ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ባሉት ሶስት አመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ሁለት ቡድኖች አሸባሪ ተብለው ሚያዚያ 28 2013 ዓ.ም ተፈርጀዋል።
ስራ አስፈፃሚው ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውን ቡድን ‹‹ሸኔ›› በማለት ላለፉት ሶስት አመታት የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ፈፅመዋል ሲል ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ አስፍሯል። ይህ የውሳኔ ሃሳብ ከፀደቀበት ዕለት ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፈቃዱ ፀጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የውሳኔ ሃቡን ተከትሎ የሚወጡ ዝርዝር ማብራሪያዎች ይኖራሉ ያሉት ፍቃዱ እነዚህ ማብራሪያዎች በተለይም አዋጁ ላይ ያሉ ድንጋጌዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው ይላሉ። ይህንን ውሳኔ አስመልክቶ እስካሁን ያለው ዘርዘር ያለ መረጃ ይሄው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ነው።
የውሳኔ ሃሳቡን ይዘት ዝርዝር እንመልከት
በጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በመግቢያው ላይ ለምን ሁለቱ ቡድኖች በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ጥያቄው እንደቀረበ ያብራራል። ‹‹ሰላማዊ ዜጎች ከድርጅቱ ጋር አንዳይተባበሩ፣ ድጋፍ እንዳይሰጡ አባል እንዳይሆኑ ብሎም የድርጅቱን ንብረቶች በመውረስ የፋይናንስ አቅሙን ለማዳከም›› ያለመ መሆኑን ይገልፃል።
ከሁለቱ ድርጅቶች በተለይም ስለ ሕወሃት ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ያቀረበው ሰነዱ የትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ የተሰኘ ሃይል በክልሉ የፀጥታ ቢሮ ድጋፍ ማቋቋሙን ይገልፃል። ቀጥሎም የትግራይ መከላከያ ሃይል የተባለ ወታደራዊ ሃይል ለማደራጀት የሚያስችል ዶክትሪን በማዘጋጀት ለህወሓት ስራ አስፈፃሚ ቀርቦ ፀድቋልም ይላል።
የዚህን አደረጃጀት መፅደቅ ተከትሎ ለጦርነት ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል፤ በ 2012 ዓ.ም መጀመሪያ ላይም ‹‹በይፋ ዘመኑ የመከታ ነው›› በማለት ሕዝቡን ቀስቅሷል ሲልም ይወቅሳል። ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያሰናዳው ይህ ባለ 12 ገፅ የውሳኔ ሃሳብ ህወሓት ‹‹የፌደራሉን መንግስት ለማዳከም በየክልሉ ችግር ለመፍጠር በማሰብ›› በተለያዩ ክልሎች ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ሰርቷል ሲል የተለያዩ ፓርቲዎችን ጠቅሷል።
የተጠቀሱት ፓርቲዎች የትኞቹ ናቸው?
በቅድሚያ የተጠቀሰው የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ሲሆን የጦር መሳሪያ እና በጀት ከህወሃት ቀርቦለታል ሲል ይህ ሰነድ ያስነብባል። ‹‹በአማራ ክልል በቅማንት አካባቢ ለሚነሱ ግጭቶች ሕወሃት የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ አቅርቧል፤ እንዲሁም በኦሮሞ ብሄረሰብ አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ከአፋር ሕዝብ ጋር እንዲጋጭ ከ 100 በላይ የጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ የተደረገ ሙከራም ነበር›› ሲል አክሏል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህወሃት ከሁለት ፓርቲዎች ጋር ሲሰራ ነበርም ይላል። የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የቤንሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ለሰላም እና ዴሞክራሲ የተባሉ ድርጅቶችን በገንዘብ ብሎም በመሳሪያ ደግፏል የሚለው ይህ የውሳኔ ሃሳብ እነዚህ ፓርቲዎች በክልሉ ውስጥ ላሉ ቀውሶች ተጠያቂ ናቸው ሲልም ይወቅሳል።
እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ‹‹በተለምዶ ሸኔ ተብሎ ለሚጠራው ቡድን በገንዘብ እና በመሳሪያ ድጋፍ አድርጓል›› ይህም ‹‹ የሰው ህይወት እና ንብረት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል›› ሲልም ይከስሳል። በተጨማሪም ‹‹የመከላከያ ሰራዊት ላይ ህወሓት ጥቃት ሲፈፅም የዚህን ቡድን ታጣቂዎች በአጋዥነት አብሮ አሰልፏል›› ይላል።
በመጨረሻም ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ሲያደርስ እና የፌደራል መንግስቱን ሲቆጣጠር አብረውት ስልጣን እንዲይዙ በማሰብ የፌደራሊስት ሃይሎች ህብረት የተባለ ጥምረት ፈጥሮ ተንቀሳቅሷል ሲልም አብራርቷል።
ህወሓት ከቀረቡበት ክሶች መካከልም ወደ ባህርዳር፣ ጎንደር እና ኤርትራ ሮኬት በማስወንጨፍ በንጹሃን ላይ እና በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት አደርሷል የሚሉ ይገኙበታል። ‹‹ይሄው ሃይል መቀሌን እና የክልሉን ዋና ዋና አካባቢዎች ቢለቅም ማህበረሰብ መሃል እና በየበረሃው ተደብቆ ንፁሃን ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛል›› ብሏል።
‹‹ሸኔ››
በውጪ አገር በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆየው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ‹‹የተወሰነው የወታደራዊ ክንፉ አባላት በጫካ ውስጥ በመቅረት እንቅስቃሴውን ቀጥሏል›› ሲል ሰነዱ ያስነብባል። በኦሮሚያ ክልል ብሎም ከክልሉ ውጪ በመንቀሳስ ሰዎችን መግደል እና ከቤት ንብረት ማፈናቀል ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ሰራዊት ወይም በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ‹‹ሸኔ›› የተባለው ቡድን ላይ የቀረበ ክስ ነው።
በድርጅቱ ተግባር በ 2013 ብቻ 112 ፖሊስ፣ 57 ሚሊሻ፣ እና 18 በተለያየ ደረጃ ያሉ አመራሮችን ገድሏል የሚለው ሌላኛው ክስ ነው። ሸኔ በጥቅምት ወር በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ 36 ንፁሃን ሰዎችን ገድሏል የሚል ክስም ሰፍሯል። ሌላው የሸኔ ተግባር ነው የተባለው አባ ቶርቤ የተሰኘ ገዳይ ቡድን አዋቅሮ ግድያዎችን መፈፀም ነው። የውሳኔ ሃሰቡን ያፀድቅልኛል ሲል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የላከው ይህ ሰነድ ሁለት የክስ መዝገቦችን በሸኔ ላይ ማስረጃ ይሆኑኛል ሲል ይጠቅሳል።
ከዚህ ቀደም ኮሎኔል ገመቹ አያን ጨምሮ 20 ሰዎች ተከስሰውበት የነበረው የእነ ኪሱ ቂጡማ መዝገብ አንዱ ነው። ኪሱ ቂጡማ በአምቦ ከተማ በሚያዚያ 08/2011 ዓ.ም የቦምብ ጥቃት በመፈፀም ክስ የቀረበባቸው ግለሰብ ነበሩ። በተጨማሪም በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ ከነበሩ ተማሪዎች እገታ ጋር ተያይዞ የተከፈተው የእነ ካሊፋ አብዱራህማን መዝገብ ሌላኛው ለምክር ቤቱ የቀረበ ሰነድ ነው።
ይህ ፍረጃ ለዜጎች ምን ማለት ነው?
የውሳኔ ሃሳቡ ከመፅደቁ በፊት በኦሮሚያ ክልል ያሉ የፀጥታ ሃይሎች ዜጎችን ከሸኔ ጋር በመስራት እና በመደገፍ በሚል ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያስራሉ፣ ያሰቃያሉ የፍርድ ቤት ስልጣንም እንደማይከበር የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ሰብስቤያለሁ ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባሳለፍነው ሳምንት ዘለግ ያለ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱም በ 21 የተመረጡ የፖሊስ ጣቢያዎች ላይ በተካሄደ ክትትል ላይ የተመሰረተ ነው ተብሏል። ኮሚሽኑም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት ተከትሎ ‹‹በወቅታዊ ሁኔታ›› በሚል፣ በተለያዩ ግዜያት በተጠሩ ሰልፎች ተሳታፊ ናችሁ በሚል እንዲሁም የኦነግ ሸኔ አባል ወይም ደጋፊ ናችሁ በሚል የታሰሩ ሰዎችን ማግኘቱን አስታውቆ ነበር።
ከእስረኞቹም በርካታ ኢ-ሰብአዊ አያያዞች መኖራቸውን መረዳቱን እና መደበኛ የፍርድ ሂደት የተጓደለባቸውን በርካታ ግለሰቦችን ማግኘቱን አስታውሶ ይህ እንዲሻሻልም ምክረ ሃሳብ ሰጥቶ ነበር። ታዲያ ይህ የሽብርተኝነት ፍረጃ ይህንን ችግር አያባብሰውም ወይ ይህንን ውሳኔ የዜጎችን መብት አደጋ ውስጥ ሳይከት መፈፀም የሚችል መወቅር አለ ወይ ስንል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉን ፈቃዱን ጠይቀናቸዋል።
ከመደበኛው ስልጠና የላቀ ስልጠና የሚያስፈልገው የፀጥታ ሃይል እንደሚያስፈልግ የሚያምኑት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ፈቃዱ ፀጋ የኮሚሽኑን ሪፖርት ግን ገና የምንመለከተው ነው ይላሉ። ‹‹ይህ የውሳኔ ሃሳብ ብሎም ያሉትን ህጎች ያለመፈፀም የሚያስቀጣው ሕግ አስከባሪውንም ነው፣ በኮሚሽኑ የተጠቀሰው መግለጫም መግለጫ ሆኖ አይቀርም፤ ለኛ ይላካል እንመረምረዋለን›› ሲሉ ፈቃዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መንግሥት በትግራይ ክልል የመንግስት መዋቅር መፍረሱን ተከትሎ መደበኛ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤቶች ብሎም ፍርድ ቤቶች ወድመውብኛል በማለት ሲገልፅ ቆየቷል። ታዲያ መደበኛ የሕግ እና የፀጥታ መዋቅር በሌለበት ይህንን ውሳኔ የንፁሃንን መብት እና ደህንነነት ሳይጋፋ መተግበር ይቻላል ወይ ስንል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉን ጠይቀናቸዋል።
‹‹በትግራይ ክልል በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ምክኒያት የተወሰኑ ከመደበኛ የሕግ ስርአት የወጡ ተግባራት ይኖራሉ እነሱን እየመረመርን ነው›› ያሉት ፈቃዱ የሕግ ተቋማትን መልሰን እያቋቋምን ነው ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹አንዳንዴ ከማዕከላዊ መንግስት በጣም የራቁ ቦታዎች ላይ ችግሮች እንዳሉ እንረዳለን፣ ለሕግ አስፈጻሚዎችም ተከታታይ ስልጠና እንሰጣለን›› ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የውሳኔው እንድምታ እና ውጤት ምን ይዞ ይመጣ ይሆን ?
ምን አልባትም ይህ ውሳኔ በኦሮሚያ ብሎም በትግራይ ክልል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ወደ ሕግ ማዕቀፍ ለማምጣት እንዲሁም የእርምጃዎቹን ስፋት የሚጨምር ይሆናል ሲሉ አደም (ዶ/ር) ይናገራሉ። ከፋይናንስ አንፃር ሕወሃት ከሸኔ በላይ ከፍተኛ የሆነ ንብረት አለው ይላሉ።
በቅርቡ ኢሕአዴግ ሲፈርስ የተከፋፈሉት ሃብት ትልቅ ነበር የሚሉት አደም ከምርጫ ቦርድ ሲሰረዝም የፓርቲው ንብረት በወኪል ተቆጣጣሪ ሲተዳደር የነበረው። ከዚህ ውሳኔ በኋላ ግን ይህ ገንዘብ ወደ መንግሥት እንዲወረስ ማድረጉ ከፍተኛ የሆነ እና የሚታይ ተጽእኖ ይኖረዋልም ይላሉ።
ህወሓት አባላት የነበሩት የተመዘገበ ፓርቲ ነበር። ይህ አባላቱ በሙሉ ከዚህ በኋላ በአባልነት እንዲሁም በድጋፍ እንዳይቀጥሉ ያደርጋል ሲሉም አደም (ዶ/ር) ይናገራሉ። ‹‹እስከዛሬ የትግራይ ተወላጆችን በጥርጣሬ ብቻ እርምጃ ሲወሰድ ነበር። ይህ ውሳኔ ያንን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለማስገባት ብሎም ለማጠናከር የታሰበም ይመስላል›› ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
‹‹ይህንን የውሳኔ ሃሳብ የሚተገብረው በተለያዩ አካባቢ ያለው ሰው ነው። ሸኔ ማነው? ህወሓት ማነው? የሚለውን በመሬት ላይ ያለው ፈጻሚ በሚገባው ልክ የሚተገብረው እንደመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት ሊያስከትል መቻሉ እሙን ነው›› ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አደም በተለይም አንድ ቡድን አሸባሪ ተብሎ የሚፈረጅበት ሂደት በፍርድ ቤት የሚወሰን መሆን ነበረበትም ይላሉ።
ይህ በተለይም የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ሆነ የተወካዮች ምክር ቤት ፖለቲካዊ ተቋማት እንደመሆናቸው ውሳኔውን ለፖለቲካ አላማ ሊያውሉት መቻላቸውን እንደምክንያት ያነሳሉ። ሂደቱ ለሕግ ተርጓሚው ተሰጥቶ ቢሆን ሆሮ ግን እነዚህ ቡድኖች ማናቸው? ቡድኖቹ መሬት ላይ ያሉ ቡድኖች ናቸው ወይ? እንዲሁም አሸባሪ ቡድን ብሎ ለመፈረጅ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዋል ወይ? የሚለውን ይመረምሩ ነበር ሲሉም አደም ያብራራሉ። ለዚህም በምሳሌነት ጋናን ያነሳሉ።
‹‹በጋና መንግሥት ያለውን መረጃ አቅርቦ ተመዝኖ ነው ይህ የሚወሰነለት›› የሚሉት አደም ‹‹ምርጫ ሳምንታት ሲቀረው የተወሰነ ውሳኔ መሆኑ በራሱ ይህ ነገር ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ውጪ ነው ብሎ ለማመን ከባድ ያደርገዋል›› ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መጪው ምርጫ ላይ ያለው ተፅዕኖ ቀጥተኛ ላይሆን ቢችልም በተለይም መንግስት በአማራ ክልል ሸኔ ላይ እርምጃ አልወሰደም በሚል ሲወቀስ ቆይቷል፤ ይህንን ለመከላከል ያቀደ ሊሆን ይችላልም ብለዋል። ‹‹እነዚህ ቡድኖች መንግስትን ማሸነፍ ባይችሉ እንኳን ከፍተኛ ጫና መፍጠር የሚችሉ እንደሆነ የሚያሳይ ውሳኔ ነው። ምንም እንኳን ከአለማቀፍ ህብረተሰቡ የሚመጣውን የተደራደሩ ግፊት ለመከላከል መንግሥት ሊጠቀመው ይችላል።
ውኔው አለማቀፍ ገዢነት ያለው ውሳኔ ስላልሆነ ግፊቱን ያቆመዋል የሚል ግምት የለኝም›› ሲሉ አደም ለቢቢሲ ገልፀዋል። በኦሮሚያ ክልል ግን ይህ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሊጠነክር እንደሚችል ያሳያል፤ እንደ አደም። ‹‹እንደዛ ከሆነ በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ሊባባስ እንደሚችል ያሳል። ይሻሻል እንኳን ቢባል ከዛ በፊት ሊያበላሸው ይችላል›› ሲሉ አደም ገለጸዋል።