ከቀናት በፊት በደምቢ ዶሎ ከተማ በአባባይ በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች የተገደለው ወጣት ወላጅ አባት፤ የልጃቸውን አስክሬን እጁ ወደ ኋላ ታስሮ አደባባይ ሆኖ ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሰኞ ግንቦት 2 ባለስልጣናት የአባ ቶርቤ አባል ነው ያሉት ወጣት በአባባይ መገደሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። የዓይን እማኞች አማኑኤል የተባለው ወጣት በአባባይ መገደሉን ሲናገሩ፤ የመንግሥት ባስልጣናት በበኩላቸው ‘የአባ ቶርቤ’ አባል ነው የሚሉት ወጣት በአደባባይ እንዲታይ ተደረገ እንጂ በአደባባይ አልተገደለም ይላሉ።

የወጣቱ ያለ ፍርድ ሂደት መገደሉ አሳሳቢ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ አውጥቷል። የወጣቱ ከፍርድ ውጭ መገደሉ እና በአደባባይ ለሕዝብ እንዲታይ የተደረገበት ሁኔታ በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካቶችን ያስቆጣ ጉዳይ ሆኖ አልፏል።

የአማኑኤል አባል ምን ይላሉ?

የአማኑኤል አባት አቶ ወንድሙ ከበደ የልጃቸውን መገደል ሳይሰሙ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው መጥተው ፍተሻ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። “ምንድነው የተፈጠረው ብዬ ስጠይቅ፤ ‘የሆነውን አታውቅም?’ ብለው ጠይቁኝ” ይላሉ። “አዎ አላውቅም ስላቸው ‘የሆነው ታወቃለህ’ አሉኝ” በማለት ይናገራሉ። የጸጥታ ኃይሎቹ መኖሪያ ቤታቸውን ከፈተሹ በኋላ እርሳቸውን እና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመኪና መሄድ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

“አደባባዩ ጋር ስንደርስ ባለቤቴ ‘ልጄ ልጄ’ እያለች መጮህ ጀመረች። ‘ልጄ ነው ልጄ ነው’ ስትል ወታደሮቹ ‘አዎ ልጅሽ ነው’ አሏት” አቶ ወንድሙ ከበደ የልጃቸውን አስክሬን አደባባይ ላይ ማየታቸው በእርሳቸው እና በባለቤታቸው ላይ ድንጋጤን እንደፈጠረ ይናገራሉ። “የልጄን አስክሬን እጁ ወደ ኋላ እንደታሰረ አየሁት” በማለት ይናገራሉ።

የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዘዋቸው መሄዳቸውን ያስረዳሉ። ከዛም የልጃቸው አስክሬን ወዳለበት ስፍራ መልሰው እንደተወሰዱ ይናገራሉ። የልጃቸው አስክሬን ባለበት አደባባይ ከደረሱ በኋላ የአማኑኤል እናት ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው እንደነበረ ይናገራሉ። “እሷ እራሷን መቆጣጠር አልቻለችም። ትንከባለላለች፤ ትጮሃለች። በጣም እየጮኃች ‘እኔንም ግደሉኝ’ ስትል አትረብሹ ብለው ደበደቡን” ይላሉ።

የአማኑኤል አባት የልጃቸውን አስክሬን ለማንሳት ስላልተፈቀደላቸው “ወደ ቤት ተመልሰን ማልቀስ ጀመርን” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ። ከቆይታ በኋላ የአገር ሽማግሌዎች አስክሬኑን አንስተው ወደ መኖሪያ ቤት ካመጡላቸው በኋላ ቀብር መፈጸሙን ይናገራሉ።

የአማኑኤል አባት ልጃቸው ቤተ-ክርስቲያን ያደገ ዲያቆን ነበር ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት,SOCIAL MEDIA

አማኑኤል ማን ነበር?

የአማኑኤል አባት ልጃቸው የ17 ዓመት ወጣት እና የ10ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረ ይናገራሉ። ልጃቸው ላይ ስለ ቀረበው ክስ ምንም እንደማያወቁ የሚናገሩት አባት፤ ልጃቸውን ቤተ-ክርስቲያን ያደገ ዲያቆን ነበር ሲሉ ያስታውሱታል።

ስለ አማኑኤል ግድያ የምናውቀ

‘የአባ ቶርቤ’ አባል ነው የተባለው አማኑኤል ሰኞ ግንቦት 2 2013 ዓ.ም. በደምቢ ዶሎ ከተማ በሚገኝ አደባባይ ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተገድሏል። ወጣቱ ከመገደሉ በፊት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በደምቢ ዶሎ ከተማ ኮሚኒኬሽን ጸ/ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ ተለጥፎ ነበር። ኮሚኒኬሽን ቢሮው ሰዎችን ሲገድል በነበረው እና ‘የአባ ቶርቤ’ ቡድን አባል በሆነው ላይ እርምጃ ተወሰደ ሲል ጽፏል።

ወጣቱ ከመገደሉ በፊት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ ይታያል። ቪዲዮን እየቀረጸ የሚገኘው ሰው የወጣቱን ስም እና የትውልድ ስፍራውን ይጠይቀዋል። አደባባይ ፊትለፊት የቆመው ወጣት ስሙ አማኑኤል ወንድሙ ከበደ እንደሚባል እና ትውልዱ ደምቢ ዶሎ ከተማ 07 ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሆነ ይናገራል።

እጁ ወደ ኋላ የታሰረው ወጣት አንገቱ ላይ ሽጉጥ ተንጠልጥሎ ይታያል። በወጣቱ እግር ላይ እና በዙሪያው ደም የሚታይ ሲሆን ልብሱም በጭቃ ተለውሷል። በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎ ተከቦ ይታያል።

ወጣተቱ በፖሊስ ኃይል ተከቦ

የፎቶው ባለመብት,DEMBI DOLO CITY ADMINISTRATION COMMUNUCATION

ወጣቱ ለምን ተገደለ?

የከተማው ኮሚውኒኬሽን ጽ/ቤት እንደሚለው ከሆነ ይህ ወጣት የመንግሥት ባለስልጣናት በመግደል የሚታወቀው “አባ ቶርቤ’ የተሰኘው ህቡዕ ቡድን አባል ነበር።ወጣቱ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊትም ንጋት ላይ ገመቹ መንገሻ የተባለ ግለሰብ በጥይት መትቶ ለማምለጥ ሲሞክር “በጸጥታ ኃይሎች ጠንካራ ትስስር እግሩን ተመትቶ ተይዟል” ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ከቀናት በፊት በደምቢዶሎ ከተማ የኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትዎርክ ጋዜጠኛ የነበረውን ሲሳይ ፊዳ የገደለው የአባ ቶርቤ ቡድን ነው ሲል አክሏል።

የዓይን እማኝ ምን ይላሉ?

የደምቢዶሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን የማንጠቅሰውወጣቱ በአደባባይ ሲገደል ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። “አማኑኤል ሕዝብ የሚወደው ልጅ ነበር” ካሉ በኋላ፤ በጥይት ተመትቶ ከተያዘ በኋላ “ሲገደል በዓይናችን አይተናል” ብለዋል።

እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት ከሆነ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ አካላት ወጣቱ ለመያዝ ሲንቀሳቀሱ ወጣቱ ከአንድ ሱቅ እቃ እየገዛ ነበር ይላሉ። ይህ ነዋሪ በአደባባይ ከተገደለው ወጣት በተጨማሪ በተመሳሳይ ቀን ሌሎች ሁለት ወጣቶች በጥይት ተመትተው ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሌላ ስፍራ ስለመወሰዳቸው አውቃለሁ ብለዋል።

የመንግሥት አካል ምን ይላል?

የቄለም ወለጋ ዞን የደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተሰማ ዋሪዮ ወጣቱ ቆስሎ ከተያዘ በኋላ ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ እንጂ በአደባባይ አልተገደለም ይላሉ። አቶ ተሰማ “ተጠርጣሪ አይደለም” በማለት የወጣቱን ወንጀለኛነት በማረጋገጥ የተወሰደው እርምጃ አግባብ ስለመሆኑ ይሞግታሉ። በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በክልሉ ህዝብን እያሸበሩ ነው የሚሏቸው አካላት ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ በአፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

“በከተሞች ሰውን እየገደሉ ህዝብን ማሸበር የነሱ የእለት ተእለት ተግባር ነው። እነሱ የሚያደርጉት መግደል ነው። ሰላምን ለማስከበር የሚሄደው ኃይል እነዚህ አካላትን አጋልጦ እርምጃ ወስዶ ሊቆጣጠር ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ የተወሰደው እርምጃ የትኛውም አይነት ይሁን ህዝብን አሸብሮ፣ አስፈራርቶ እቆጣጠራለሁ የሚለው ኃይል ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።” ብለዋል።

ግድያውን ተከትሎ ማን ምን አለ?

አማኑኤል ፍርድ ሳይሰጠው በአደባባይ መገደሉ አሳሳቢ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ አውጥቷል።። በወንጀል ተጠርጥሯል የተባለው አማኑኤል ወንድሙ ከፍርድ ውጭ የተፈፀመበት ግድያና በአደባባይ ለሕዝብ እንዲታይ የተደረገበት መንገድ አሳስቦኛል ብሏል ኮሚሸኑ።

በማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም ግድያውን በመቀውም ለግድያው ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲጠይቁ ነበር። ባለሥልጣናት ጉዳዩን በአፋጣኝ እንዲመረምሩ እና ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ኮሚሽኑም ጠይቋል።

አባ ቶርቤ ማነው?

“አባ ቶርቤ” የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ባለ ሳምንት” ማለት ነው። ይህ ቡድን በኦሮሚያ የተለያዩ ስፍራዎች ታጥቆ ከሚንቀሳቀሰው በቅርቡ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው አካል ጋር ግንኙነት እንዳለው የክልሉ ባለስልጣናት ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ “አባ ቶርቤ ማለት የአሸባሪው ሸኔ የከተማው ክንፍ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። በከተማ ደግሞ ‘አባ ቶርቤ’ እና ‘ሶንሳ’ ተብሎ የሚጠራ ቡድን አለው። እነዚህ ቡድኖች በተቻላቸው መጠን ግድያ በመፈጸም ሽብር ለመፍጠር የሚሞክሩ ናቸው ሲሉ ተናግረው ነበር።

አቶ ጅብሪል መሐመድ እንደሚሉት የዚህ ቡድን አባላት ምንም አይነት የተለየ ስልጠናም ሆነ መሳሪያ የላቸውም። የሚጠቀሙት ስልት፤ ማህበረሰቡን በመምሰል፤ ለማምለጥ በሚያመቻቸው ቦታ በድንጋት አደጋ አድርሰው ይሰወራሉ” ብለው ነበር አቶ ጅብሪል።

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *