በአዲስ አበባ “ብሔራዊ ክብር በሕብር” በሚል በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ኢትዮጵያውያን በያሉበት ድምጻቸውን አሰሙ።

በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” ፣ “ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የአገርን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው”፣ “ግድቡ የኔ ነው” የሚሉና መሰል መልዕክቶች በመኪናዎች ላይ በመለጠፍና በእጃቸው በመያዝ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

ከአስተባባሪዎቹ አንዷ የሆኑት ክብሬ ተስፋዬ ድምጽ የማሰማቱ መርሃ ግብር ዓላማ በቀጥታ ጣልቃ ገብነትን የሚመለከቱ መግለጫዎችን ለሚያወጡ አካላት ‘እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ’ ለመጠየቅ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“የሕዳሴ ግድብ፣ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ምርጫን ተከትሎ የውጭ ተጽዕኖ ኢትዮጵያ ላይ እየበረታ ነው” ያሉት አስተባባሪዋ፤ የውጭ አካላት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ለመጠየቅ መርሃ ግብሩ መካሄዱን ተናግረዋል።

“‘ለኢትዮጵያ እናውቅላታለን’ የሚል የውጭ ኃይል ሲመጣ፤ እኛ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ እናውቀዋለን፤ ስለዚህ እጃችሁን አንሱልን ነው ያልነው” ብለዋል አስተባባሪዋ። የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ማለት ምን ያስቆጣል ተብለው የተጠየቁት አስተባባሪዋ፤ ተቃውሟቸው ‘ለእናንተ እኛ እናውቅላችኋለን’ ብለው ውሳኔና መፍትሔ ካልፈለግን ለሚሉት እንደሆነ ተናግረዋል።

“የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም መንግሥትም ያመናቸው እንዳሉና እኛም እያለቀስንበት ያለ ጉዳይ ነው” በማለት “የውስጥ ጉዳይን መፍታት ያለብን እኛው ነን” ብለዋል። አስተባባሪዋ አክለውም ዛሬ በነበረው የመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት “በቀጥታ ጣልቃ ገብነትን የሚመለከቱ መግለጫዎችን ለሚያወጡት እጃቸውን እንዲያነሱ፤ አብረውን ለቆሙ ለተረዱን አገራት ደግሞ የምስጋና ደብዳቤ የማስገባት እቅድ ነበረን” ብለዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ‘የጸጥታ ስጋት’ በሚል መሥሪያ ቤታቸውን በመዝጋታቸው ይህንን ማድረግ እንዳልቻሉ አስረድተዋል። ድምጽ የማሰማት መርሃ ግብሩ አዲስ አበባ በሚገኘው ከአሜሪካ ኤምባሲ ውጪ ተቃውሞ እንደሚካሄድ ቀደም ብሎ የተገለጸ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ይህ እንዳልተከናወነ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጿል።

ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሐይማኖት ተቋማት፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት የተዘጋጀ የተቃውሞ ደብዳቤ ወደ ኤምባሲዎች ለማስገባት ታቅዶ እንደነበርና ዛሬ ኤምባሲዎቹ ዝግ በመሆናቸው አለመሳካቱን ከመርሃ ግብሩ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ዐብይ ታደለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል። ኮሚቴው ኤምባሲዎቹን ቀጠሮ እንዲሰጠው መጠየቁንና ቀጠሮውን በሚሰጣቸው ጊዜ ደብዳቤውን በአካል እንደሚያቀርቡ አስተባባሪው አክለዋል።

አንዲት ህጻን ከሰልፈኞቹ መካከል

የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ባወጣው መግለጫ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በኤምባሲው አካባቢ ተቃውሞ ሊኖር እንደሚችል በመግለጽ አርብ መሥሪያ ቤቱ ዝግ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል። በትግራይ ውስጥ የህወሓት ኃይሎች በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ እንዲሁም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ምዕራባዊያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታውን ሲያሰማ ቆይቷል።

ሰልፈኞች

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ባለሥልጣናት በተለያዩ መድረኮች ላይ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ መሆናቸውን፤ ነገር ግን ይህ ተቀባይነት እንደሌለው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ይህ “ብሔራዊ ክብር በሕብር” የተሰኘው በታዋቂ ሰዎች የተዘጋጀው እንቅስቃሴም ዜጎች የውጭ አገር መንግሥታት በኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት እያደረጉ ነው ያሉትን ጥረት ለመቃወም የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

መኪኖች
ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *