የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ትናንት ሰኞ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ዙሪያ መወያየታቸውን ከሁለቱም ወገን የወጣ መግለጫ አመለከተ።
ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ ስለገባችበት ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንስተው መወያየታቸውን ከፕሬዝዳንት ባይደን ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አመልክቷል። ፕሬዝዳንት ባይደንና አልሲሲ ከሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት ጋዛ ውስጥ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማስቆም በግብጽ አሸማጋይነት ስለተደረሰው ተኩስ አቁምም ተወያይተዋል።
ከዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በስልክ በተደረገው ውይይት ላይ “ፕሬዝዳንት ባይደን የአባይን ውሃ በተመለከተ ግብጽ ያላትን ስጋት እንደሚረዱ ገልጸዋል” ብሏል። ጨምሮም ፕሬዝዳንት ባይደን በጉዳዩ ዙሪያ “የግብጽን፣ የሱዳንንና የኢትዮጵያን ሕጋዊ ፍላጎቶችን የሚያሟላ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲገኝ የአሜሪካ ፍላጎት መሆኑን እንደገለጹ” ጠቅሷል።
ሮይተርስ በሁለቱ መሪዎች መካከል ስለተደረገው ውይይት የግብጽ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባይደንን አልሲሲ “የሁሉንም ወገኖች የውሃና የልማት መብቶችን የሚያስከብር ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚያስችል የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማድግ ተስማምተዋል” ብሏል።
አሜሪካ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንስቶ በከፍተኛ ባለስልጣናቶቿ አማካይነት በኢትዮጵያ፣ በግበጽና በሱዳን መካከል በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት ለማሸማገል ጥረት ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት በተከታታይ ዋሽንግተን ውስጥ በአሜሪካ አሸማጋይነት የተደረገው ድርድር ወደ መቋጫው ደርሶ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ “ጥቅሜን የሚያስከብር አይደለም” ስትል የቀረበውን የስምምነት ሐሳብ ሳትቀበለው በመቅረቷ ሳይሳካ ቀርቷል።
ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር አውጥታ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ 20 በመቶ ያህል የቀረው ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሁሉ ቀዳሚው ይሆናል ተብሏል። ግድቡ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ሲጀምር ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው።
ግብጽና ሱዳን የግድቡን ውሃ ሙሌት በተመለከተ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ የውሃ መሙላት ሥራው እንዳይከናወን በተደጋጋሚ ቢወተውቱም ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ ተደረሰም አልተደረሰ ሥራዋን እንደምትቀጥል በይፋ ማሳወቋ ይታወሳል።
በዚህም ባለፈው ዓመት የግድቡብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ያከናወነች ሲሆን ሁለተኛውን ዙር ደግሞ በመጪው ክረምት እንደሚከናወን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል። ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግድቡ የግንባታ ሥራ መከናወኑ የተነገረ ሲሆን በመጪው ዓመትም በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሏል።