ኢትዮጵያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ በነበረው የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ዓይነት የውጭ ግንኙነት ምዕራፍ የመመለስ ፍላጎት የላትም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን ያለው በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት ስማቸው ባልተጠቀሱ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የባለሥልጣናት ላይ የጣለውን የጉዞ ዕገዳ ተከትሎ በተደረጉ ሕዝባዊ ሠልፎችና አስተያቶች፣ ኢትዮጵያ ከምዕራባውኑ አገሮች ፊቷን የማዞር አዝማሚያ እያሳየች ስለመሆኗ አስመልክቶ ለቀረበ ጥያቁ ምላሽ በተሰጠበት ወቅት ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከማንኛውም አገር ጋር ጠንካራ ግንኙነት የመመሥረት ዓላማ አለው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምሥራቅ ሆነ ምዕራብ፣ ሀብታምና ደሃ ሳትል ከሁሉም አገሮች ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደምትሻ ተናግረዋል፡፡
ከሳምንት በፊት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳዳር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን የገቢ ማሰባሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣውን የጉዞ ዕገዳ አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹ከአሜሪካ የሚቀርብልን የነቀዘ ስንዴ መጣም ቀረም…›› ማለታቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቃል አቀባዩ በሰጡት ምላሽ፣ ምንም አንኳ የውጭ ግንኙነት ሥራ ዋነኛ አዝማች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሆንም፣ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት በተወሰነ ደረጃ ኃላፊነት ሊኖራቸው እንደሚችል በመጥቀስ፣ ከሰሞኑ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሌሎች አካላት የሰጡት አስተያየት ግን የግለሰቦች አስተያየትና ስሜት ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የተፈጠረውን ችግር ማጋጋል እንደማይፈልግ በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ካልተገደደች በስተቀር አገሮችን ከዚህኛው ያኛው ይሻለኛል ብላ የምትመርጥበት ሁኔታ እንደማይኖርና የወዳጅ ምርጫ ውስጥ የምትገባበት ጉዳይ አለመኖሩን አክለዋል፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹ግንኙነቱ የእኛን ነፃነት፣ ልማትና ዕድገት ችግር ላይ የሚጥል በሚሆንበት ጊዜ ቀይ መስመር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው ሁኔታ ‹‹ስቅታ›› ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹ይህም ጊዜያዊ ስለሆነ ሊቀየር አንደሚችል እርግጠኞች ነን፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ከሳምንት በፊት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ቃል አቀባዩ ከአሜሪካ መንግሥት በኩል እንዲህ ዓይነቱን በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ተመልሶ ለማጤን እንደሚገደድ በመጥቀስ፣ ጉዳዩ ከግንኙነቱ ባለፈ ሌላ አንድምታ ሊኖረው እንደሚችል መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዲና (አምባሳደር) በሰሞነኛው መግለጫቸው ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ቀርቶ፣ ጎረቤት ሱዳን በኢትዮጵያ መሬት ላይ ወራራ አካሂዳ መንግሥት በትዕግሥት ለመፍታት እንጂ ለማጋጋል አልፈለገም ብለዋል፡፡ ከአሜሪካ ጋር አሁን የተፈጠረውን ችግር በእርግጠኝነት መቀየር ይቻላል ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ግንኙነቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ንግግሮች (good will missions) በቅርቡ እንደሚኖሩ በመጥቀስ፣ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የነበሩት የሪፐብሊካን ሴናተር ጂም ኢንሆፍን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ ወዳጆችና በሲቪክ ማኅበራት አማካይነት ንግግር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል ይወጣሉ ተብሎ በሁለቱ መንግሥታት ስምምነት ከተደረገ ሁለት ወራት ያለፉ ቢሆንም፣ እስሁን ስለመውጣታቸው ግልጽ መረጃ ለምን አልተሰጠም ብሎ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ቃል አቀባዩ፣ ‹‹አንድ ቀን እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን፤›› በማለት መልሰዋል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር