በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በወራት ጊዜ ውስጥ የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስጠነቀቀ።
የዩናይትድ ኪንግደም ረሃብ የመከላከል ልዩ መልዕከተኛ የሆኑት ኒክ ዳየር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው በግጭት በተጎዳው የትግራይ ክልል ካደረጉት ጉብኝትና ግምገማ በመነሳት ነው ስጋታቸውን የገለጹት።
አሳሳቢ ግድያዎችና አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችን የሚያመለክቱ ሪፖርቶችን በመጥቀስ ያለው ሁኔታ “አደገኛ” ነው ሲሉ ልዩ መልዕክተኛው ገልጸዋል። ኒክ ዳየር ጨምረውም የግብርና መገልገያዎች፣ የሰብል ዘር እንዲሁም መንደሮች መውደማቸውን በመግለጽ ያለውን ችግር አመልክተዋል።
በተዘጉ መንገዶችና በውጊያዎች ምክንያት በክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ሕዝብ ለመድረስ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በተጨማሪም ከጥቂቶች በስተቀር በክልሉ ውስጥ በርካታ የጤና ማዕከላት መውደማቸው አሳሳቢው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጤና ችግር እንደ ረሃብ አደጋው ሁሉ ከፍ ያለ ስጋትን ይደቅናል ብለዋል።
ኒክ ዳየር ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ውስጥ ባደረጉት ጉብኝት ከአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ መወያታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በዚህም ወቅት ሚኒስትሩ በክልሉ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እየተደረገ ስለሚገኘው ድጋፍን ጨምሮ በክልሉ ስላለው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራዎች ማብራሪያ እንደሰጡ ተገልጿል።
በተጨማሪም በክልሉ ተፈጽመዋል ስለተባሉት የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ከተለያዩ መንግሥታዊና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር በመሆን ምርመራ ለመጀመር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከስድስት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ በሰውና በመሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ሲነገር የቆየ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነዋሪ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚፈልግ የረድኤት ድርጅቶች ገልጸዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ