ጋዜጠኞች ለሰላም ማስከበር፣ ለሰላም  ግንባታ እና ሰላም  መፍጠር እንዴት ሊያግዙ እንደሚችሉ ፥ ክፍል 3

 

2.8 የተለያዩ ገኖች ስሜታቸውን እንዲገልጹ መፍቀድ

በሽምግልና ሒደት ዙሪያ ባደረግነው ውይይት ላይ እስኪወጣላቸው በማናገር ስለ ‘ማስተንፈስ’ አስፈላጊነት ተነጋገርን ነበር። እናም በዚህ ረገድ ጋዜጠኞች ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ተሳታፊ ወገኖች ብስጭታቸው በሚያይልበት ጊዜ ጋዜጠኞቹ ስሜታቸውን በመገናኛ ብዙኃን በኩል እንዲገልጹ በመፍቀድ ስሜታቸውን የሚተነፍሱበት ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ ይችላሉ። ይህ ማለት በግጭት የሚሳተፉ የርስዎን ብዙኃን መገናኛ ተጠቅመው ሌሎችን ለመሳደብ እንዲጠቀሙበት መፍቀድ ማለት አይደለም፤ ግን ስለ ብስጭት እና ፍርሐታቸው እንዲናገሩ መፍቀድ ማለት ነው። ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆነው ‘ጌቲንግ ቱ የስ’ የተሰኘ መጽሐፋቸው ሮጀር ፊሸር፣ ዊልያም ዩሪ አና ብሩስ ፓቶን1      በድርድር ወቅት ሰዎችን ከችግር ለይቶ ስለማየት ጥቅም ያብራራሉ። እኛም ጋዜጠኞች ተሳታፊ አካላት ይህን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዲያበራታቷቸው እንመክራለን። ሰዎች በመገናኛ ብዙኃን ሌሎችን እንዲሰድቡ መፍቀድ አስደሳች ወሬ ሊገኝበት ይችላል፤ ነገር ግን በግጭት ተሳታፊዎቹም ሆኑ ተደራሾቻችን በትክክል እየተከናወነ ያለውን ሁኔታ እንዲገነዘቡ አይረዳቸውም። ሆኖም ሰዎች ስለ ፍላጎቶቻቸው እና ስለሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ለጋዜጠኞች የተናገሩት በመገናኛ ብዙኃን ተላልፎ ሲመለከቱ አንዳንድ ብስጭቶቻቸው ይወጣላቸዋል።

የተቃውሞ ሰልፎች እና ሌሎች ዓይነት ሰልፎች ብዙውን ጊዜ የሚዲያዎችን ትኩረት ለመሳብ የታቀዱ ናቸው። በግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በመገናኛ ብዙኃን ችላ እንደተባሉ ከተሰማቸው ሽፋን ለማግኘት የበለጠ አክራሪ ድርጊት ላይ ይሳተፋሉ። በደቡብ አፍሪካ ለዴይሊ ዲስፓች ጋዜጣ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ዕቅድ እንዳላቸው ወደ ዜና ክፍሉ ደውለው ባሳወቁ ሰዎች ሁኔታ ተፈትነው ነበር። ጋዜጠኞቹ ቦታው ላይ ሲደርሱ ሰዎቹ ሰልፉን ‘ከመጀመራቸው’ በፊት ተሰብስበው የሚዲያ አካል እስኪመጣላቸው እየጠበቁ ነበር። እንደነዚህ ያሉት ክስተቶች ጋዜጠኞችን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያስገቧቸዋል። ጋዜጠኞቹ በተገለጸላቸው መሠረት በቦታው መድረስ ባይችሉ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ትኩረት ለመሳብ  ከባድ ነውጥ የማስነሳት ስልት የመጠቀም ዕድላቸው ከፍተኛ እንደነበር ጋዜጠኞቹ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሆኖም ይህ ማለት ጋዜጠኞችን የጥላቻ ንግግርን ወይም የነውጥ ጥሪን ሳያጤኑ ለማሰራጨት ያስፈልጋሉ ማለት አይደለም። ባጭሩ ሜጋፎን መስጠት የእኛ ሚና አይደለም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ሰዎች ስለ ዓላማቸው ሊጠየቁ እና ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል።

2.9 ቡድኖችን ማጠናከር

ለተገፉ ወገኖች ድምፅ በመስጠት ጋዜጠኞች የኃይል ሚዛንን እንዲመጣጠን በማገዝ ረገድ በጣም ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ሽፋናችን ሚዛናዊ ከሆነ እና ደካማ ቡድኖችን ከኃያል ቡድኖች በተመሳሳይ መንገድ የምናስተናግድ ከሆነ፥ ሁለቱን ቡድኖች በተመሳሳይ ደረጃ ላይ በማስቀመጥ ደካማውን ቡድን ማብቃት ችለናል ማለት ነው።በግጭት ወቅት የበላይ የሆኑ ተሳታፊዎች ተቀናቃኞቻቸውን በጭራሽ አምነው ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው የተለመደ ነው። በብዛት ‘ወንበዴዎች’ ወይም ‘ወንጀለኞች’ በማለት ያጣጥሏቸዋል። ይህን በማድረግ አንድ ቡድን በግጭቱ ውስጥ ለምን እየተሳተፈ እንዳለ ለማወቅ ፈቃደኛ አይሆኑም፤ እንዲሁም ለወደፊቱ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ የተሸሸጉ ጉዳዮችን ችላ በማለት ያልፏቸዋል። ይህ በግልጽ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ማንኛውም የሰላማዊ ውይይት ዕድልን የሚገድብ ነው።

ስለዚህ ምን እናድርግ? የእኛ ሚና ሰዎች ውሳኔዎችን በሚያሳልፉበት ጊዜ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉትን መረጃዎች መስጠት እና ሰዎች በዓለም ላይ እየተከናወነ ያለውን ነገር እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። አንዱ የበላይ ቡድን ሌላውን ቡድን እንደ ‘ወንጀለኛ’ ስለቆጠረ ይህንን አቋም መቀበል አለብን ማለት አይደለም። ይህንን አቋም በመፈተን ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወት እንችላለን። በዜናዎች ላይ የተገፉ ቡድኖችን በማካተት፣ የበላይነት ያላቸው ቡድኖች ችላ እንዳይሏቸው ማድረግ እንችላለን።

በተመሳሳይ በግጭቱ ላይ ዋና ድርሻ ወይም ዋና ፍላጎት ለሌለው በጣም ትንሽ ለሆነ ቡድን ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠን እንዳይሆን ልንጥንቅቅ ይገባል። ይህን ችግር ለመፍታት ቀላል መንገድ የለም። እውነታው እኛ ትናንሽ ቡድኖችን ችላ የምንል ከሆነ ሁልጊዜ ዕውቅና እና ትኩረት ለማግኘት የነውጥ ዘዴዎችን የመጠቀም ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።

2.10 ገጽታ ጥበቃ እና ሥምምነት ማኖር

በብዙ የድርድር አጋጣሚዎች ውስጥ የቡድኖች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ግጭቶችን ለማቆም ማሻሻያዎችን መውሰድ እንደደካማነት በሚቆጠርበት ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ሲከብዳቸው ይታያል። አንዳንድ ጊዜ ይህ መዋረድ ወይም እጅ መስጠት ከማይፈልጉ መሪዎች ጋር ይዛመዳል። በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ በዙሪያቸው ያሉ አካላት ማሻሻያ ማድረጉን እንደ መዋረድ ሊያዩት ይችላሉ። በእንደዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ላሉ ወገኖች ‘እጅ ሰጠ’፣ ‘ተሸነፈ’፣ ‘አቆመ’ ወይም ‘አፈገፈገ’ የሚሉ የሚዲያ ዘገባዎች ስጋት ማሻሻያዎች ለማድረግ ፍላጎታቸው እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።ጋዜጠኞች ቃላት አጠቃቀማቸው ላይ ጠንቃቃ መሆን ይኖርባቸዋል። አንድ ቡድን ያለፍላጎቱ በኃይል ተገዶ እጅ ከሰጠ በትክክል አግባብ ያለው ሐረግ ነው። ሆኖም በሁለቱም ወገኖች በኩል ተጨማሪ የደም መፋሰስ እንዳይከሰት ለመከላከል በሚል ወይም እንደ ጥሩ እምነት መግለጫ ትንሽ ሥምምነት ካደረጉ እንዲህ ዓይነቱ ገለጻ ትክክለኛ አይሆንም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ስለምንመርጣቸው ቃላት መጠንቀቅ አለብን። ስሜት የማይቀሰቅሱ ቃላትን መምረጥ ብዙውን ጊዜ ተመራጭ ነው።

ምሳሌ:

“ይህ ፓርቲ በዚህ ነጥብ ላይ በመሥማማት ለዚያ ፓርቲ ፍላጎቶች እጅ ሰጥቷል” ከማለት ይልቅ፥

“ይህ ፓርቲ ያኛው ፓርቲ ያስቀመጣቸውን ሁኔታዎች ለሟሟላት ተሥማምቷል” ወይም “ይህ ፓርቲ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ተሥማምቷል”

ልዩነቱ ስውር ቢሆንም በግጭት ውስጥ ላሉ አካላት በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ፓርቲውን በስሩ ለማቆየት እየታገለ ያለ መሪ ደካማ  መስሎ እንዳይታይ ያለበት ፍርሐት ማንኛውንም ሥምምነት ከመፈፀም ለማገድ በቂ ሊሆን ይችላል። ለ“ማቆም” መወሰኑ የሥልጣኑ ማብቂያ ሊሆን ይችላል። መሻሻል እንዳሳዩ መታየት በበጎ ጎን ሊወሰድ ይችላል። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ጥቃቅን ሥምምነቶችን ብቻ ባደረጉበት ሁኔታ ከባድ ቃላትን መጠቀም በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ላይ ጉዳት የሚያደርስ እና ለአንባቢዎች እና አድማጮች አሳሳች ሊሆን እንደሚችል ያስታውሱ።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *