በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ ጥቃት በሚከሰትበት መተከል ዞን ያለውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት መፍትሄ ለማምጣት የክልሉ መንግሥትና ታጣቂ ቡድኑ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ዞኑ አስታውቋል።
ስምምነቱ የተፈረመው በትናንትናው ዕለት ግንቦት 10፣ 2013 ዓ.ም በግልገል በለስ ከተማ መሆኑን የመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማህበራዊ ትስስር ገፁ አስፍሯል። የአካባቢውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በታጣቂ ቡድኑ በኩል የሚነሱ እና የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች የስምምነት ሰነድ ተዘጋጅቶ መፈረሙም ተገልጿል።
በዚህ ሰነድ ከተካተቱት ዋነኛ ጉዳዮች መካከል እነዚህ ኃይሎች የኃላፊነት ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የከተማ የቤት መስሪያ ቦታ፣ የገጠር የእርሻ መሬት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገኙባቸዋል። በኃላፊነት ቦታ የሚመደቡት አቅምና የትምህርት ደረጃቸውን ባማከለ መልኩ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው በክልል ደረጃ ሁለት፣ በዞን ደረጃ ሶስት እና በወረዳ ደረጃ ደግሞ አራት ሰዎች ይቀመጣሉ ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ልምድ ያላቸው የቡድኑ አባላት በክልሉ ውስጥ ባሉ የፀጥታ መዋቅሮች መመደብ፣፣ሴቶችን አካታች ያደረገና በተለያዩ ማህበራት እንዲደራጁ ማስቻል፣በተማሩበት የሙያ መስክ እንዲመደቡ ማድረግና የብድር አገልግሎት እንዲመቻች ማድረግ የሚሉ ሃሳቦች በሰነዱ ውስጥ ተካተዋል። ታጣቂ ቡድኑ በስም ባይገለፅም የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ከሚገኙ አባላት ጋር እንደሆነ መግለጫው አስፍሯል።
በታጣቂ ቡድኑ በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት ስልጠና የሚወስዱ መሆናቸውም ተገልጿል። ክልሉን ወክለው ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሃሰን እና የታጣቂ ቡድኑ ተወካይ አቶ አጀግናማው ማንግዋ የስምምነት ሰነዱን ፈርመዋል።
ሰነዱ በክልሉ መንግሥት በኩል ያለምንም መጓተት ተፈፃሚ እንደሚሆን በስምምነት ፊርማው ዕለት የገለፁት አቶ አሻድሊ ሃሰን ለዚህም መሳካትና ስራውን በቅርበት ለመከታተል ከታጣቂ ቡድኑ ሶስት አባላትን ያካተተ ጊዜያዊ ፅህፈት ቤት በግልገል በለስ ከተማ መቋቁሙን አስታውቀዋል። የክልሉ መንግሥት አቅም በፈቀደና ህግና ስርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት ሁሉንም ተግባራዊ እንደሚያደርግ አቶ አሻድሊ መናገራቸውን መግለጫው አስፍሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ታጣቂ ቡድኑ አባላትን በተመለከተም በሰላም የገቡትን “የሰላም አምባሳደር” ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ሌሎች ወደ ሰላም ያልመጡ የታጣቂ ቡድን አባላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ የፊርማ ስነ ስርዓትም ላይ የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄነራል አለማየሁ ወልዴን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ እና የዞን አመራሮች እንዲሁም የታጣቂ ቡድኑ አባላት መገኘታቸውንም ቢቢሲ ከዞኑ ካገኘው መረጃ መረዳት ችሏል።
በመተከል ዞን በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጡ የተባሉ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ቁጥር 3 ሺህ 230 መሆኑን ዋልታ መጋቢት 7፣ 2013 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ አስነብቧል። ዘገባው የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የግብረ ሃይል አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁን ዋቢ አድርጎ እንደጠቀሰው ለነዚህ ታጣቂዎችም በአካባቢያቸው ሰላም፣ ልማትና፣ ዲሞከራሲያዊ ስርዓት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጥ አስፍሮ ነበር።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚፈጸሙ ጥቃቶች
በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚዋሰነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሦስት ዞኖች የሚገኙ ሲሆን እነሱም መተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ የሚባሉ ናቸው።በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰዎች ከሞትና ለመፈናቀል ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
ከእነዚህም መካከል ለረጅም ጊዜ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት የቆየው የመተከል ዞን በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ ይህንንም ለመቆጣጠር በሚል የክልሉና የፌደራል መንግሥት የጸጥታ አካላት በጥምረት የሚመሩት የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) በዞኑ ውስጥ ከተቋቋመ ወራት ተቆጥረዋል።
ከስድስት ወራት በፊት ታኅሣሥ 14/2013 ዓ.ም በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ኢሰመኮን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ይህንና ሌሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ በክልልና በፌደራል መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በርካታ የታጠቁ ሽፍቶች እንደተገደሉ ተገልጾ ነበር።
የክልሉ መስተዳደር ጥቃቱን የሚፈጽሙት “ጸረ ሰላም ኃይሎችና ሽፍቶች” ናቸው ከማለት ውጪ ጥቃቱን የሚፈጽመው ኃይል ምን አይነት ቡድንና አላማው ምን እንደሆነ አስካሁን በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።ነገር ግን በበርካታ አካባቢዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚገደሉና የሚፈናቀሉ ሰዎችን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ድርጊቱ የብሔር ማንነትን የለየ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለእርሻ የሚውል ሰፊ ለም መሬት ያለበት አካባቢ ሲሆን ለዓመታት የዘለቀው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽን እያወዘገበ ያለው በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግዙፉ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚገኝበት ክልል ነው።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ ወደ 1.1 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ሕዝብ ይገኛል።
ምንጭ – ቢቢሲ