የቀድሞ የምዕራብ ወለጋ ዞን ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ አምስት የመንግሥት ሠራተኞች በታጣቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።
እነዚህ አምስት ሰዎች የተገደሉት ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ከቆንዳላ ወረዳ ወደ መንዲ እየተጓዙ እንደነበረ የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለሥራ ጉዳይ በመጓዝ ላይ የነበሩትን የቀድሞው የጸጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ ዋቅጋሪ ቀጄላና ሌሎች ባልደረቦቻቸውን የገደሉት ታጣቂዎች፤ “እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብለው የሚጠሩት በቅርቡ ደግሞ መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጃቸው የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።
የአምስቱ ሰዎች የመገደል ዜና የተሰማው ከአንድ ሳምንት በፊት አባ ቶርቤ በተባለ ቡድን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ መገደልን ተከለትሎ የቡድኑ አባል ነው የተባለ ወጣት በመንግሥት የጸጥታ ኃይል በአደባባይ ከተገደለ በኋላ ነው።
አቶ ኤልያስ እንዳሉት ቅዳሜ ዕለት በታጣቂዎች የተገደሉት አምስቱ ሰዎች በሁለት መኪና ሆነው እየተጓዙ ሳሉ ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው።
ከዞን አመራር በተጨማሪ አንድ አሽከርካሪ እና ጥበቃ ለማድረግ ከዞን አመራሩ ጋር አብረው ሲጓዙ የነበሩ ሁለት የሚሊሻ አባላት እና አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል መገደላቸውን ተነግሯል።
ከሟቾቹ መካከል የቀድሞው የዞን አመራር የቀብር ሥርዓት ትናንት መፈጸሙን የተገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው አለመኖሩን የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
አምስቱ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት የተፈጸመው ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚዋሰኑበት ስፍራ መሆኑን አቶ ኤልያስ አመልክተው፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ በአካባቢው የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ፍተሻ እያደረጉ ነው ብለዋል።
አቶ ዋቅጋሪ ማን ናቸው?
አቶ ዋቅጋሪ ቀደም ሲል የምዕራብ ወለጋ ዞን የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። ከዚህ በፊትም የወረዳ አስተዳዳሪ እንዲሁም የከተማ ከንቱባ በመሆኑን ሰርተዋል።
ከአንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ የዞን የመንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ በመሆን ሲስሩ እንደነበረ አቶ ኤልያስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአራት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ዋቅጋሪ “ታታሪ፣ ጠንካራ ሠራተኛ እና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የነበራቸው ሰው እንደነበሩ” ሲሉ አቶ ኤልያስ ያስታውሳሉ።
አቶ ዋቅጋሪ የሁለት ዲግሪ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለምረቃ ተቃርበው እንደነበረ ተነግሯል።
በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በአካባቢው ካሉ የመንግሥት ባለስልጣናትና የጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ለእነዚህ ጥቃቶችም ለረጅም ዓመታት በትጥቅ ትግል ላይ ከነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣውና እራሱን ‘የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት’ የሚለው መንግሥት ደግሞ ‘ሸኔ’ የተባለው ቡድን ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡድኑን የሽብር ቡድን አድርጎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መሰየሙ ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 18 የመንግሥት ባለስልጣናት፣ 112 የፖሊስ አባላት እና 42 ሚሊሻዎች መገደላቸውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።