የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ኬሚካል መሣሪያ ጥቅም ላይ ውሏል የሚለውን የቴሌግራፍ ዘገባ አስተባበለ።

ሚኒስቴሩ ጉዳዩን በተመለከተ ሁለት ተከታታይ መግለጫዎችን ያወጣ ሲሆን በዚህም የዩናይትድ ኪንግደም ጋዜጣ የሆነው ቴሌግራፍ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ ባለው ግጭት የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ አውለዋል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

ጋዜጣው ባወጣው ዘገባ ሠራዊቶቹ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የተከለከሉ ተቀጣጣይ የጦር መሣሪያዎችን ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ተጠቅመዋል ብሎ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ የጋዜጣው ዘገባ ከመውጣቱ በፊት ባወጣው መግለጫ ዘገባውን አገሪቱን ለመከፋፈል ያለመ “አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው” ሲል ወቅሷል።

ሚንስቴሩ በተከታይነት ባወጣው መግለጫ ላይም በጋዜጣው የቀረበውን ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ ውድቅ በማድረግ በትግራይ ክልል ንጹሀን ዜጎች በኬሚካል ጦር መሣሪያ ተቃጥለዋል የሚለውን ዘገባ አስተባብሏል። በዘገባው በትግራይ ክልል በዋይት ፎስፈረስ ቃጠሎ የደረሰባቸው ንጹሀን ዜጎች እንዳሉ ገልጾ ይህም የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል በስፋት አትቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መግለጫ ከዘገባው በተቃራኒው “ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የኬሚካል መሣሪያዎች ድንጋጌ ስለምታከብር ክልከላ የተጣለባቸውን የጦር መሣሪያዎችን አልተጠቀመችም። አትጠቀምም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። የቴሌግራፍ ዘገባ እንደሚለው፤ ንጹሀን ዜጎች በነጭ ፎስፈረስ ቃጠሎ እንደደረሰባቸው የሚጠቁም መረጃ ማግኘቱን አመልክቷል።

የአይን እማኞች እና ቃጠሎ የደረሰባቸው ዜጎችን ጠቅሶ “የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች ንጹሀን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ኃይለኛ ቃጠሎ የሚያደርሱ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይጠቁማል” ሲል ዘገባው አስንብቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ የቴሌግራፍን ክስ ውድቅ አድርጓል። “ኢትዮጵያ የኬሚካል መሣሪያ ጥቃት የደረሰባት አገር እንደመሆኗ፤ የኬሚካል ጦር መሣሪያ በማንም አካል፣ በየትኛውም አገር ጥቅም ላይ መዋሉን ትቃወማለች” ሲል መግለጫው አትቷል።

ዘ ቴሌግራፍ በድረ ገጹ ያስነበበው ዘገባ ላይ በእማኝነት ከጠቀሳቸው መካከል ቅሳነት ገብረሚካኤል የተባለች የ13 ዓመት ታዳጊ አንዷ ናት። ታዳጊዋን በስልክ እንዳነጋገሯትና ቃጠሎው ከደረሰባት በኋላ ወደ ሆስፒታል ሄዳ የተነሳችው ፎቶ፤ የእጇ፣ የእግሯ እና የፊቷ ቆዳ መቃጠሉን እንደሚያሳይ ዘገባው ይገልጻል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለዚህ ዘገባ ባወጣው መግለጫ ላይ “እንዲህ ያሉ የተሳሳቱና ኃላፊነት የጎደላቸው ዘገባዎች ውጥረት ከማባባስ ያለፈ ሚና እንደሌላቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቀናል” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። ዘገባው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየተረገ ያለው ጥረት አንድ አካል እንደሆነ የሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ ጠቅሷል።

የቴሌግራፍ ዘገባ በበኩሉ የተባበሩት መንግሥታት የጄኔቫ ስምምነትን አጣቅሶ፤ ንጹሀን ዜጎች ላይ ኬሚካል የጦር መሣሪያ መጠቀም ዓለም አቀፍ መርህን እንደሚጥስ ይጠቅሳል። በኬሚካል መሣሪያ የደረሱ ጥቃቶች ባለሙያ የሆኑ ግለሰብን እንዳነጋገረና፤ በፎቶ ላይ ያዩዋቸው ምስሎች በሰሜን ምሥራቅ እና በሰሜን ምዕራብ ሶርያ በነጭ ፎስፈረስ ከደረሰ ጥቃት ጋር እንደሚመሳሰሉ ማረጋገጣቸውን ያትታል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ግን የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ አልዋለም ሲል ዘገባውን ውድቅ አድርጓል። አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በትግራይ ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመ ይከሳሉ። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችም ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ እነዚህን ክሶች አይቀበልም። አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ ይገልጻል። በኢትዮጵያ ላይ በተለያየ መንገድ ጫና ለማሳደር የሚደረገውን ሙከራ እንደማይቀበልም መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እንዲሁም በኤርትራ ባለሥልጣኖች፣ ወታደራዊና የደኅንነት አባሎች፣ በአማራ ክልል ኃይሎች እና በህወሓት አባላት ላይ የጉዞ እቀባ መጣሉን አስታውቋል።

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *