ጋዜጠኞች ለሰላም ማስከበር፣ ለሰላም  ግንባታ እና ሰላም  መፍጠር እንዴት ሊያግዙ እንደሚችሉ ፥ ክፍል 3

 

2.6 ግጭትን መተንተን

ጋዜጠኞች ግጭት ውስጥ የገቡ አካላትን ግጭቱን በጥንቃቄ በመተንተን ማለትም ግጭቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች መመልከት እንዲችሉ እና የተለያዩ ሰዎች ላይ እንዴት ተፅዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል በማሳየት መርዳት ይችላሉ። በጋዜጠኞች በኩል ምን እየተከሰተ እንዳለ ብቻ የመዘገብ አዝማሚያ አለ። ይህ አዝማሚያ አንባቢዎችን፣ አድማጮችን እና ተመልካቾችን በትክክል ምን እየተካሔደ እንዳለ እንዲረዱ አያስችላቸውም። ጋዜጠኞች የግጭት ዘገባ በሚሠሩበት ወቅት ምን እየተከናወነ እንዳለ በመተንተን ሰዎች ምን ተከሰተ? እና ለምን ተከሰተ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ከትንታኔው እንዲገነዘቡ ማስቻል አለብን። እኛ እንዲሁ በክስተቶች ላይ ዘገባ ከመሥራት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈጠረ እና እያደገ መሔዱን እንደ ግጭት ሪፖርት ማለፍ ያስፈልገናል። ክሪስ ቺናካ አፅንዖት ሰጥቶ እንደሚናገረው፣ እኛ እንዲሁ በክስተቶች ላይ ብቻ ሪፖርት ከማድረግ ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነና እየተሸሻለ የሚሔድ የግጭት ዘገባ ልንሠራ ይገባል።

ከክስተቶች ባሻገር ስንል ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሸ መስጠት ማለት ነው።

  • በግጭቱ ተሳታፊ አካላት እነማን ናቸው? በግጭቱ በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑትን እና ሌሎች በግጭቱ ላይ ፍላጎት ያላቸውን ባለድርሻ አካላት ከግምት ውስጥ አስገቡ። ግጭቱ ቢቀጥል ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስበው ማነው?
  • ግጭቱን ያስከተሉ ምክንያቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
  • እስካሁን ያለው የግጭቱ ዕድገት ምን ይመስላል?
  • በግጭት ተሳታፊ በሆኑ አካላት እና አንዳንድ ፍላጎቶች ባሏቸው ባለድርሻ አካላት ላይ ምን ተፅዕኖ አሳድሯል?
  • ለግጭቱ መባባስ፣ መርገብ ወይም መሻሻል እንዲኖር አስተዋፅዖ ያደረጉት የትኞቹ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ?
  • ይህን ግጭት ለመፍታት ምን ሊያስፈልግ ይችላል?

ትንታኔያችንን እንደ እውነተኛ መረጃ ማቅረብ አንዳንድ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል እንደ አምድ፣ ርዕሰ አንቀፅ ወይም አስተያየት በማረግ ማቅረብ እንችላለን። ሆኖም፣ ይህንን ዓይነት ትንተና የማድረግ ዋና ዓላማው የትኞቹን ምንጮች ማናገር እንዳለብን እና ምን ዓይነት ጥያቄዎች መጠየቅ እንዳለብን ለመረዳት ነው። እንዲሁም እኛ ባዳበርነው አስተያየት ላይ ትንታኔዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ወይም  አስተያየት እንዲሰጡ ባለሙያዎችን እና ተንታኞችን ማነጋገር እንችላለን።

እዚህ ጋር ቁልፉ ቃል ምርምር የሚለው ነው። ጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ጽፈው ወሳኝ የሆኑ መላምቶችን የሚያሳልፉባቸው ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ጋዜጠኞች ሌሎች ሰዎች ጽሑፋቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩባቸው አይፈልጉም ሆኖም ግጭቶች ላይ የተለየ ዕይታ ያላቸው ሰዎችን መጠየቅ የራሱ የሆነ ዋጋ አለው። ትንታኔው ወይም ርዕሰ አንቀፁ ስለ ግጭቱ እና ምን መደረግ አለበት የሚለው ላይ ትክክለኛ ሁኔታውን ለማሳየት ያግዘዋል።

የግጭት ትንተና ለማዳበር ዋነኛው ነገር ወደ ‘እውነት’ ደርሰናል ብለን ፈፅሞ አለማሰብ ነው። ያደረግነው ነገር ቢኖር መላ ምት ማስቀመጥ ነው። ይህ መላ ምት ሊሞከር የሚችል ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ማሻሻል እንችላለን። ምንም እንኳን ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በትንተናው ባይስማሙም፣ ስለ ግጭቱ በማሰብ ግጭቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት እንዲችሉ፣ ጠቃሚ እና አዳዲስ ሐሳቦችን እንዲያዳብሩ ሊረዳቸው ይችላል። በብዙ አጋጣሚዎች፣ አንድ ጋዜጠኛ ሊያደርገው የሚችለው የተሻለው ነገር ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው። ካለፈው ክፍል፣ ግጭቶች እንዴት ሊባባሱ እንደሚችሉ የተወሰነ ግንዛቤ ይዘናል። ይህም ለሰዎች ግጭቱ እንዴት እያደገ እንደሆነ የሚያሳዩ ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ ያስችለናል። እንዲሁም ግጭትን ለመፍታት የሚመረጡ የተወሰኑ አቀራረቦች ድክመት እንዳለባቸው ተረድተን ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ግጭትን ለመፍታት የመረጡትን መንገድ በተመለከተ ጥያቄ እንድናነሳ ይረዳናል።

2.7 የተሸሸጉ የጥቅም ጉዳዮችን ለመለየት መርዳት

በአብዛኛዎቹ ግጭቶች ውስጥ ግጭት ውስጥ የገቡት ወገኖች አቋማቸውን በይፋ ለማሳየት ይፈልጋሉ። ነገር ግን በእነዚህን አቋሞች ሥር የተሸሸጉ ፍላጎቶቻቸውን ለመግለጽ ፈቃደኛ አይሆኑም። በአጠቃላይ ይህ ማለት ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች አንዳቸው የሌላቸውን የተሸሸጉ ምክንያቶች ሳያውቁ ከአቋማቸውን ለማስለቀቅ በመሞከር የገመድ ጉተታ ውድድር ውስጥ ናቸው ማለት ነው። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች አንዳቸው የሌላኛቸውን ፍላጎት ማወቅ ከቻሉ፥ አንዳቸውም ከሌላው ጋር የሚጣጣሙበት ወይም የሚሥማሙባቸው መንገዶች ይኖሩ እንደሆነ ለመገምገም ይችላሉ። ጀምስ ምፋንዴ እንደሚለው “የሁሉም ቡድን ፍላጎቶች እና ጥቅሞች የሚስተናገዱበት እና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መፍትሔ ግጭትን ማስቆም የሚቻል መሆኑን ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች እንዲገነዘቡ ያስፈልጋል።”መረጃ ሰጭ እና አውጣጭ ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ጋዜጠኞች እነዚህን ፍላጎቶች በማብራራት ረገድ ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ይህንን ለማድረግ መሪዎችን እንዲሁም የተለያዩ ቡድኖችን ተራ አባላት ቃለ መጠይቅ ማድረግ ይቻላል። በክፍል ሦስት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ አንዳንድ ስልቶችን እናዳብራለን።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *