የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ወ/ሮ ቀለብ ሥዩምን በዕጩነት የመመዝገብ ሒደት መጀመሩንና ለሚወዳደሩባቸው ቦታዎች ቀደም ሲል አሳትሟቸው የነበሩት 1.3 ሚሊዮን የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዲቃጠሉ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ለፍርድ ቤት አስታወቀ።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደተናገሩት፣ ባልደራስ ፓርቲ ቀደም ሲል አስመዝግቧቸው በነበሩ ዕጩዎች ምትክ ማስመዝገብ የሚፈልጋቸውን ዕጩዎች እንዲያሳውቅ በመሥሪያ ቤታቸው በኩል ጥያቄ ቀርቦለታል። በዚህም መሠረት ፓርቲው ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲሶቹን ዕጩዎች ማሳወቁንም ገልጸዋል፡፡ ሰብሳቢዋ ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት እውነት መሆኑን፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ፓርቲ አመራር አባልና ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ አረጋግጠዋል፡፡

ባልደራስ ዕጩዎቹን ለማስመዝገብ እንዲችል በተተኪነት የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች ፎቶግራፍ እንዲያቀርብ ቦርዱ መጠየቁን አቶ ሔኖክ አክለዋል፡፡ በጥያቄውም መሠረትም የተተኪ ዕጩዎችን ፎቶግራፎች ለቦርዱ መስጠታቸውን ጠቁመው፣ ‹‹ማረጋገጥ የምንችለው የዕጩዎቻችንን ሰርተፊኬት ስንቀበል ነው፤›› ብለዋል። የዕጩዎች ሰርተፊኬት የመስጠት ሒደት በ30 ደቂቃ ውስጥ ማከናወን የሚቻል ቢሆንም፣ ቦርዱ ግን ይህን ማድረግ እንዳልቻለ አቶ ሔኖክ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በፍርድ ቤቱ የዕጩዎች ሰርተፊኬት ለመስጠት ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል የተጠየቁት ወ/ሪት ብርቱካን፣ በማግሥቱ ዓርብ ግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ለዕጩዎቹ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን ለፍርድ ቤቱ ጨምረው እንዳስረዱት፣ ሰበር ሰሚ ችሎት በዕጩነት እንዲመዘገቡ ውሳኔ ላስተላለፈላቸው በእስር ላይ በሚገኙት የባልደራስ አመራሮቹ ምትክ በዕጩነት አስመዘግቧቸው ለነበሩ ዕጩዎች ቦርዱ 1.3 ሚሊዮን ያህል የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን አሳትሞ ጨርሷል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከሁለት ሳምንት በፊት ቦርዱ እነ አቶ እስክንድር ነጋ (ሦስት ተከሳሾች)ን እንዲመዘግብ ሰጥቶ የነበረውን ውሳኔ ባለመፈጸም አንድ ጊዜ ለፓርቲው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለራሱ ለችሎቱ ‹‹ውሳኔውን ለመፈጸም ስለሚያዳግተኝ ቀርቤ እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ፤››  በማለት ሲያንገራግር ቆይቶ፣ ውሳኔውን ለምን እንደማይፈጽም ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሲደርሰው፣ ሰብሳቢዋ ፍርድ ቤት ቀርበው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እያስፈጸሙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በእስር ላይ ያሉ የባልደራስ አመራሮች ለምርጫ በዕጩነት መቅረብ እንደሚችሉ፣ ቦርዱም የታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በማቃጠል በሌላ እንዲተኩ የማድረግ ሒደት መጀመሩን አክለዋል፡፡ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን የሚያትመው ኩባንያም በሦስትና በአራት ቀናት ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ማስታወቁን ጠቁመው፣ አጠቃላይ ሒደቱ ቦርዱን 3.5 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ እንደሚያስወጣውም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለዕጩ ተወዳዳሪዎች ሰርተፊኬት መስጠት አለመስጠቱን ለመጠባበቅ፣ ለሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *