በቅርቡ በሽብር የተፈረጀው ህወሐት ሲመራው በነበረው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም የተጀመረው ወታደራዊ ግጭት ሰባተኛ ወሩን ይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፣ በሕዳር ወር መጀመርያ ላይ የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌዴራል ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሏን ተከትሎ፣ ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ ቢናገሩም፣ አሁንም በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች ውጊያዎች መቀጠላቸው ሪፖርቶች ያመላክታሉ።

እንደ ዓለም አቀፍ መንግሥታት ሪፖርት ከሆነ በክልሉ የቀጠለው ግጭት ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። በሌላ በኩል ሰሞኑን በሐውዜን ወረዳና በተለይ ደግሞ በገርዓልታ ተራሮች ዙርያ ውግያ መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከሚያዝያ 25 2013 ጀምሮ በሶስት ግንባሮች ውጊያ መካሄዱን እነዚህ ነዋሪዎች ጨምረው ተናግረዋል።

ከአንድ ቤት ተቆፍረው የወጡ ሰባት ህጻናት

ሃፍቶም የተባለው የሐውዜን ከተማ ነዋሪ፣ ከጥቅምት 24 2013 ጀምሮ ሐውዜን “የውጊያ መናሃርያ ሆናለች ቢባል ማጋነን አይሆንም” ይላል። በአከባቢው ቢያንስ ለስድስተኛ ግዜ ውግያ መሰማቱንና፤ የበርካታች ሰላማዊ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ይናገራል። የዓይን ምስክሮች እንደሚሉት፤ ሚያዝያ 29 2013 ዓ.ም ላይ ሐውዜን በከባድ መሳርያ ድብደባ ተፈጽሞባታል።

በከተማዋ በ02 ቀበሌ የሚገኘው፤ የአቶ ብሩ በላይ መኖርያ ቤት ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል አንዱ ነው። “ከባድ መሳርያ ከመውደቁ በፊት በከተማዋ ምንም ነገር አልነበረም። በመጋብና ድጉም አቅጣጫ ግን ከርቀት የውግያ ድምጽ ይሰማ ነበር። ቤቱ ላይ በከባድ መሳሪያ ጥቃት ሲደርስ በርከት ያሉ ሴቶች ነበሩ። በተለይ በአንድ ክፍል ደግሞ የጎረቤት ልጆችን ጨምሮ ሰባት ህጻናት ነበሩ” ትላለች ከአደጋው የተረፈችው ግደይ።

በህይወት የተረፉት ህጻናት ለህክምና ወደ መቀለ አይደር ሆስፒታል የወሰደችው ግደይን ሁኔታውን ስታስረዳ፣ “በ16 [ሚያዝያ] የከባድ መሳርያ ድብደባ ነበር። የአሁኑ የሚያዝያ 29 ግን የከፋ ነው” ትላለች። እንደ ግደይ ገለጻ የተተኮሰው የከባድ መሳሪያ መካከል አንዱ በከተማዋ 02 ቀበሌ በሚገኘው የአቶ ብሩ በላይ መኖርያ ቤት ላይ ወድቆቤቱ ሙሉ በሙሉ ተደርምሷል።

ግደይ አምስቱን ልጆች በመያዝ በቅድሚያ ወደ ውቅሮ ሆስፒታል ያመራች ሲሆን አንዷ ተሽሏት ወደ ቤተሰቦቿ ስትሄድ ቀሪዎቹን ወደ አይደር ሆስፒታል ወስዳ ህክምናቸውን እየተከታተለች መሆኑን ትናገራለች። የሞቱት ሕጻናት ዕድሜያቸው ሁለት ዓመት መሆኑን የምትናገረው ግደይ በህይወት ተርፈው በህክምና ላይ የሚገኙት ደግሞ ከ7 እስከ የ12 ዓመት ያሉ ልጆች መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

የሁለተኛ ዓመት የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪ የሆነው ተክለብርሃን ከአራቱ ህጻናት መካከል ሶስቱን በሆስፒታሉ ውስጥ ማየቱን ይናገራል። ህጻናቱ ስብራት፣ የመቁሰልና የቆዳ መሰንጠቅ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ገልጿል። “በከባድ መሳርያ የተመታ ቤት ፈራርሶ፤ እዛው ተደፍነው ተቆፍረው እንደወጡ ነው የነገሩን፤ የፈራረሰው ድንጋዩም ጭምር ጉዳት አድርሶባቸዋል ብለን ነው የምናስበው።”

የመከላከያ ሰራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮለኔል ጌትነት አዳነ፤ በሐውዜን ከተማና አካባቢው በህጻናት ላይ ደረሰ ስለተባለው ጉዳት ተጠይቀው በከባድ መሳርያ ድብደባ የግለሰብ ቤት ወደመ የሚባል ነገር ስህተት ነው ብለዋል።

“በሽብር የተፈረጀው ከባድ መሳርያ የለውም፤ ከባድ መሳርያ ያለው እኛ ጋር በመከላከያ ሰራዊት እጅ ነው። የት ቦታ ላይ መተኮስ እንዳለበት ያውቃል። . . . በከባድ መሳርያ ድብደባ የግለሰብ ቤት ወደመ የሚባል ነገር ስህተት ነው። እንደዛ የሚሆንበት ዕድል በጣም ውሱን ነው። የደረሰ ጉዳትም ካለ ወደፊት ታይቶ ይታረማል ፤ ይፋ የሚደረግም ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እስካአሁን ባለው መረጃ ግን በከባድ መሳርያ ይህን ያህል ጥቃት ደረሰ የሚል በመከላከያ ሰራዊት በፍጹም የለም። እንደው አንደኛ ነገር የሚባለው፤ እሱ ውግያ የተመራበት አግባብ በጣም በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት መሆኑ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

gerealta

የፎቶው ባለመብት,GT

ግደይ ሚያዝያ 17 2013 ዓ.ም የመንግሥት ወታደሮች ተኩሰው የገደሉዋቸው የአንድ ቤተ ሰብ አባላትን ታስታውሳለች። ወታደሮቹ አማርኛም ትግርኛም የሚናገሩ ነበሩ ስትልም ትናገራለች። ግደይ መጋቢት 28 ደግሞ ሁለት የቅርብ ዘመዶችዋ የሚገኙባቸው አራት የገጠር ነዋሪዎች በከተማ ውስጥ እንደቀበረች ትናገራለች።

አርሶ አደር ግርማይ በበኩሉ ሚያዚያ 17 2013 ዓ.ም የመንግሥት ወታደሮች ሊገድሉት እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል። በዕለቱ በቤቱ ውስጥ ድግስ እንደነበር የሚናገረው ግርማይ፤ ‘ጠላ ለጁንታ ነው የጠመቅከው’ ብለው ሊገድሉኝ መሳርያ አቀባብለውብኝ ነበር” ይላል።

በአካባቢው ሚያዝያ 16 2013 ዓ.ም ከባድ ጦርነት መካሄዱን የሚያስታውሰው ግርማይ “ከቀኑ ጀምረን ፈርተን ከቤት አልወጣንም። ‘ጧት ተነስተው ማነው ሲዋጋን ያደረው’ ብለው ጠየቁን። ‘እኔ ከቤት አልወጣሁም፤ አላየሁም’ ስላቸው አላመኑኝም” ይላል።

“ትልቁ ነገር በሕይወት መትረፌ ነው” የሚለው ግርማይ፣ የልጁ ወርቅና የባለቤቱን ብርና ልብስ፤ ሽልማት በሙሉ፤ ሴቶቹ ወታደሮች እንደወሰዱበት ይናገራል። አንደኛዋ ሴት ልጁ በቅርቡ ያገባች እንደሆነች የሚያስረዳው ግርማይ በስጋት፤ ዕቃዋን ጠቅልላ ወደ መቀለ ለመሄድ ተዘጋጅታ ባለችበት እንዲህ አይነት ሁኔታ ማጋጠሙን ለቢቢሲ አስረድቷል።

ኮሎኔል ጌትነት ግን ሰራዊቱ ከገበሬ አብራክ የወጣ ህዝባዊ ነው በማለት “በፍጹም ተዓማኒነት የሌለው” በማለት አጣጥለውታል። “ሰራዊቱ፤ አንዱ ስልጣን ላይ ሲቆይ ህዝባዊ ሌላ ሰው ስልጣን ላይ ሲወጣ ገዳይ እንዲሆን ሆኖ አይደለም የተገነባው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በህዝባዊነቱ ነው የሚታወቀው።” ከሚያዝያ 25 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሶስት ግንባሮች ውጊያዎች መካሄዳቸው ይነገራል።

ራሱን ‘የትግራይ መከላከያ ሰራዊት’ [TDF] ብሎ የሚጠራው ኃይል ቃል አቀባይ የሆኑት ገብረ ገብረጻዲቅ፤ ለህወሓት ቅርበት ባለው ድምፀ ወያነ ፌስ ቡክ ገጽ ላይ በሰጠው መግለጫ፤ በሶስቱ ግንባሮች በአጠቃላይ 1 ሺሕ 896 የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ከ1800 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውንና መማረካቸውን ይናገራሉ።

የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት በበኩላቸው ሰራዊቱ በአካባቢው የአሰሳ እንቅስቃሴ ማድረጉን ሆኖም የደረሰበት ጉዳት እንደሌለ፤ በህወሓት የተሰራጨው መረጃ ውሸት እንደሆነ ተናግረዋል።

ኃላፊው ገርዓልታ አካባቢ ውጊያ መካሄዱን ተናግረው ወደፊት የተሟላ መግለጫ እንደሚሰጥበት አክለዋል። በህወሓት የተሰጡ መግለጫዎችን በተመለከተ ግን፡ “እነሱ ያልገደሉት ምን ነገር አለ፤ እነሱ ‘ገደልን’ በሚሉት ልክ ቢሆን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ሰራዊት አይኖራትም ነበረ” በማለት ውሸት መሆኑ እና ድርጅቱ በሌላ አካባቢ በተለይ ደግሞ በሑመራ ደረሰበት ያሉትን ጉዳት ለመሸፈን መሆኑን ተናግሯል።

አክለውም “ህወሐት በአሁኑ ወቅት ሰራዊት ይዞ መከላከያን ደምስሶ የሚገፋበት አቅም የለውም። እውነታው ይሄ ነው። አሁን ያለው የድብብቆሽ ጨዋታ ነው። መደበቅ፤ አመራሮቹን መሸሸግ። በተለያየ ነገር አመሳስሎ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ካልሆነ በስተቀር”።

“ቢያንስ ቢያንስ እንኳን ተአማኒነት እንዲኖረው፤ ደፈጣ አድርገን መታን ቢባል ያስኬዳል፤ ደፈጣ ግለሰቦችንም ሊያደርጉት ስለሚችሉ። ውግያ ገጥሞ ግን የሚገፋ ኃይል አለ ተብሎ የሚባለው የውሸት ፕሮፖጋንዳቸው አካል ነው” ብለዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *