ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ባወጣቸው ተደጋጋሚ ጋዜጣዊ መግለጫዎች መንግስት ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለቻቸው በአለም አቀፍ ድንጋጌዎች እና በሕገ መንግስቱ የተጣሉበትን የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ሲያሳስብ ቆይቷል። ዜጎችን ከተደጋጋሚ ጥቃቶች መጠበቅ የመንግስት ሃላፊነት በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት የዜጎችን ደህንነት ከማንኛውም ጥቃት በመጠበቅ በሕገ መንግስቱ የተጣለባቸውን ኃላፊነቶች እንዲወጡም ድርጅታችን ሲወተውት ቆይቷል። እንዲሁም  የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎቹን መንግስት ከሕግ ፊት በማቅረብ ተጠያቂነትን እንዲሰፍን በተደጋጋሚ አሳስበናል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከግጭቶች ጋር በተያያዘ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግጭቶችን ሳይባባሱ በፊት ተገቢውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርግ እና ሌሎች ሕጋዊ መፍትሄዎች እንዲወሰዱ ማሳሰባችን ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እጅግ በጣም ሰፊ እና አስከፊ በሆነ ሁኔታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ድርጅታችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መባባስ ሀገራችን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ያለችው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር ስጋት ፈጥሮበታል፡፡  በሚያዝያ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በሶስት የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፡፡ የመንግስት ሚዲያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተአማኝነት ያላቸው ሚዲያዎች በመጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጡት ዘገባ ከአሶሳ ወደ መተከል እንዲሁም ከቡሬ ወደ ነቀምቴ መስመር ሲጓዙ በነበሩ ተሸከርካሪዎች ላይ በታጠቂዎች በተከፈተ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።  በሁለቱም ስፍራዎች በደረሱት ጥቃቶች  ከ 20  በላይ ሰዎች ህይወት እንዳለፈ እና እንዲሁም በበርካቶች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመተከሉ በተፈጸመ ጥቃት የፀጥታ ሀይሎችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም ተሽከርካሪዎች ላይ በሚደርስ ጥቃት ሳቢያ የብዙዎች ህይወት በተደጋጋሚ መጥፋት እና ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት አደጋ ላይ መውደቅ ድርጅታችንን በጥልቅ ያሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ ቀን (ሚያዝያ 22 ቀን 2013 ዓ.ም) በቤንቺ ሸኮ ዞን ዳንቹ ቀበሌ ስድስት ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ቤት ውስጥ እያሉ መቃጠላቸውን እና መገደላቸውን የወረዳው አስተዳዳሪዎች ገልፀዋል፡፡ በሌላ ኩነት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ በንፁሃን ላይ በደረሰ ጥቃት የአማራ ብሄር ተወላጅ የሆኑ 20 ሰዎች መገደላቸውን የመገኛኛ ብዙሃን የክልሉ ቃል አቀባይ የሆኑንት አቶ ጌታቸው ባልቻን ጠቅሰው ዘግበዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች እና ግለሰቦች ለጥቃት ከመጋለጣቸው በፊት ቅድመ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ እንደነበርም አብሮ በመገናኛ ብዙሃኑ ተገልጿል፡፡

ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘም አማራ ክልል ዋግህምራ አካባቢ ታጣቂዎች በንፁኃን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት አድርሰዋል፡፡ ሚያዚያ 17 ቀን 2013 ታጣቂ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት የ11 ንፁሃን ዜጎች እና የፀጥታ  አካላት ህይወት ማለፉን አረጋግጠናል።  በተመሳሳይም በአካባቢው ከወር በፊት ንፁኃን መገደላቸውን እና ንብረት መውደሙን በዶይቸ ቬሌ እና በሀገር ውስጥ ሚድያዎች በቀን 19/2013 ተዘግቧል፡፡ ለዚህም በወረዳ አስተዳዳሪዎች እና በነዋሪዎች እንደምክንያት የተነሳው ቸልተኝነት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን ማባሪያ ያጣው እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ እና በተባባሰ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ከመጣሉም በላይ አገራችን ልታካሂድ በዝግጅት ላይ ያለችውን 6ኛ አገር አቀፍ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዳይካሄድ እንቅፋት ይሆናል የሚል ስጋት አለው፡፡

በተጨማሪም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተከትሎ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በጊዚያዊ መጠለያዎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የእነዚህ ዜጎች ጉዳይ አፋጣኝ እና ዘላቂ መፍትሄ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በኩል አለማግኘቱ መጪው ጊዜ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለአስከፊ ችግር የሚያጋልጣቸው በመሆኑ ድርጅታችንን የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግስት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሰብአዊ እርዳታ የሚያቀርቡ አካላት ከወዲሁ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ድርጅታችን ያሳስባል፡፡

ሌላው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ በፖለቲካ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች እና አመራሮች ላይ የሚደርሰው ጥቃት፤ በተለይም ግድያ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ ሁለቱም ድርጅቶች እያንዳንዳቸው ሁለት እጩ ተመራጮቻቸው እና አመራሮቻቸው ተገድለውባቸዋል፡፡ ይህ አይነቱ በተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት እና አመራሮች ላይ የሚፈጽም ጥቃት የፖለቲካ ምህዳሩን ከማጥበብ ባለፈ በምርጫው ጠቅላላ ሂደትም ላይ ጥቁር ጥላ ሲለሚጥል መንግስት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ተገቢውን ጥበቃ እና ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። .

በአጠቃላይ ድርጅታችን ሀገራችን በዚህ ወቅት የገጠማትን ፈታኝ ሁኔታ፤ በተለይም ከውጭ አካላት የሚደርስባት ጫና እና ከውስጥ ባሉ ታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በመንግስት ላይ ሊያሳርፉ የሚችሉትን ከፍተኛ ጫናዎች  በቅጡ የሚረዳ ቢሆንም መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ መብት የማስከበር ግደታውን ቅድሚያ ሰጥቶ በሕግ የተጣሉበትን ኃላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጣ ማሳሰብ ይወዳል፡፡ በተጨማሪም ሀገራችን አሁን ያለችበት የሰብአዊ መብቶች ቀውስ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት በመንግስት እርምጃዎች ብቻ ሊቀረፍ ስለማይችል  የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የኃይማኖት ተቋማት እና ህዝቡም በአጠቃላይ ለግጭቶች መንስዔ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲመክር እና መንግስት ሕግን ለማስከበር በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ድርጅታችን ጥሪ ያቀርባል።፡፡

ስለሆነም ድርጅታችን መንግስት የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወስድ ጥሪውን ያቀርባል፡-

  •  በንፁኃን ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያስቆም እና ሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብታቸውን እንዲያስከብር፤
  • ክረምቱ ሳይገባ ተፈናቅልው የሚገኙ ዜጎችን በሚመለከት አስፈላጊ ዝግጅቶችን እና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ከወዲሁ እንዲወስድ እና በቂም እርዳታ ለተፈናቃዮቹ እንዲያደርግ፤ ወይም ሁኔታዎችን እንዲያመቻች፤
  • ተደጋጋሚ ችግር በሚነሳባቸው አካባቢዎች ላይ ህዝባዊ ምክክር እና ውይይት፤  መንግስት የቅድመ ማስጠንቀቂያ መንገዶችን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንዲፈጥር  እና  አደጋዎችን እና ግጭቶችን ቀድሞ ማስቆም ወይም መቆጣጠር የሚቻልባቸውን ዘዴዎች እንዲፈጥር፤
  • የዜጎችን መብት በመጣስ የንጹሃን ሰዎችን ሕይወት እና ንብረት አደጋ ላይ የሚጥሉ ግለሰቦችን እና የተደራጁ ሕገ ወጥ ቡድኖችን  በፍጥነት ለፍርድ በማቅረብ ተጠያቂ እንዲያደርግ ፤ ተጎጅዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ እንዲሰራ ድርጅታችን ለማሳሰብ ይወዳል፡፡
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *