የአውሮፓ ኅብረትና የቡድን ሰባት አገሮች ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል

የአሜሪካ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ያለው ግጭት በአፋጣኝ እንዲቆምና በክልሉ ኢሰብዓዊ ጥሰቶችን የፈጸሙ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

አሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተመደቡት ጄፍሪ ፊልትማን በኢትዮጵያ፣ በግብፅ፣ በሱዳንና በኤርትራ ያደረጉትን የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አሰቃቂው የትግራይ ክልል ግጭት እንዲያበቃ አሜሪካ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር እንደምትሠራ አስታውቋል።

‹‹ከዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር በመሆን በትግራይ ክልል ጦርነት እንዲቆምና በክልል ያለው አሰቃቂ ግጭት እንዲያበቃ፣ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብና ኢሰብዓዊ ጥሰቶችን የፈጸሙ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንሠራለን›› ሲል፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ያለው ፈርጀ ብዙ ተግዳሮት ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳያመጣ እንቅፋት እንደሆነ፣ የትግራይ ክልል ቀውስም የዚህ ችግር አንዱ ምልክት መሆኑን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማን ሰሞኑን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከሌሎች የፖለቲካ አመራሮች ጋር መምከራቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህን ፈርጀ ብዙ ችግሮች በተሻለ ሁኔታ መቅረፍ የሚችለው ሁሉንም የሚያሳትፍ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር መሆኑን፣ የሁሉንም ዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች በማክበር የአገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰን የሚቻልበት ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው ማለታቸው ተገልጿል።

ወደ እዚህ ግብ ለመድረስ ግን በቅድሚያ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው መውጣት እንዳለባቸው ማስረዳታቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛው ተልዕኮ አንዱ አካል ሉዓላዊነቷ የተከበረና አንድ የሆነች ኢትዮጵያን የሚያረጋግጥ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ያለው ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነትና የፖለቲካ ውጥረት አሳሳቢ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፊልትማን ያደረጉትን የመጀመርያ ጉዞ የተመለከተ ሪፖርት በቀናት ውስጥ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። የአሜሪካ መንግሥት መግለጫ በወጣበት በዚሁ ቀን፣ የአውሮፓ ኅብረትም በትግራይ ክልል ቀውስ ላይ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥቷል።

የኅብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጭ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጆሴፍ ቦሬል ከኅብረቱ የቀውስ ጉዳዮች አስተዳደር ኮሚሽነር ጋር በመሆን ባወጡት መግለጫ፣ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን የፀጥታ ኃይሎች ማስተጓጎላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ማረጋገጡን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ክልከላን እንደ ጦር መሣሪያ መገልገል ዓለም አቀፍ ወንጀል መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሮቹ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዳይደርስ ሆን ብለው ክልከላ ያደረጉ አካላት በሕግ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።

ይህንኑ ተመሳሳይ አቋም የቡድን ሰባት አገሮች ከሁለት ሳምን በፊት በወጡት መግለጫ አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በኋላ በዚሁ ጉዳይ ላይ እንደሚመክሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *