እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲሆን ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ።
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የሆኑት ጃዋር መሐመድ እና ሌሎችም በፀረ ሽብር አዋጅ እና በሌሎችም የተከሰሱ ሲሆን ቀጠሯቸው ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲያዝ ቢጠይቁም ፍርድ ቤት ጥያቄቸውን ውድቅ አድርጓል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእነ ጃዋርን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር የተከሰሱት በዛሬው ዕለት ግንቦት 12፣ 2013 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል። ከተከሳሾቹ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ እነደተናገሩት የዛሬ ችሎቱ የተሰየመው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ጉዳያቸውን ለማየት ነበር።
ትናንት ረቡዕ ዕለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጀዋር መሐመድ መዝገብ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት ወይስ ከመጋረጃ ጀርባ ይካሄድ የሚለውን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በድጋሚ እንዲመረምር ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።
ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ በምስክሮች ላይ ሊደርስባቸው ይችላል ያላቸውን በቂ እና አሳማኝ አደጋዎች በዝርዝር ለከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዲያቀርብም አዝዟል። የተከሳሾች ጠበቆች ደግሞ ይህንን ውሳኔ በመቃወም አቤቱታቸውን ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤት እንደሚሉ ተናግረው ነበር።
ይሁን እንጂ በዛሬው ዕለት የዚህ ትዕዛዝ ግልባጭ ፍርድ ቤቱ ስላልደረሰው ጉዳዩን ሳያየው ቀርቷል። በዛሬው ቀጠሮ ላይም አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 20 ተከሳሾች ልደታ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ችሎት በአካል ቀርበው ነበር።
በዚሁ መሰረት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ግንቦት 18 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል። በዛሬው ዕለት ከተከሳሾች አቶ ጃዋር መሐመድ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ ችሎቱን በማስፈቀድ ለፍርድ ቤቱ ሃሳባቸውን ማቅረባቸውን ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ተናግረዋል።
እነዚህ ተከሳሾችም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የሚታይ ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔ የሚፈልግ መሆኑን በመግለጽ፣ ፍርድ ቤት በመመላለስ የተከሳሾችን፣ የሕግ ባለሙያዎችን፣ የጠቅላይ አቃቤ ሕግን እና የጠበቆችን ጊዜ ከማጥፋት ረዥም ቀጠሮ ለሁለት ዓመት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ብለዋል።
“ምርጫ አልፎ መንግሥት ከተረጋጋ በኋላ በ2015 ወይንም ደግሞ በ2016 ጉዳያችን ይታይ ሲሉ ተናግረዋል።” የኮሎኔል ገመቹ እና የሌሎችን ተከሳሾችን ጉዳይ እንደማስረጃ ያቀረቡት እነ አቶ ጃዋር፣ ይህ ፍርድ ቤት ነጻ ቢለቀን እንኳ መንግሥት አይለቀንም ሲሉ መናገራቸውን አቶ ቱሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ እለት እነ ኮሎኑል ገመቹ አያናን ፍርድ ቤት በነጻ ቢያሰናብታቸውም፣ የፌደራል ጸጥታ ኃይሎች ከማረሚያ ቤቱ በራፍ ላይ በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የሚታይ ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔ የሚፈልግ መሆኑን ሲናገሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ፖሊስ በወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ቢናገርም እነ ጃዋር ግን ምርጫ ላይ እንዳንሳተፍ ነው በቁጥጥር ስር የዋልነው ሲሉ ለችሎቱ ሲናገሩ ቆይተዋል።
እን አቶ ጃዋር መሐመድ በተከሰሱበት ወንጀል በአሁኑ ጊዜ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን እያየ ያለ ሲሆን የተጠረጠሩበትን ወንጀል አልፈጸምንም ሲሉ ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል። ከዚህ በኋላ አቃቤ ሕግ ማስረጃውን እንዲያቀርብ የታዘዘ ሲሆን ማስረጃ የሚቀርብበት አኳኋን ላይ ግን ክርክር እየተካሄደ ይገኛል።
ዛሬ ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት ጉዳይ ላይ አቃቤ ሕግ፣ የሌላን ጉዳይ መዝገብ ከዚህ መዝገብ ጋር ማያያዝ ትክክል አይደለም፤ እያደረጉት ያሉት ክርክር የፖለቲካ ክርክር ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ሊፈቅድላቸው አይገባም ሲል ተከራክሯል።
ፍርድ ቤቱም ከሁለቱም ወገን ያለውን ሃሳብ ካደመጠ በኋላ ተከሳሾች ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲሰጣቸው የጠየቁትን ቀጠሮ ውድቅ በማድረግ ለግንቦት 18 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን አቶ ቱሊ ተናግረዋል።
በ2012 ሰኔ ወር ላይ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በቁጥጥር ስር የተያዙት አቶ ጃዋር መሐመድ እና በመዝገባቸው ስር የሚገኙ ሌሎች የፀረ ሽብርን አዋጅን የቴሌኮም ወንጀል አዋጅን የጦር መሳሪያ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን እና የአገሪቷን የወንጀል ሕግ የተለያየ አንቀጽ በመተላለፍ ነው የተከሰሱት።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ከጦር መሳሪያ ቁጥጥር አዋጅ ጋር የተያያዙ ክሶች እንዲቋረጡ ማድረጉ ይታወሳል። አቶ ደጀኔ ጉተማ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ፣ ፀጋዬ ረጋሳ አራርሳ፣ በአገር ውስጥ የሌሉት እና በእነ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ስር ከተከሰሱት ውስጥ ናቸው።
ምንጭ – ቢቢሲ