ብልጽግና ፓርቲ ሐሰተኛውን ድምጽ አቀነባብረው ይፋ ያደረጉት ሕዝብ እና መንግሥት በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚፈልጉ የአገር ውስጥ እና የውጪ ኃይሎች ናቸው አለ።

የብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ “ዜጎች የራሳቸውን መንግሥት መርጠው ተቀባይነት ያለው መንግሥት ተመስርቶ ስኬታማ ሥራ እንዳይሰራ የሚሰሩ የውስጥ እና የውጪ ኃይሎች አሉ” ብለዋል። ቢቂላ (ዶ/ር) ዛሬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሐሰተኛው የጠቅላይ ሚንስትሩ ድምጽ ከየት ተቆርጦ እንደተቀጠለ የሚያሳይ ማስረጃ ለሕዝብ ይቀርባል።

ትናንት ምሽት ኬሎ የተባለ መቀመጫውን ከአገር ውጪ ያደረገ መገናኛ ብዙሃን ከአንድ ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በብልጽግና ስብሰባ ላይ የተናገሩት ንግግር ነው በሚል አንድ ቅጂ አስደምጧል።

በቅጂው ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፓርቲያቸው ምርጫው እንዲራዘም ፍላጎት እንዳለው፣ ለበርካታ ዓመታት በሥልጣን የመቆየት ፍላጎት እንዳላቸው እና ምርጫውን ከወዲሁ እናሸንፋለን ብለው ስለመናገራቸው ኬሎ ሚዲያ ዘግቧል።

የዚህ ድምጽ መሰማትን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት የተለቀቀው የድምፅ ፋይል በውሸት የተቀነባበረና እና ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለያዩ ጊዜያት የተናገሩትን በመቁረጥና በመቀጠል የተፈጠረ የሐሰት መረጃ መሆኑን አረጋግጣለሁ ብሎ ነበር።

ብልጽግና ፓርቲም በተመሳሳይ “ከስብሰባው የተወሰደ አንድም ቃል የሌለው፣ የፓርቲያችን ፕሬዝደንት በተለያዩ ጊዜያት ካደረጓቸው ንግግሮች የተወሰዱ ቃላትን በመገጣጠም የተቀነባበረ ሐሰተኛ ድምጽ ነው” ብሏል። ቢቂላ (ዶ/ር) ይህን ድምጽ ተቆርጦ የተቀጠለው ሙያውን ጠንቅቆ በማያውቅ ሰው በመሆኑ፤ “ሁሉም ድምጹን እንደሰማ መረዳት የሚችለው ነው” ብለዋል።

“ከአንድ ቦታ የተወሰደ ድምጽ አይደለም። በተለያዩ አጋጣሚዎች ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ የተናገሯቸውን እና በሚዲያዎች የተላለፉ ድምጾችን ቆርጦ በመቀጠል ነው ዓረፍተ ነገር ለማስመሰል የሞከሩት” ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር)፤ ድምጾቹ ከየትኛው የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ተቆርጠው እንደተቀጠሉ እየተለዩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *