የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት በተመለከተ የሚከተለውን ፖሊሲ በመቃወም ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሄደ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ግጭት እንዲቆም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር። እሁድ እለት በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ሰዎች አሜሪካንን የሚተቹ መፈክሮችን ይዘው የነበረ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንንና የቻይናውን መሪ ዢ ጂንፒንግ ሲያደንቁ ነበር።
በትግራይ ክልል ሰባት ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት ሳቢያ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫናዎች ሲደረጉበት ቆይቷል። በግጭቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች እንደተገደሉ ሲነገር ቢያንስ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የነበረው የህወሓት ኃይሎች በፌደራሉ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር ግጭቱ የተቀሰቀሰው።
ከሦስት ሳምንታት በኋላ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራሉ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ ጦርነቱ ማብቃቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማወጃቸው ይታወሳል። ነገር ግን ከስድስት ወራት በኋላ አሁንም የኢትዮጵያ ሠራዊትና የጎረቤት አገር ኤርትራ ወታደሮች አሁንም የህወሓት ኃይሎችን ትግራይ ውስጥ እየተዋጉ ነው።
በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች በሙሉ የጅምላ ግድያንና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በመፈጸም በሰብአዊ መብት ቡድኖች ይከሰሳሉ።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በግጭቱ ውስጥ እየተፈጸመ ነው ያሉት “ጾታዊ ጥቃትን” ጨምሮ “ሠፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች” እንዲቆሙ ጠይቀው፤ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ፕሬዝደንቱ ጨምረውም “በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየከፋ የመጣው ክልላዊና ብሔርን መሰረት ያደረገ ከፍፍል” በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ እገዳ ከመጣሉ በተጨማሪ ለአገሪቱ በሚሰጠው የደኅንነትና የምጣኔ ሀብት ድጋፍ ላይ እቀባዎችን መጣሉ ይታወሳል። በዚህ እርምጃም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቃወሞውን የገለጸ ሲሆን፤ ውሳኔውን “አሳዛኝ” በማለት ይህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት “በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳው ይችላል” ብሏል።
የጆ ባይደን አስተዳደር በተጨማሪ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆነውና ከኢትዮጵያ ግዛት እንደሚወጣ የተነገረለት የኤርትራ ሠራዊት በአስቸኳይ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።
በሰልፉ ላይ ምን ተባለ?
በአዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ የተካሄደውን ይህንን የተቃውሞ ሰልፍ በወጣቶች ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ደጋፊዎች ተሳትፈውበታል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ንግግር ካደረጉ ታዳሚዎች መካከል አንዷ ነበሩ ።
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ “ፈጽሞ አንንበረከክም። በአሜሪካና በአጋሮቿ የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎችና የጉዞ እቀባዎች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የላቸውም። ሊስተካከሉ ይገባል” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የሰልፉ ተሳታፊዎች በአማርኛ፣ በእንሊዝኛ እና በአረብኛ የተጻፉ መፈክሮችን ይዘው ነበር።
ከእነዚህም መካከል “ኢትዮጵያ ሞግዚት አያስፈልጋትም”፣ “አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን አቋም እንድታጤነው እንጠይቃለን” እና “ለውጭ ጫና ፈጽሞ አንንበረከክም” የሚሉ ይገኙባቸዋል። አገሪቱ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የምታካሂደውን ምርጫ በመደገፍም “መሪዎቻችን የምንመርጠው እኛ ነን” የሚል መፈክርም የያዙ ነበሩ።
አዲስ አበባ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲንናና የቻይናው መሪ ዢ በሰልፉ ላይ የተሞገሱት ኢትዮጵያ ሌሎች ኃያላን ወዳጆች እንዳሏት ለአሜሪካ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። የአሜሪካንን እርምጃ በመቃወም ከአዲስ አበባው በተጨማሪ ድሬዳዋን፣ ሐረርንና ጋምቤላን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች መካሄዳቸው ተዘግቧል።
ምንጭ – ቢቢሲ