ኮሮናቫይረስን በሚመለከት የሚለቀቁ የሴራ ትንተና፣ የተሳሳተ መረጃ እና መላ ምቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙዎች ሲያጋሯቸው ይስተዋላል። ነገር ግን እነዚህን መረጃዎች የሚያመነጨው ማነው? የሚያሰራጨውስ?

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በብዛት የተሰራጩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አሳሳች መረጃዎችን ተመልክተናል። ይህም እነዚህን መረጃዎች ማን እንደሚያሰራጫቸው መነሻ ሀሳብ ሰጥቷል። ምን እንደሚያነሳሳቸውም ያሳያል። ከዚህ በታች የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያስጀምሩ እና የሚያሰራጩ ሰባት አይነት ሰዎችን ተለይተዋል።

ቀልደኞች

በአንድ ወቅት የእንግሊዝ መንግሥት ዌምብሌይ ስታዲየም ውስጥ የለንደን ነዋሪዎችን ለመመገብ ላዛኛ እያበሰለ ነው የሚል መረጃ ሲለቀቅ በርካቶች እንደቀልድ እንኳን አልወሰዱትም ነበር። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አንድ ግለሰብ መንግሥት ያስቀመጣቸውን ገደቦች በመጣስ ከቤቱ ብዙ ጊዜ በመውጣቱ ተቀጣ የሚል መረጃና ለማሳመኛ ደግሞ የሐሰት ምስል ተጠቅሞ ነበር። እሱ እንደሚለው ይህ መረጃ ሰዎች ከቤት መውጣት እንዲፈሩ ያደርጋል በሚል ነበር።

ኢንስታግራም በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚከተሉትን ሰዎች ይህንን መረጃ እንዲያጋሩ የጠየቀ ሲሆን መረጃው ግን ከኢንስታግራም አልፎ በፌስቡክም በርካቶች ሲጋሩት ነበር። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎችም መረጃውን እውነት አድርገው ወስደውት ነበር። “በሰዎች ዘንድ ድንጋጤ መፍጠር አልፈልግም” ይላል መረጃውን መጀመሪያ ላይ ያጋራው ግለሰብ። ስሙን ግን መናገር አልፈለገም። “ነገር ግን እነዚህ ሰዎች እውነተኛ ያልሆነውን ምስል መለየት ካልቻሉ ከበይነ መረብ መረጃ የሚያገኘበትን መንገድ በደንብ መመርመር አለባቸው” ብሏል።

ቀልደኞች

“አጭበርባሪዎች

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በርካታ አጭበርባሪዎች ከመንግሥት የሚላኩ በማስመሰል የተለያዩ የጽሁፍ መልዕክቶችን ለዜጎች ሲልኩ ነበር። ዋነኛ ዓላማቸው ደግሞ ሰዎችን አሳስቶ ገንዘብ ማግኘት ነው። ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ አንድ መረጃ አጣሪ ቡድን ባደረገው ምርመራ መሰረት አንድ አጭበርባሪ መንግሥት ለዜጎች ድጎማ ለማድረግ ስላሰበ የባንክ መረጃችሁን ላኩ የሚል የጽሁፍ መልዕክት ሲልክ ነበር።

የአጭበርባሪው የጽሁፍ መልዕክት በፌስቡክ በርካቶች ተጋርተውታል። ይህ መልዕክት ለዜጎች ሲላክ የነበረው የጽሁፍ መልዕክትን በመጠቀም ስለነበር ከጀርባው ማን እንዳለ ለማወቅ አስጋቸሪ ነበር። ከጥቅምት ወር ጀምሮ ደግሞ አጭበርባሪዎች በተለያዩ መንገዶች ገንዘብ ለማግኘት ስለኮሮናቫይረስ የተሳሳቱ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ነበር። አንዳንዶቹ ኢሜል በመጠቀም ሰዎች ስለ ክትባቱ ለማወቅ ከፈለጋችሁ ይህንን ተጫኑ በማለት የሰዎችን የባንክ መረጃ ለማግኘት ሞክረዋል።

በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ መንግሥት በወረርሽኙ ምክንያት በየወሩ የሚወስደውን ግብር አቋርጧል፤ ከዚህ በፊት የተቆረጠባችሁ እንዲመለስላችሁ ከፈለጋችሁ የባንክ መረጃችሁን ንገሩን የሚሉ አጭበርባሪዎችም አልጠፉም።

አጭበርባሪዎች

ፖለቲከኞች

ስለኮሮናቫይረስ እና ስለክትባቱ የተሳሳቱና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከበይነ መረብ ጀርባ ተደብቀው ከሚያሰራጩ ብቻ የሚመጣ አይደለም። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ግንቦት ወር ላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ፀሐይ ላይ ማሞቅ አልያም ኬሚካሎችን መውጋት ከበሽታው እንዲድኑ ሊያደርጋቸው ይችል ይሆን ብለው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በኋላ ላይ የሰጡት አስተያየት እንደ ቀልድ እንደሆነ ገልጸዋል። ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ይህንን ግምታቸውን ከተናገሩ በኋላ በርካታ ሰዎች ወደ መረጃ ማዕከላት በመደወል እራሳቸውን በተመሳሳይ መንገድ ከበሽታው ማዳን ይችሉ እንደሆነ ሲጠይቁ ነበር።

መሰል መረጃዎችን ያሰራጩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ብቻ አይደሉም። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ የኮሮናቫይረስ መጀመሪያ ላይ ወደ ዉሃን ከተማ የመጣው ምናልባት “በአሜሪካ ወታደሮች ሊሆን ይችላል” ብለው ነበር።

የሩሲያው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ደግሞ ስለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተለያዩ የሴራ ትንተናዎችን ሲያደርግ የነበረ ሲሆን የክሬምሊን ደጋፊ የሆኑ የትዊተር ገጾችም ቢሆኑ ተመሳሳይ መረጃ ሲያሰራጩ ነበር። በአሜሪካ አሪዞና ግዛት የዓሳ ገንዳ ማጽጃ ኬሚካል ኮሮናቫይረስን ይፈውሳል የሚል ዜና ያነበቡ ጥንዶች ኬሚካሉን ጠጥተው ሆስፒታል ገብተዋል። ለዚህ አንዱ ተጠያቂ የሚሆኑት እንደመጣላቸው ይናገራሉ የሚባሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሳይሆኑ አይቀሩም።

ፖለቲከኞች

የሴራ ተንታኞች

ስለኮሮናቫይረስ ባለሙያዎቹ እንኳን እርግጠኛ መረጃ መስጠት አለመቻላቸው የሴራ ትንታኔ ለሚሰጡ ሰዎች አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። ለምሳሌም በሴራ ላይ በተመሰረተ የተሳሳተ መረጃ ምክንያት በዩናይትድ ኪንግደም 70 የሚሆኑ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ማማዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ 5ጂ ቴክኖሎጂ ነው ቫይረሱን ያመጣው የሚለው ወሬ ነው።

ዩጎቭ እና ዘ ኢኮኖሚስት ባለፈው ወር ባደረጉት አንድ ጥናት እንዳመለከቱት 13 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውሸት ነው ብለው ያምናሉ። 49 በመቶዎቹ ደግሞ ሰው ሰራሽ ሊሆን ይችላል ብለዋል። በአንድ ወቅት ደግሞ እንግሊዝ ውስጥ የክትባት ሙከራ ላይ አንድ በጎ ፈቃደኛ በሂደቱ ላይ ህይወቱ አልፏል የሚል መረጃ ተሰራጭቶ ነበር። በዚህ ምክንያት ክትባቱ ሰዎችን ለመግደል የተሰራ ነው የሚል የሴራ ትንታኔ ተሰራጭቶ ነበር።

የሬዲዮ ሞገዶችን በመጠቀም ለሞባይል ስልክ አገልግሎት የሚውለውን የ5ጂ ቴክኖሎጂ በስፋት እየተሰራጨ ላለው የኮሮናቫይረስ ተጠያቂ በማድረግ ይህንን ሐሰተኛ መረጃ በስፋት እያሰራጩ ያሉት ሰዎች የሴራ ንድፈ ሐሳብን መሰረት አድርገው ነው። ይህ ወሬ መሰራጨት የጀመረው በጥር ወር መጨረሻ አካባቢ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ታማሚ አሜሪካ ውስጥ በተገኘበት ሰሞን ሲሆን፤ ክስተቱ ከ5ጂ ኔትወርክ ጋር ግንኙነት እንዳለው በፌስቡክ በኩል ሲወራ ነበረ።

የሚሰራጨውም ወሬ ሁለት ገጽታ የነበረው ሲሆን አንደኛው 5ጂ የተፈጥሮ በሽታን የመከላከያ አቅምን በመቀነስ ሰዎችን ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ያደርጋል የሚሉ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ቫይረሱ በቀጥታ በ5ጂ ቴክኖሎጂ በኩል ይተላለፋል ሲሉ ያልተረጋገጡ መልዕክቶችን በስፋት አሰራጭተዋል።

የሴራ ተንታኞች

“ውስጥ አዋቂዎች”

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ስለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተሳሳተ መረጃ የሚመጣው ታማኝ ከሆኑ ምንጮች ነው። ለምሳሌ ዶክተሮች፣ መምህራን አልያም የጤና ማዕከላት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ተናገሩት እየተባለ የተሳሳተ ወሬ ይዛመታል። በአንድ ወቅት እንግሊዝ ውስጥ አንዲት የአምቡላንስ ሠራተኛ ተናገረችው ተብሎ “ወጣቶች በብዛት እየሞቱ ነው” የሚል የድምጽ መልዕክት ተሰራጭቶ ነበር።

ቢቢሲ ይህንን የድምጽ መልዕክት አስተላልፋለች የተባለችውን ሴት ለማነጋገር ቢሞክርም የእውነትም የጤና ሠራተኛ መሆኗን ማረጋገጥ አልቻለም። ነገር ግን መረጃው ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው ብሎ መደምደምም ይከብዳል።

ውስጥ አዋቂዎች

“ዘመዶች

ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለቤተሰቦቻቸው አልያም ስለወዳጆቻቸው ሲያስቡ ይጨነቃሉ። በተለይ ደግሞ በዚህ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን በሚያስጨንቅበት ወቅት። እናም አንዳንድ ሰዎች ጠቃሚ ነው ብለው የሚያስቡን መረጃ ለቤተሰብና ወጃጆቻቸው ያገራሉ። መረጃ ማጋራቱ በራሱ መጥፎ ባይሆንም መረጃው ግን ምን ያህል ተአማኒና እውነተኛ ነው የሚለውን ሳያጣሩ ለሌሎች ማጋራት አደገኛ ውጤትን ሊያስከትል ይችላል።

እንግሊዛዊቷ ዳኒኤል ቤከር የዚህ ጉዳይ ሰለባ ነበረች። በአንድ ወቅት ፌስቡክ ላይ ያገኘችውን መረጃ ምናልባት እውነት ከሆነ በማለት ለብዙ ሰዎች አጋርታ ነበር። “መጀመሪያ ላይ ትንሽ አሳስቦኝ ነበር። ምክንያቱም እምብዛም ከማላውቃት ሴት ነበር መልዕክቱ የተላከልኝ” ትላለች። “መልዕክቱ ጠቃሚ ስለመሰለኝ ልጅ ላላት እህቴ ላኩላት።” እነዚህ ሰዎች የሚያገኙትን መረጃ ለሚወዷቸው ሰዎች ለማጋራት መቸኮላቸው የሚያስገርም አይደለም። ነገር ግን ሁሉም የሚባለው ነገር ግን እውነት ነው ማለት አይደለም።

ዘመዶች

ታዋቂ ሰዎች

ኮሮናቫይረስን በተመለከተ የተሳሳቱ እና እውነት ላይ መሰረት ያላደረጉ መረጃዎችን ከሚያሰራጩ ሰዎች መካከል የምናደንቃቸውና የምንወዳቸው ሰዎችም ጭምር ይገኙበታል። ብዙ ጊዜ በይነ መረብ ላይ የሚያገኙትን መረጃ ማጋራት የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን በርካታ ተከታዮች ያላቿው ሰዎች እንዲህ አይነት ነገሮች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ምክንያቱም አንድ ተራ ሰው የተሳሳተውን መረጃ ሲያጋራና ታዋቂ ሰዎች ሲያጋሩት መልዕክቱ የሚያገኘው ተቀባይነት ተመሳሳይ አይደለም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በቅርቡ በሰራው አንድ ጥናት መሰረት በመላው ዓለም ከሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ጀርባ የታዋቂ ሰዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አሳይቷል። የሞባይል ስልክ አገልግሎትን ፈጣንና ዘመናዊ ያደርገዋል ተብሎ የታመነበት የአምስተኛው ትውልድ [5ጂ] ቴክኖሎጂ የኮሮናቫይረስን እያሰራጨ ነው በሚል በተናፈሰው ወሬ ላይ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ነበሩበት።

አዲሱ ቴክኖሎጂ በሽታውን እያስተላላፈ ነው የሚሉ መላምቶችን የያዙ መልዕክቶች ዕውቅና ባገኙና በመቶ ሺህዎች ተከታይ ባሏቸው የፌስቡክ፣ የዩቲዩብና የኢንስታግራም አካውቶች በኩል ሳይቀር በስፋት ሲሰራጩ ነበር። ነገር ግን ሳይንቲስቶች ይህ በኮቪድ-19 እና በ5ጂ አገልግሎት መካከል አለ የተባለው ግንኙነት “ፍጹም የማይረባ” ከመሆኑ በተጨማሪ ከሥነ ፍጥረት እሳቤ አኳያም ሊሆን የማይችል ነው ብለዋል።

አሁንም ድረስ ኮሮናቫይረስ አውሮፓውያን የሸረቡት ሴራ እንጂ እውነት አይደለም ብለው የሚያምኑ ሺህዎች ናቸው። አሁንም ድረስ ኮሮናቫይረስን የወለደው 5ጂ ኔትወርክ ነው የሚሉ አሉ። አሁንም ድረስ ‘አልኮል ኮሮናቫይረስን ድራሹን ያጠፈዋል’ ብለው ጉሮሯቸው እስኪሰነጠቅ የሚጨልጡ በርካቶች ናቸው። ከኢትዮጵያ እስከ ማዳጋስካር፣ ከታይላንድ እስከ ብራዚል፣ ከአሜሪካ እስከ ታንዛኒያ በሐሳዊ ወሬ ያልናወዘ፣ መድኃኒት ያልጠመቀ የለም።

ሳይንስ መፍትሔ የለውም ብለው ከደመደሙት ጀምሮ አምላክ ያመጣው መቅሰፍት ነው ራሱ ይመልሰው ብለው ሕይወታቸውን በተለመደው መልኩ የቀጠሉ የዓለም ሕዝቦች ብዙ ናቸው።

ታዋቂ ሰዎች

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *