ስድስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ በተያዘለት ቀን ማካሄድ እንደማይቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬው ዕለት ግንቦት 7፣ 2013 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር እያደረገ ባለበት ወቅት እንዳለው አገር አቀፉን ምርጫ በተያዘለት ቀን ማካሄድ እንደማይቻል አስታውቋል።

በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያ መክሯል። ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ለማካሄድ እቅድ ተይዞ ነበር።

ይሁንና የምርጫ ካርድ ምዝገባው እና ሌሎች ስራዎች በተያዘላቸው ቀናት ባለመጠናቀቃቸው የተነሳ ምርጫው በተያዘለት ቀን መካሄድ እንደማይችል አስታውቋል። ምርጫ ቦርድ አክሎም በአዲሱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ጋር በተመሳሳይ ቀን ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ ብሏል።

በመሆኑም ድምጽ መስጫው በሁለት ወይንም በሶስት ሳምንታት እንዲራዘም ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ አቅርቧል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኘውን ሃሳብ ግምት ውስጥ በማስገባት በቅርቡ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስና ይፋ እንደሚደረግም ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጨማሪ በዛሬው ምክክር ላይ እንዳስታወቀው እስከ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 36 ሚሊዮን 245 ሺህ 444 ሰዎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጿል።

የምርጫ ካርድ ከወሰዱት መካከል 16.6 ሚሊዮኑ ሴቶች ሲሆኑ ፤ 19.5 ሚሊዮኑ ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት 50 ሚሊዬን ዜጎች ካርድ ሊወስዱ እንደሚችሉ ግምቱን አስታውቆ ነበር።

እንደ ምርጫ ቦርድ መረጃ ከሆነ ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ከተገመተው በላይ የመራጮች ካርድ ከተወሰደባቸው መካከል ናቸው። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የመራጮች ምዝገባ መከናወኑን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *