የአውሮፓ ሕብረት ቀጣዩን 6ኛ አገራዊ ምርጫ እንዲታዘቡ ባለሙያዎቹን ይልካል ሲሉ የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
ከአውሮፓ ሕብረት በተጨማሪ ከአሜሪካ እና ሩሲያ የተውጣጡ የባለሙያዎች ምርጫውን ለመታዘብ እንደሚመጡ የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባዩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከስምምነት መድረስ ባለመቻሉ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ አስቦ የነበረውን የምርጫ ታዛቢ እንዲቀር መወሰኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የአውሮፓ ሕብረት የቀደመ ውሳኔውን ሰርዞ ምርጫውን ለመታዘብ ስለመወሰኑ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ሕብረቱ የሚልካቸው የምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚሰማራበት ቁልፍ መለኪያዎች /ፓራሜትርስ/ ላይ ከመንግሥት ጋር ከስምምነት መድረስ አልተቻለም ብሎ ነበር።
የአውሮፓ ሕብረት ይህን ካለ በኋላ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ከአንድ ሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ምርጫ ለመታዘብ ካቀደው የአውሮፓ ሕብረት ጋር ያልተስማማቸው ሕብረቱ ሉዓላዊነትን የሚጻረር ጥያቄን በማቅረቡ ነው ብለው ተናግረው ነበር።
ቃል አቀባዩ በወቅቱ የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑኩን ላለመላክ የወሰነው በሁለት ምክንያት ነው ብለዋል። ይህም ሕብረቱ አገሪቱ የሌላትን የኮሚኒኬሽን ስርዓት ማስገባትን አስገዳጅ ማድረጉ እንዲሁም የምርጫውን ውጤት ይፋ የማደርገው እኔ ነኝ ማለቱን ተናግረው ነበር። ይህም የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና ደህንነት የሚጻረር ስለሆነ ከስምምነት ሳይደረስ ቀርቷል ሲሉ አስረድተው ነበር።
ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘው አቋም እንዳልተቀየረ ተናግረው፤ ከአውሮፓ ህብረት ስድስት አባላትን የያዘ ቡድን፣ ከአሜሪካ ሁለት ተቋማት የተውጣጣ እንዲሁም ከሩሲያና የአፍሪካ ህብረት ምርጫውን የሚታዘቡ ባለሙያዎች ይመጣሉ ብለዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ