ከሁለት ሳምንት በፊት የ 12 ዓመቱ ታዳጊ ጆሽዋ ኃይለ ኢየሱስ በኮሎራዶ ሕፃናት ሆስፒታል ውስጥ ከፍተኛ እርዳታ ቢደረግለትም ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም ።
ጆሽዋ ኃይለ ኢየሱስ በቲክቶክ የተሰራጨ ‘ብላክ አውት ቻሌንጅ ‘ ላይ በመሳተፉ ነበር ሕይወቱ ሊያልፍ የቻለው። ጨዋታው ራስን ለተወሰኑ ጥቂት ደቂቃዎች ሳይተነፍሱ በማቆየት የሚደረግ ፉክክር ነው። በዚህ የቲክ ቶክ ፉክክር ላይ ራስን አንቆ ደምና አየር እና እንዳይተላለፍ በማድረግ ለጥቂት ደቂቃዎች ራስን ከሳቱ በኋላ የመንቃት ውድድር ላይ ሲሳተፍ ራሱን ስለሳተ ሆስፒታል የተወሰደ ቢሆንም ሕይወቱን ማትረፍ ግን አልተቻለም ነበር።
ይህም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። እኛም ይህንን መሰረት በማድረግ ልጆች የማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም አለባቸው? ከተጠቀሙስ እንዴት መሆን አለበት የቤተሰብ ክትትልስ ምን መሆን ይገባዋል? የሚለውን የሕጻናት ስነልቦና ባለሙያ የሆኑትን ቴዎድሮስ ጌቴን አጋግረናል።
ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ ማህበራዊ ሚዲያ ለአዋቂዎችም ቢሆን መጥፎም ጥሩም ሊሆን ይችላሉ። የሚወስነው ግን አጠቃቀም ላይ ነው። ይኹን እንጂ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ብቸኝነት ሲሰማቸው ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ሃሳብ ለመለዋወጥ እንዲሁም ትስስር ለመፍጠር፣ ማህበራዊ ሚዲያን ሊጠቀሙ ይችላሉ ይህም በበጎ ጎኑ መታየት ይኖርበታል ብለዋል።
ሆኖም ግን፣ እነዚህ ልጆች የአእምሮ እድገታቸው እና የሚነገራቸውን ነገር የሚቀበሉበት መንገድ በምክንያት እና ውጤት የተደገፈ ስላልሆነ በጥንቃቄ ሊታዩ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። በዚህም መሰረት የማህበራዊ ሚዲያው ያለው ተጽዕኖ ትልቅና ከሚታሰበው በላይ መሆኑን ባለሙያው ያብራራሉ።
ለምሳሌ ይላሉ አቶ ቴዎድሮስ፣ “አንድ ቲክቶክ ላይ ያለ ተጠቃሚ አንድ ድርጊት እየፈፀመ የሚያሳይ ቪዲዮ ቢለጥፍ፣ በዚህ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች እኔ ይህ አያቅተኝም፤ እችለዋለሁ፤ በሚል ድርጊቱን መድገም ይጀምራሉ። ምክንያቱም ይህ እድሜያቸው ሁሉን እንደሚችሉ የሚያምኑበት ጊዜ በመሆኑ ነው።”
የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቻቸው፣ በእውነት ከእነርሱ ጋር እንዳሉ የሚያስቡበት “በምክንያትና ውጤት ከሚያምነው የአእምሮ ክፍላቸው ይልቅ ‘ኢጎ’ የሚባለው በስሜት የሚያምኑበት እና ድርጊት የሚፈጽሙበት ጊዜ ይበዛል። በተጨማሪም ይህ ጊዜ እኔ ማን ነኝ? ማለት የሚጀምሩበት እና ጉርምስና ውስጥ እያለፉ ያሉበት ወቅት ነው። በዚህም ተጽዕኖ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፉት ነገር ብዙ ላይክ እንዳገኘ ለማሳየት ይፈልጋሉ በዚያም መጠን ተከታዮቻቸውን ለማብዛት ይጥራሉ።”
ስለዚህ እነዚህ ልጆች የለጠፉት ነገር ምን ያህል ተወደደልኝ ወይንም ደግሞ ምን ያህል ሰዎች ተጋሩልኝ የሚለው እንጂ ምን ዓይነት አደጋ አለው የሚለውን ለመረዳት እንደሚከብዳቸው ይገልጻሉ።

የፎቶው ባለመብት,VYSTEKIMAGES
መወደድ በማህበራዊ ሚዲያ መንደር
ልጆች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የለጠፉት ነገር በበርካቶች ከተወደደላቸው፣ ከዚህ በላይ ምን ብለጥፍ ተወዳጅነት ያመጣልኛል በሚል ስለ ራሳቸው ሳይሆን ተከታዮቻቸው ይወዱታል ብለው ስለሚያስቡት ነገር በመጨነቅ ይለጥፋሉ ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የሚለጥፉት ነገር የማይወደድ ከሆነ እና ጥሩ ምላሽ ከሌላው ጥያቄ ያጭርባቸዋል።
ምክንያቱም እነዚህ ታዳጊዎች የሚሰጣቸውን አስተያየት የሚመዝኑበት እድሜ ላይ አይደሉም። ይህም ለውጥረት እና ድባቴ ያጋልጣቸዋል። “በአይናቸው አይተዋቸው የማያውቋቸው፤ በሚሰጧቸው አስተያየት ራሳቸውን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የሚያስገቡበት ጊዜ ቀላል አይደለም።” ይላሉ እኚህ የሕጻናት ስነልቦና ባለሙያ።
የውጪ አገራት መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ ራስን በመጥላት ሕይወታቸውን በገዛ እጃቸው ማጥፋት ላይ የሚደርሱ ታዳጊዎች በርካታ ናቸው። በአገራችንም ከተሞች አካባቢ ይህ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እና አስጊ እየሆነ መጥቷል በማለት የዚህን ጉዳይ አሳሳቢነት ይገልጻሉ።
ከራሳቸው ተሞክሮ ሲናገሩም፣ ለራሳቸው ቅርብ ከሆኑ ሰዎች አንስቶ በሥራ ምክንያት ስላናገሯቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ ማህበራዊ ሚዲያው እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ እንዲህ ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት,SDI PRODUCTIONS
“ተማሪዎች፣ ክፍል ውስጥ ተቀምጠው ፌስቡክ አልያም ኢንስታግራም ላይ ስሚለጥፉት ፎቶ እንደሚያስቡ፣ አንድ ታዳጊ ፎቶ ለጥፎ ብዙ ተከታዮች ካላገኘ እና ሌሎች ካገኙ በተቃራኒው መጨነቅ መኖሩን ያስረዳሉ።
ቤተሰብ ምን ያድርግ?
አቶ ቴዎድሮስ በዚህ ዘመን ቤተሰብ ያስተዳደር ዘዬ መቀየር ወይንም ማሻሻል ይኖርበታል ይላሉ። “ልጆች ከማህበራዊ ሚዲያ መማር ስለሚችሉ እድሉ ሊሰጣቸው ይገባል። ለምሳሌ ልጆች ከዩቲዩብላይ ምግብ መስራት የተለያዩ የእጅ ስራዎችን እንዲማሩ እና ክህሎቶቻቸውን ሊያሳድጉ ይችላሉ። ሆኖም ይህ በቤተሰብ ቁጥጥር ስር መሆን አለበት።”
አቶ ቴዎድሮስ ብዙ ቤተሰቦች መካከል በአሁኑ ጊዜ የሚስተዋለው ግን ከዚህ የተለየ መሆኑን ሲያስረዱም ” ልጆች ኢንተርኔት ካገኙ ስለማያስቸግሩ፣ ጥያቄ ስለማይጠይቁ ይህን አድርጉ ያንን አድርጉልኝ ስለማይሉ በዘፈቀደ ይለቅቋቸዋል” ብለዋል።
ስለዚህ ቤተሰብ ለልጆቹ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ሲሰጥ፡
- እቅድ በማውጣት የልጆችን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መገደብ፤
- ምን እንደሚጠቀሙ ማወቅና መከታተል፤
- ከልጆች ጋር በግልጽ መነጋገር፤
- ለልጆች የተፈቀዱ መተግበሪያዎችን በመስጠት ቀሪዎቹን መዝጋት፤
- ቴክኖሎጂው እያደገ በሚመጣበት ጊዜ ደግሞ የልጆችን ስልክ ከራሳቸው ጋር በማገናኘትም መከታተል ይችላሉ ብለዋል።
እኚህ የስነልቦና ባለሙያ “ቤተሰብ ልጆቻቸውን ከመረዳት እና ከማቅረብ ይልቅ እንዲሁ ከፈረዱባቸው የሚያደርጉትን ደብቀው ስለሚፈጽሙ ለአደጋ መጋለጣቸው አይቀርም” በማለት ቤተሰብ ልጆቻቸውን ማቅረብና በግልጽ መነጋገርን ይመክራሉ።