ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ዕጣ ፈንታ የሚወስን በመሆኑ፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ የሚጠቅመውን ሰላማዊ መንገድ በመተከል፣ ለአገርና ለወገን የሚጠቅመውን በመምረጥና ውጤቱንም በፀጋ በመቀበል፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚረጋገጥበት እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 17 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ያካሄደውን ዓመታዊ ጉባዔ (በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ያካሂዳል) ሲያጠቃልል ባስተላለፈው ማኅበራዊና መንፈሳዊው ውሳኔዎች እንዳሳሰበው፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሽግግር ላይ የምትገኝና ሕዝባዊ ምርጫ ለማካሄድ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ በመሆኗ፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅመውን ማድረግ አለባቸው፡፡ ሰላማዊ ሒደት እንዲኖረውና ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በፀጋ ተቀብለው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ማስመስከር እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በጉባዔ ማጠቃለያው ላይ ባለ 11 ነጥብ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ፣ ትኩረት ያደረገባቸው ነጥቦች ስለአገር ደህንነት፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለስደት ስለተዳረጉት ወገኖችና በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ስላሉ አለመግባባቶችን በሚመለከት ነው፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሕይወታቸው ያለፈ፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉና በተፈጠረው ችግር ምክንያት የወደመ ንብረት በዓይነትና በቁጥር ተጣርቶ እንዲቀርብለትም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ ተመዝግቦ የሚገኝን የመስቀል አደባባይና የባህረ ጥምቀት ቦታዎችን ምክንያት በመፍጠር ግጭትና ትንኮሳ እንደተፈጸመ ጠቁሞ፣ ይህ አካሄድ በአገሪቱ የነበረውንና የቆየውን ታሪካዊ ሒደት ለማስቀየር ያለመ መሆኑ እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ የአምልኮ ሥፍራና ተጠብቆ የቆየ ክብሯ እንዲሁም በካህናትና ምዕመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት ስደትና ውድመት በሚመለከት መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡
ዳር ድንበራን ጠብቃና አስጠብቃ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት፣ በአገር ወዳድ መሪዎቹ አንድነቷን ጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የውጭ አገሮች ከሩቅና ከቅርብ ግንባር በመፍጠር ያደረጉት ጣልቃ ገብነትና ድንበር የመድፈር ሙከራ፣ በተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ የተቃወመው መሆኑን በጉባዔው ወስኗል፡፡ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት ማሳያ በመሆኑ ሁሉም እንዲረባረብ፣ መንግሥት ያዘጋጀው በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ለአየር ንብረት ጥበቃና በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ሁሉም ዜጋ ችግኝ በመትከል የበኩሉን እንዲወጣም አሳስቧል፡፡
በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች፣ እንዲሁም በኮቪድ-19 እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ምክንያት በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን መርዳት አገራዊና ሃይማኖታዊ ግዴታ በመሆኑ፣ ሁሉም የተሻለ ወገን እጁን እንዲዘረጋላቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም አገረ ስብከት በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት፣ በሕገወጥ መንገድ ዶግማና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ፣ የራሳቸውን ጳጳስና ፓርትርያርክ መሾማቸውን ከእነ መነኮሳቱ፣ ካህናትና ዲቆናት አውግዟል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር