ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን የምትቀጥል ከሆነ መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት መለስ ብሎ ለማጤን እንደሚገደድ አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ እገዳ መጣሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ነው ይህንን ያለው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ መፍትሔ እንዲያገኝ የተደረጉት ጥረቶች ውጤት ባለማስገኘታቸው በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በአማራ ክልል ባለስልጣናትና በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕገዳ መጣሉን እሁድ ሌሊት ማሳወቁ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ መንግሥት በዚህ እርምጃው “በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫናን ማድረግ መቀጠሉን” በመጥቀስ ተቃውሞውን አሰምቷል።

ይህ ውሳኔ የተሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ገንቢ የሆነ ግንኙነት እያደረገ ባለበት ጊዜ መሆኑን ጠቅሶ፤ አገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀት ባለችበት በዚህ ወቅት መሆኑ ደግሞ የተሳሳተ መልዕክትን የሚያስተላለፍ ነው ብሎታል። ጨምሮም አሜሪካ የጣለችው የቪዛ ዕቀባና ቀደም ሲል የወሰደቻቸው ሌሎች ተያያዥ እርምጃዎች የሁለቱ አገራትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳዋል ብሏል።

ይህ የአሜሪካ የጉዞ ዕቀባ ውሳኔ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ እንዲፈጠር ያደረጉ ወይም የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ እንዳይሳካ ያደናቀፉ የአገራቱን የደኅንነት ኃይል አባላትን ወይም የአማራ ክልልና ኢመደበኛ ኃይሎችንና ሌሎች ግለሰቦች እንዲሁም የህወሓት አባላትን የሚያካትን መሆኑ ተገልጿል።

ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ግጭት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መግለጫ ከዚህ አንጻር ከሁሉ የከፋ ብሎ የጠቀሰው የአሜሪካ መንግሥት ከሁለት ሳምንታት በፊት በአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተሰየመውን ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በእኩል የመመልከት ዝንባሌ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ ውይይት የሚያደርገው ከውጭ በሚደረግበት ግፊት ሳይሆን የአገሪቱን የወደፊት ተስፋ በተሻለ መንገድ ላይ ለመምራት ብሔራዊ መግባባት ትክክለኛው መንገድ ነው ብሎ ስለሚያም እንደሆነ ገልጿል።

ነገር ግን “ሽብርተኛ ተብሎ ከተሰየመው ህወሓት ጋር ድርድር ማድረግ እንደማይቻል ከግንዛቤ ሊገባ ይገባል” በማለት ቡድኑ መልሶ እንዲያንሰራራ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ አሉታዊ ውጤት የሚኖረውና የማይሳካ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል።

ጨምሮም “የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ግልጽ እንዳደረገው፤ የአሜሪካ አስተዳደር በውስጣዊ ጉዳዩ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርገው ሙከራ ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው” ብሏል።

ትግራይ ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግሥት አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ በሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም በአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራት በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

የሰብአዊ እርዳታን በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ባልተገደበ ሁኔታ እርዳታ እንዲቀርብ ከማድረጉ በላይ መንግሥት ያለውን ውስን አቅም በመጠቀም እርዳታ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጿል።

የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ መፍትሔ እንዲገኝ በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በኩል ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ልዩ መልዕከተኞች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

አሜሪካ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳይን በቅርበት እንዲከታተሉላት አንጋፋውን ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማንን በልዩ መልዕክተኝነት ሰይማ ከሳምንታት በፊት በአካባቢው ጉብኝት አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንትም የአገሪቱ ሴኔት በትግራይ ግጭት ላይ ተሳታፊ በሆኑ ወገኖች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰድ የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ አሳልፎ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥትም በተደጋጋሚ በውስጥ ጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ተጽእኖ ለመሳደር የሚሞክሩ መንግሥታትን ጫና እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ እና ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የሚያደርጉትን ጥረት የሚቃወም ንቅናቄ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዶ ነበር።

በትግራይ ክልል ውስጥ ከስድስት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ግጭት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ እስካሁን የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሃዙ በሺዎች የሚቆጠር ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በተጀመረው ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ኃይሎች በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ሲከሰሱ ቆይተዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *