የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ በሰባት ክፍለ ከተሞች በተመረጡ 20 ቦታዎች ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ‹‹አካሄድኩት›› ባለው ፍተሻ፣ በዋና ዋና አደባባዮችና በምሽት ሰዋራ ሥፍራዎች የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ የነበሩ 999 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን በማወክ ከአሽከርካሪዎች ወይም ከተሳፋሪዎች ላይ ስልክ፣ የአንገት ሀብል፣ ቦርሳና ልዩ ንብረቶችን በጠራራ ፀሐይ ቀምተው እንደሚሰወሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ግለሰቦቹ በምሽት የቅሚያ ወንጀል ሲፈጽሙ እንደነበር በመረጋገጡ፣ በተለይም የውጭ አገር ዜጎችንና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን በማዋከብና በማስጨነቅ በከተማዋ ላይ አሉታዊ ገጽታ ሲፈጥሩ እንደነበር በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተወሰኑት ግለሰቦች የጎዳና ተዳዳሪ በመምሰል የሽብር ተግባር ለማስፈጸም ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ መገኘታቸውንም አስረድቷል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ብሔራዊ የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የ19 ከፍተኛ የሕወሓት ሹማምንት ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስና ሀብታቸው ላይ ዕገዳ መጣሉን አስታውቋል፡፡ በመግለጫው በአዲስ አበባ የሚገኙ ቋሚ ንብረቶቻቸውን በቤተሰቦቻቸውና በወኪሎቻቸው አማካይነት በማከራየትና ከፍተኛ ገቢ በመሰብሰብ ለሽብር ተልዕኮ እያዋሉ ባሉ፣ በሽብርተኝነት በተሰየመው የሕወሓት ቡድን አባላት ላይ የተጣለ ዕግድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ዕገዳ የተጣለባቸው ግለሰቦች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶችን በመፈጸም ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሰው የሕወሓት ቡድን ጋር በአመራርነትና በአባልነት እንደሚሳተፉ ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል ከሕዝብና ከአገር በመዘበሩት ሀብት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የገነቧቸው የመኖሪያ ሕንፃዎችና ያቋቋሟቸው የንግድ ድርጅቶች፣ በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቻቸው አማካይነት በማከራየት በወር እስከ ዘጠኝ ሺሕ ዶላር ይሰበስቡ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስና እንዲታገድ ከተደረገባቸው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አባላት መካከል ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት፣ ሌተና ጄኔራል ፍሰሐ ኪዳኑ፣ ሜጀር ጄኔራል ሐለፎም እጅጉ፣ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ግደይ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይለ ሥላሴ ግርማይ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ምግበ ኃይለይ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ተክላይ አሸብር፣ አቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ ሀሰን ሽፋ ይገኙበታል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ መቐለ ከተማ ሆነው ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲሰጡ፣ የፋይናንስና የሎጀስቲክ ድጋፎችን በድብቅ ሲያቀርቡ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብሶችን በመልበስ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩ 14 የሕወሓት አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና በሽብርተኝነት የተሰየመውን የሸኔ ቡድን በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ141 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲቋረጥና ገንዘባቸው እንዲታገድ መደረጉን፣ የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ለሸኔ ተገዝተው ሲላኩ የነበሩ 5,661 የክላሽንኮቭ ጥይቶች፣ 2,000 የብሬን መትረየስ ጥይቶችና ሌሎች ለጥፋት ተልዕኮ መፈጸሚያ የሚውሉ ቁሳቁሶችና ሰነዶች ከአዘዋዋሪ ግለሰቦች ጋር ቡራዩ፣ ጊንጪና ከአምቦ ወጣ ብሎ በሚገኘው ባቢች በተባለ ቦታ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አክሎ ገልጿል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *