ጋዜጠኞች ለሰላም ማስከበር፣ ለሰላም  ግንባታ እና ሰላም  መፍጠር እንዴት ሊያግዙ እንደሚችሉ ፥ ክፍል 3

 

2.4 የተለያዩ ወገኖች እርስ በርስ እንዲተማመኑ  ማስቻል

ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት መካከል አለመተማመን ለቀጣይ ግጭት የሚዳርግ ዋነኛው ምክንያት ሲሆን ብዙኃን መገናኛዎች በግጭት ተሳታፊ አካላት መካከል መተማመንም እና አለመተማመንን ሊፈጥሩ ይችላሉ። አስተያየቶችን ከሐሳቡ አውድ ውጭ በማንሳት እና በጣም ቀስቃሽ የሆኑ መግለጫዎችን ሆን ብለን ነቅሰን በማውጣት እንዲሁም ሚዛናዊ የሆኑ አመራሮችን ትተን ተንኳሽ ንግግሮችን የሚያደርጉ አመራሮችን በማነጋገር ብቻ መተማመንን ልናጠፋ እንችላለን።

መተማመንን የመገንባት ሒደትን ለመደገፍ ጋዜጠኞች ግጭቶችን በጣም በቅርብ እንዲከታተሉ ያስፈልጋል። እንዲሁም ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ትናንሽ ሙከራዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ እነዚህን ታሪኮች በሚገባ መዘገብ ይኖርብናል። ብዙ ግጭቶች የሚፈቱት ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት እርስ በርሳቸው ለመተማመን ደረጃ በደረጃ በሚወስዷቸው እርምጃዎች ነው። ቡድኖቹ በተከታታይ ትንንሽ ሥምምነቶች መተማመንን ሲገነቡ፥ ትልልቅ ጉዳዮችንም መፍታት ይጀምራሉ።

ያስታውሱ:

በርካታ ተደራሾች ጋር ደረስን ማለት በመሪዎች መካከል መተማመን ስለ መገንባት ብቻ ሳይሆን በቡድኖች መካከልም መተማመንን ለመገንባት እየረዳን ነው ማለት ነው። ቡድኖች መሻሻል እንዳለ ከተገነዘቡ በመካከላቸው የሚኖር ውጥረት እና ነውጥ የመነሳቱ ዕድል ይቀንሳል።

በተጨማሪም ስለ ሰላም ሒደቶች ዘገባ በመሥራት እና የሰላም ሥምምነቶች ስለሚያስከትሏቸው ተፅዕኖዎች ሰዎችን በማስተማር መተማመንን ማስፈን እንችላለን። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የደረሱባቸው ስምምነቶች የኽዝብ ተቀባይነት እንዳገኙ ሲገነዘቡ ሥምምነቶቹን የመተግበር ዕድላቸው ሰፊ ነው። የገቡትን ቃል የሚጥሱ ሆነው ከታዩ ማኅበረሰቡ በመጥፎ ዓይን አንደሚመለከታቸው ይገነዘባሉ።

ጋዜጠኞች በግጭት ወቅት ነውጥ እና ተምኔታዊ ክስተቶችን የመጠበቅ ዝንባሌ ያሳያሉ። ክስተቶቹ ተምኔታዊ ናቸው ማለት በጣም አስፈላጊ ናቸው ማለት አይደለም። ብጥብጥ ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሌላ ማኅበረሰብ ነውጥን የሚቆጣጠርበት መንገድ የማግኘቱ ዘገባ እየተከሰተ ካለው ረብሻ እኩል አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ዜና የብዙ ሰዎች ሕይወትን ሲነካ ብቻ አስፈላጊ እንደሚሆን የማሰብ ዝንባሌ አለን። የግጭቶች መቆም በማኅበረሰብ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚያሳድር ክስተት ቢሆንም በሚዲያዎች ዘንድ ከነውጥ ታሪኮች እኩል ክብደት አይሰጣቸውም።

በግጭት ተሳታፊ ወገኖች መተማመንን እንዲያዳብሩ መርዳት ማለት ለነገሮች ከልክ በላይ እናራግ ባለን ማለት እንዳልሆነ ልብ ልንል ይገባል። ሰዎች ለመነጋገር ተሥማምተዋል ማለት የሰላም ሥምምት ላይ ተደርሷል ማለት አይደለም። መልካም የሆነን ነገር ማጋነን፣ መጥፎ ነገርን ከማጋነን እኩል ጉዳት አለው።

2.5 የተዛቡ ግንዛቤዎችን መቀልበስ

በግጭት መባባስ ላይ ባደረግነው ውይይት እንደተመለከትነው የተሳሳቱ አመለካከቶች ግጭት እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ አይተናል። ጋዜጠኞች ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የሚኖራቸውን የተሳሳቱ አመለካከቶች የመለየት ብቃት ይኖረናል። ምክንያቱም በየጊዜው የተለያዩ ወገኖችን በማነጋገር ስለሁኔታዎች እና አንዳቸው ስለሌላቸው ያላቸውን አስተሳሰብ ማወቅ ስለሚጠበቅብን ነው። ጋዜጠኞች ሰዎች ያላቸውን የተዛባ አረዳድ የሚገልጹበት ዕድል በመስጠት ሌላኞቹ ቡድኖች ደግሞ ጉዳዩን በመገናኛ ብዙኃን ግልጽ ለማድረግ የሚሞክሩበት ዕድል ያመቻቻሉ።

ይህ ማለት ቡድኖች አንዳቸው ስለሌላቸው የሚናገሩትን ለመስማት ጊዜ መውሰድ ማለት ነው። ይህም አንዳቸው ስለሌላቸው ባሕል የሚገልጹበትን ሁኔታ እና አንዳቸው ስለሌላቸው ዓላማ ያላቸውን አመለካከት መገልጽን ያካትታል። ጋዜጠኞች የተሳታፊዎቹን የተዘቡ አረዳዶች እንደ ታሪክ ወስደው ዘገባ መሥራት ይችላሉ። በዚህም ግጭት ውስጥ የገቡት ወገኖች አመለካከታቸውን መለስ ብለው እንዲያዩ በማበረታታት በሒደት ግጭቱን ለመከላከል ወይም መፍትሔ ለመስጠት እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል። ይህንን በማድረግ ሌለኞቹ ቡድኖች የተወሰኑ ነገሮችን ለምን እንደሚያደርጉ እና እነዚህም ጉዳዮች ለምን አስፈላጊ እንደሆኑ እንዲረዱ ያስችላቸዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች፣ በአካባቢያቸው ያለው አገልግሎት እጦትን በኃይል የሚቃወሙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ሥነ ምግባር የጎደላቸው፣ ኢ-ምክንያታዊ እና አውዳሚ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። ሆኖም፣ ጋዜጠኞች ለሌሎች ሰዎች በምን ዓይነት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየኖሩ እንዳለ እንዲሁም ተገፍተናል ብለው ማሰብ ደረጃ እንደደረሱ እንዲረዱ በማገዝ ሰዎቹ የሚያደርጉትን ነገር ለምን እንደሚያደርጉት መረዳት ያስችላዋል።

ግጭቶች እየተባባሱ በሔዱ ቁጥር ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሌላውን ቡድን አባላት አንድ ዓይነት ባሕርይ እና መገለጫዎችን እንደሚጋሩ በመቁጠር ሁሉንም ጨካኝ እና እምነተ-ቢስ እንደሆኑ አድርገው ማየት ይጀምራሉ። እነዚህ ጭፍን አመለካከቶች የተቀናቃኝ ቡድኑ ትንሽ ክፍል በነውጥ ወይም በጭካኔ ድርጊት ውስጥ ከተሳተፈ፣ ሰዎች አጠቃላይ ቡድኑ እነዚህን እርምጃዎች የመውሰድ ፍላጎት እንዳለው ይሰማቸዋል።

ጋዜጠኞች ሰዎች በጭፍን እንደሚያስቧቸው አለመሆናቸውን የሚያሳዩ ማሳያዎችን በማቅረብ ጭፍን አመለካከት የሚይዙ ሰዎችን አስተሳሰብ መፈተን ይችላሉ። ይህን በማድረግ የሌሎች ቡድኖችን አባላት የሚመለከቱበትን ዕይታ እንደገና እንዲገመግሙና እያንዳንዱ ሰው ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንደሌለው እንዲገነዘቡ እንረዳቸዋለን።

ይህ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳዩ ብዙ ታሪኮች አሉ። በጎሳዎች መካከል ፅንፍ ይዞ የነበረው የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚካሔድበት ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ከሌላ ጎሳ የሆኑ ሰዎችን ከለላ የሰጡ ሰዎች ታሪክን የሚያወሳ በርካታ ምሳሌዎች ነበሩ። ተመሳሳይ ምሳሌዎችን በራሳችሁ ማኅበረሰብ ውስጥ ማሰብ ትችላላችሁ። እነዚህ ጉዳዮች የዜና ሽፋን ማግኘት አለባቸው። ምክንያቱም ጭፍን አመለካከቶችን ለመፈተን እንዲሁም ከሌላ ቡድን የሆነ ሁሉም ሰው ጠላት ሊሆን ይችላል የሚለውን አስተሳሰብ ለማፍረስ ይጠቅማሉ።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *