ፖለቲካዊ መነሻን ይዞ በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ውጊያና ውጊያውን በተከተለው ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስና ኢሰብዓዊ ጥሰቶች ምክንያት ሥጋቱን ሲገልጽና ግጭቱ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኝ ሲወተውት የነበረው የአሜሪካ መንግሥት፣ ባለፈው ሳምንት ውሳኔው ሥልጣን ላይ የሚገኙና የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የመከላለከያና የደኅንነት ዘርፍ ኃላፊዎች ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል። ከጉዞ ማዕቀቡ በተጨማሪም ከዓመት በፊት የተቋረጠው የኢኮኖሚና የመከላከያ ግንባታ ድጋፍም እንዳይለቀቅ ወስኗል።
ይህንን የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ኢትዮጵያ ተገቢ ያልሆነና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ፣ በአንድ ነፃ አገር ላይ የሚደረግ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት በማለት ማጣጣሏ ይታወቃል። ከዚህም እልፍ በማለት አሜሪካ በዚህ መንገድ የምትቀጥል ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ ጋር ያለውን የውጭ ግንኙነት መልሶ ለማየት እንደሚገደድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ፣ በባለሥልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣሉ በተጠናቀቀው ሳምንት ውስጥ የነበረና አሁንም የቀጠለ ዓብይ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። በተጠናቀቀው ሳምንት መጀመርያ ላይ የአማራ ልማት ማኅበር በአዲስ አበባ ለማስገንባት ላቀደው የባህል ማዕከል የይዞታ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ አጋጣሚውን መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ ተጠቅመውበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ብዙ ፀጋ ያላት ቢሆንም፣ የአገሪቱ ሕዝብ እርስ በእርስ የመተጋገዝና ተባብሮ መቆም ባለመቻሉ የአገሪቱን ፀጋ ወደ ሀብት መለወጥና መበልፀግ እንዳልተቻለ ገልጸው፣ ይህ እንዲሆንም ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭም የሚሠሩ ኃይሎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት እንፈልጋለን የሚሉ ብዙዎች እንዲሁ ትልቅ እያልናችሁ ኑሩ እንጂ፣ ትልቅ መሆን እምብዛም አያስፈልጋችሁም ይላሉ፤›› ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ይህንን የሚሉት እኛ የእነሱን ልጆች አዝለን ማሳደግ ግዴታችን እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው፤›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ ጥያቄዋ በኅብረት መልማትና መበልፀግ እንደሆነ በመግለጽም፣ ‹‹የሀብታም ልጆችን እያዘልን ማሳደግ ሳይሆን እርስ በርስ ተጎራርሰን ተደጋግፈን በኅብረት ማደግ፣ መለወጥና ሲተርፈን ሳናዝል መደገፍ የምንችልበት ቁመና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሊፈጥሩ ይገባል፤›› ብለዋል። ‹‹ይህም ሲባል ኢትዮጵያውያን ማለት ሕዝቦች ማለት አይደለም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ምክንያቱም ሕዝቦች ማለት ብዙዎች ማለት ነው። ብዙዎች ማለት በአንድ ሊጠሩ የማይችሉ የአፍሪካ ሕዝቦች እንደ ማለት ነው፤›› ብለዋል።
አክለውም፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ልንባል ሲገባን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተብለን ያንኑ እንደ በቀቀን እየደገምን በአንድ መቆም እስኪሳነን፣ አንደኛው ለአንደኛው ጋሻ መሆን ሲገባው እንቅፋት እንዲሆን ስላደረገን ነው ስሙንም ግብሩንም ሆነ ዕሳቤውን ፈንቅለን ጥለን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብልፅግና ይገባዋል ያልነው፤›› ሲሉ ተደምጠዋል። ነገር ግን የብልፅግና ጉዞ ቀላል አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ከተባበርን እንለወጣለን፣ ከተባበርን እንበለፅጋለን፣ ከተባበርን ልክ እንደ አባቶቻችን ማንም አይደፍረንም፤›› ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካስተላለፉት መልዕክት ጋር ቀጥተኛ ግንኙት ባይኖረውም፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታን የተመለከተ መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በተላለፈ በሁለተኛው ቀን ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሐሙስ ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ እየጨመረ ነው ባሉት ግጭትና በተለያዩ የአገሪቱ በክልሎች፣ እንዲሁም በብሔረሰቦች መካከል እየተስተዋለ ነው ያሉት መከፋፈልና መካረር በእጅጉ እንዳሳሳባቸው ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ፆታዊ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ሊቆም ይገባል ብለዋል። ከየትኛውም ብሔረሰብ የተገኘ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ የብሔረሰብ ክብሩ፣ እንዲሁም ሰላሙና ደኅንነቱ ተጠብቆ በአገሩ ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቁስሎችን በጦር ኃይል ማከም እንደማይቻል በመግለጽም፣ በትግራይ ክልል ግጭት የሚሳተፉ ኃይሎች ግጭቱን በፍጥነት እንዲያቆሙ፣ የአማራ ክልል ኃይልና የኤርትራ ጦርም በአስቸኳይ ከትግራይ ክልል ሊወጡ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መሪዎችና ተቋማት በአገሪቱ ብሔራዊ ዕርቅ እንዲፈጠርና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ እንዲሁም የአገሪቱ ብዝኃነት እንዲከበርና እንዲጠበቅ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው አሳስበዋል። ‹‹ይህንን ማድረግ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊ ግዛት ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ደኅንነትንና አስፈላጊ የሆነ አስቸኳይ ዕርዳታ መድረሱን ለማረጋገጥም ያስችላል፤›› ብለዋል። ኢትዮጵያ ብዝኃነቷ ተከብሮና ተረጋግጦ እንድትቀጥልም የአገሪቱ መንግሥትና ሁሉም የፖለቲካ ልሂቃን ሁሉን አቀፍ የሆነ ውይይት እንዲደረግ በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው የገለጹት ፕሬዚዳንት ባይደን፣ በዚህ መንገድም ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ቀጣይ የፖለቲካ ራዕይ በጋራ መቅረፅና ለጋራ ብልፅግናና ተጠቃሚነት መሠረት መጣል እንዳለባቸው ገልጸዋል። የአሜሪካ መንግሥትም በዚህ መንገድ የሚደረግ ጥረትን ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል በቅርቡ የመንግሥታቸው ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በኢትዮጵያ ተገኝተው የነበሩት ጄፍሪ ፊልትማን ሰሞኑን ለተመሳሳይ ሥራ ዳግም ወደ አካባቢው እንደሚጓዙ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በተለያዩ የዓለም አገሮች የተከሰቱ ግጭት ወለድ ሰብዓዊ ቀውሶችን አስመልክቶ ባካሄደው ውይይት፣ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ የውይይቱ አንዱ ትኩረት ነበር። በዚህ የፀጥታ ምክር ቤቱ ውይይት ላይ የአሜሪካ መንግሥት ተወካይ ባደረጉት ንግግር፣ የትግራይ ክልል ቀውስ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ የአሜሪካ መንግሥት ለሰብዓዊ ቀውሱ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጨምሮ፣ ሌሎች የግጭቱ ተሳታፊዎችን ተጠያቂ ያደረገ ዕርምጃ መውሰዱን በማስታወቅ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። የፀጥታ ምክር ቤቱ ሰላማዊ ዜጎች በግጭቶች ምክንያት ደኅንነታቸውን እንዳያጡ ለመጠበቅ የሚችልበት አንዱና ውጤታማው አማራጩ የሰላም አሰከባሪ ኃይል ሥምሪት መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንን ለማድረግ ግን የሚሰማራው ኃይል የፖለቲካ፣ የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘት ሲችል እንደሆነ ተናግረዋል።
የእንግሊዝ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በማራመድ የፀጥታ ምክር ቤቱ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስቸለውን በእጁ የሚገኝ አማራጭ በሙሉ መጠቀም እንደሚገባውና ማዕቀብ መጣልም አንዱ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል። ከእንግሊዝና አሜሪካ አቋም ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ በማራመድ ዕርምጃ እንዲወሰድ ከጠየቁ የፀጥታ ምክር ቤቱ አባል አገሮች መካከል ኖርዌይ፣ አይርላንድ፣ ሜክሲኮ ይገኙበታል። በሌላ በኩል ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና ተመሳሳይ አቋም በማራመድ በአሜሪካና በእንግሊዝ መሪነት የተራመደውን ሐሳብ ተቀናቅነዋል። በተለይም ሩሲያና ህንድ ከዚህ ቀደም ካራመዱት ሙግት በተጨማሪ፣ ሽብርተኞች በሰብዓዊ ቀውስ ሽፋን እንዳያደናግሩ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግና ሰብዓዊ ቀውስን አስመልክቶ በሚያሠራጩት ሐሰተኛ መረጃ ምክር ቤቱ እንዳይጠለፍ ሩሲያ አሳስባለች።
የሽብር ቡድኖች በሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀናቸውን የጠቀሰችው ሩሲያ ለአብነትም በሶሪያና በኢራቅ ያሉ ክስተቶችን አውስታለች። ይኼንን መነሻ በማድረግም የፀጥታው ምክር ቤት በተመድ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ሽብርተኝነትን በጋራ እንዲዋጋ የጠየቀች ሲሆን፣ ኢሰብዓዊ ወንጀሎችን በፈጸሙ ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ፣ ነገር ግን ይህ ጉዳይ ለፖለቲካ ጥምዘዛ አለመዋሉን መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ አሳስባለች።
የህንድ መንግሥትም በተመሳሳይ በሲቪል ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው አንዱ ጉዳይ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ይህንን የሽብርተኝነት ጉዳይ ሊዘነጋ እንደማይገባ አስታውቋል። የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት የመጠበቅና ደኅንነቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሠረታዊነት መተው ያለበት ለሚመለከታቸው መንግሥታት እንደሆነ፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚቀመጡ ብሔራዊ መፍትሔዎችን ሊተካ የሚችል ቋሚ አማራጭ እንደሌለ ተከራክሯል። የቻይና መንግሥትም በተመሳሳይ ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው ለችግሩ ሥር የሆነውን ፖለቲካዊ ጉዳይ መፍትታት እንደሚገባ፣ ይህ መፍትሔ ደግሞ ከሚመለከታቸው መንግሥታት ከውስጥ ብቻ መምጣት አለበት የሚል አቋም አራምዷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሕወሓትንና ኦነግ ሸኔን በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚታወስ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥት በቅርቡ ባፀደቀው የውሳኔ ሐሳብ የትግራይ ክልልን ቀውስ ለመፍታት ሁሉን አሳታፊ ውይይት እንዲደረግ መጠየቁን በመቃወም፣ ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀ ቡድን ጋር ውይይት እዲደረግ አሜሪካ መጠየቋን እንዳወገዘ ይታወቃል።
ምንጭ – ሪፖርተር