የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ከቀረበለት ዕርምጃ ወስዳለሁ ብሏል
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች የታሰሩ ሰዎች ተገደው ወታደራዊ ዩኒፎርም በመልበስና መሣሪያ በመታጠቅ ቪዲዮ እንደሚቀረፁ፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።
ኮሚሽኑ አክሎም በኦሮሚያ ክልል ክትትል ባደረገባቸው የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ‹‹የኦነግ ሸኔ›› አባል ወይም ደጋፊ ‹‹ልጆቻችሁን አቅርቡ›› ተብለው እናቶችን የማሰር፣ በተመሳሳይም ‹‹ባልሽን አቅርቢ›› በማለት ሚስትን የማሰር ድርጊት እንደሚፈጸም፣ ከተለያዩ ታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነቶችን እንደተቀበለ ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት አስታውቋል።
ሕወሓትና ‹‹ሸኔ›› የተባሉት ሁለት ድርጅቶች በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ተወያይቶ ውሳኔ መሳለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ በውይይቱ ወቅት ሸኔ ማነው የሚል ጥያቄ በአንድ የምክር ቤቱ አባል ተነስቶ ምለሽ እንደተሰጠበትም አይዘነጋም።
ለተነሳው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የፈዴራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሆኑት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሸኔ›› በሚል መጠሪያ የቀረበው ድርጅት በተለምዶ ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የሚባለው ወይም ራሱን ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት›› በማለት የሚጠራው ድርጅት መሆኑን አስረድተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሓትና ‹‹ሸኔ›› የተባሉት ድርጅቶች በአሸባሪነት እንዲፈረጁ በወሰነበት በዚሁ ቀን፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበርን አስመልክቶ ምክር ቤቱ ለሚያደርገው ክትትል ድጋፍ የሚሰጠውና ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በተመረጡ 21 ፖሊስ ጣቢያዎች ያለውን የእስረኞች አያያዝ የተመለከተ የክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
የኮሚሽኑ ሪፖርት ክትትል በተደረገባቸው የተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ‹‹ኦነግ ሸኔ›› በሚል ምክንያት ያልተገባ እስርና ጥሰት መፈጸሙን ያመለክታል። ኮሚሽኑ ክትትል ካደረገባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች መካከል በሦስቱ ማለትም በገደብ አሳሳ፣ በዶዶላና በአዳባ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የነበሩ በድምሩ አሥር ተጠርጣሪዎች ያለ ፍላጎታቸው ወደ ሻሸመኔ ከተማ ተወስደው የተፈጸመውን ጥሰት በሪፖርቱ አስፍሯል።
ከተገለጹት የፖሊስ ጣቢያዎች በድምሩ አሥር ተጠርጣሪዎች ያለ ፍላጎታቸው ወደ ሻሸመኔ ከተማ ከተወሰዱ በኋላ፣ ‹‹የታጣቂ ወይም የወታደር ልብስ እንዲለብሱ፣ አርቲፊሻል ፀጉር እንዲያደርጉና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን እንዲይዙ ተደርገው፣ ከዚያ በፊት ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር በቪዲዮ ካሜራ መቀረፃቸውን ለኮሚሽኑ ተናግረዋል፤›› በማለት በሪፖርቱ ይገልጻል።
ይህንን ቅሬታ በተመለከተ ስለሁኔታው የሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች በኮሚሽኑ የክትትል ቡድን ተጠይቀው እስረኞቹ ወደ ሻሸመኔ መወሰዳቸውን ያረጋገጡ ቢሆንም፣ በካሜራ ስለመቀረፃቸው እንደማያውቁ መናገራቸውን ሪፖርቱ ይጠቅሳል።የአንድ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ ቪዲዮ መቀረፃቸውን ያመኑ ቢሆንም፣ የተቀረፁት ግን የጦር መሣሪያ በመያዝ ሳይሆን፣ ቀደም ሲል በሌላ ቦታ ወንጀል ፈጽመው አሁን ወደሚገኙበት ወረዳ የመጡ በመሆናቸው በፊት ከነበሩበት ወረዳ ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ በማገናኘት መረጃ ለመሰብሰብ እንደሆነ መግለጻቸውን ያትታል።
የኮሚሽኑ የክትትል ቡድን በተወሰኑ ቦታዎች ‹‹የኦነግ ሸኔ›› አባል ወይም ደጋፊ በመሆናቸው በሕግ እንደሚፈለጉ በመግለጽ፣ ‹‹ልጆቻችሁን አቅርቡ›› የተባሉ እናቶችና አባት ታስረው ማግኘታቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል።በተመሳሳይ የኦነግ ሸኔ አባል ነው በማለት ‹‹ባልሽን አቅርቢ›› የተባለች የተጠርጣሪ ባለቤት መታሰሯንና መሰል ተገቢ ያልሆነ ሰዎችን የማሰር ድርጊት እንደሚፈጸም፣ ከተለያዩ ታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነቶችን እንደተቀበለ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል።
ኮሚሽኑ በማከልም፣ በተለያዩ ቦታዎች ሰዎችን ያላግባብ ማሰርና ‹‹የኦነግ ሸኔ አባል ናችሁ ብለን እንከሳችኋለን›› በማለት በማስፈራራት ገንዘብ የመጠየቅ ሁኔታዎች መኖራቸውን፣ ከተለያዩ እስረኞች መስማቱን ገልጿል።ሆኖም የክትትል ቡድኑ ‹‹በኦነግ ሸኔ›› በማስፈራራት ገንዘብ መቀበልን አስመልክቶ ከሌላ ገለልተኛ ወገን በማስረጃ ማረጋገጥ አለመቻሉን ሪፖርቱ ይጠቁማል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት በሰጠው ምላሽ ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያስችል ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት መኖሩን በማመልከት፣ ቅሬታው ‹‹ከእውነት የራቀ›› እንደሆነና ያም ሆኖ ቅሬታዎቹ በማስረጃ ተደግፈው ከቀረቡ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለሕግ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ለኮሚሽኑ መግለጹን ሪፖርቱ ይጠቁማል።
የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ በክልሉ ያለው የእስረኞች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻ ነው ብለዋል።ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ምርመራቸው እንዲፋጠንና ፍርድ ቤት ቀርበው ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲያገኙ እንዲደረግ፣ በእስረኞች ላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ለሕፃናትና ለሴቶች ተጠርጣሪዎች ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በተለይም በወንጀል ነክ ጉዳዮች ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሕፃናት በሕጉ መሠረት በአፋጣኝ በዋስ እንዲለቀቁ አሳስበዋል።በክልሉ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሚገኙ ግለሰቦች በወቅታዊ ሁኔታ በሚል የተሳሩ መሆናቸውን ይህም ማለት ከኦነግ ሸኔ በተገናኘ፣ ለሕወሓት ድጋፍ በማድረግና ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተገናኘ መሆኑን መረዳት እንደቻለ የኮሚሽኑ ሪፖርት ያስረዳል።
በወቅታዊ ጉዳይ በሚል ምክንያት የታሰሩ ሰዎችን ጉዳይ የሚታየው በየዞኑ በተደራጁ የፀጥታ ምክር ቤቶች እንደሆነ ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ ይህ ምክር ቤት የሚሰጠውን ውሳኔ ፍርድ ቤቶች ጭምር ማክበር እንደሚጠበቅባቸው ሪፖርቱ ያመለክታል።
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ዳኝነት ጉዳይ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን በተሰጣቸው ፍርድ ቤቶች ብቻ እንዲታዩ ማድረግና የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ ማክበር ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፤›› ሲሉ አሳስበዋል።
ምንጭ – ሪፖርተር