በግጭቱ የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት የበለጠ እንዲሠራ ግፊት እያደረጉ ነው። በአስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ በክልሉ እንዲቀርብ ካልተደረገ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተከሰተውን አይነት አስከፊ ረሃብ ሊደገም ይችላል በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን አስቸኳይ የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርቧል።

የፌደራል መንግሥቱ ግጭቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ወደ ተለያዩ የትግራይ ክልል ክፍሎች እያሰራጨ መሆኑን ገልጿል። ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የፌደራል መንግሥቱ ወታደራዊ ካምፖች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ሰባት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸው ተነግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 1.8 ሚሊዮን ሰዎችን ለመድረስ መቻሉን አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለችግር የተጋለጡ የክልሉን ነዋሪዎች ለመድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርሱ እየሠራሁ ነው ብሏል።

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *