ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ግንቦት 28፣ 2013 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ብሔራዊ ምርጫ፣ ከምርጫ ካርድ ምዝገባ እና ሌሎች ስራዎች በተያዘላቸው ቀናት ባለመጠነቃቀቸው የተነሳ ምርጫው ለሁለት ሳምንታት እንዲገፋ ሆኗል። ኢትዮጵያ በየአምስት አመቱ የምታካሂደው ምርጫ መካሄድ የነበረበት ባለፈው አመት ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም መደረጉ የሚታወስ ነው።
ምርጫው ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ በስተቀር ግንቦት 28 እንዲካሄድና በሁለቱ ከተሞች ደግሞ ከሳምንት በኋላ ተይዞ ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው የተለያዩ የስራ ሂደቶች ባለመጠናቀቃቸው ምርጫውን በተያዘለት ቀን ለማካሄድ እንደሚቸገር አሳውቋል።
ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልል ፅህፈት ቤቶችን ለመክፈት በተለያዩ የክልል መንግሥታት በኩል የታየው ቸልተኝነት፣ የዕጩዎች ምዝገባ መራዘም እና የምርጫ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ ችግሮች በመኖራቸው የመራጮች ምዝገባን ቀንን ማራዘሙ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው እስከ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 36 ሚሊዮን 245 ሺህ 444 ሰዎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጿል።
የምርጫ ካርድ ከወሰዱት መካከል 16.6 ሚሊዮኑ ሴቶች ሲሆኑ ፤ 19.5 ሚሊዮኑ ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት 50 ሚሊዮን ዜጎች ካርድ ሊወስዱ እንደሚችሉ ግምቱን አስታውቆ ነበር። እንደ ምርጫ ቦርድ መረጃ ከሆነ ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ከተገመተው በላይ የመራጮች ካርድ ከተወሰደባቸው መካከል ናቸው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የመራጮች ምዝገባ መከናወኑን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል። በግጭት ውስጥ ባለችው ትግራይ ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ዋነኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።
ፓርቲዎቹ በኃይል ተዘግተዋል ያሏቸው ፅህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የታሰሩ አባሎቻቸው እንዲፈቱና የፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ ብሄራዊ መግባባት ያለበት መሆን አለበት በማለት እነዚህ ባለመከናወናቸው ከምርጫው ተገፍተው እንደወጡ አስታውቀዋል።
የአገሪቱ መሪ ብልፅግና በበኩሉ ይህንን ውንጀላ አይቀበለውም። በዚህ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ “ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የማካሄድ ባህል ባለመኖሩ በዝግጅት ውሰጥ ያጋጠሙ አንዳንድ ተግዳሮቶች አሉ” ብለዋል።ሆኖም ከቀደሙት አመታት በተሻለ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉና ወደፊት ለሚካሄዱ ምርጫዎች መሰረት እንደሚሉም ተናግረዋል።