በሱዳን የነበራቸውን ግዳጅ የጨረሱ 120 ኢትዮጵያውያን የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት ወደ አገራችን አንመለስም አሉ።

የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላቱ ዓለም አቀፍ ጥበቃ እና በሱዳን ጥገኝነት መጠየቃቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። የሠላም አስከባሪ አባላቱ በቅርቡ በተጠናቀቀው የተባበሩት መንግስታት የዳርፉር ተልዕኮ አካል ነበሩ።

በተመሳሳይ ከወራት በፊት 15 በደቡብ ሱዳን የነበራቸውን ግዳጅ የጨረሱ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም ማለታቸው ይታወሳል። አገር መከላከያ ሠራዊት ወደ አገር ቤት አንመለስም ያሉት “የጁንታው ተላላኪዎች” ናቸው ብሎ ነበር።

አሁን ላይ ወደ አገራችን አንመለስም ያሉት 120 የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት የትግራይ ተወላጆች ስለመሆናቸው ተመድ ያለው ነገር የለም።

ስለ ሠላም አስከባሪ ኃይሎቹ ምን ተባለ?

በዳርፉር አካባቢ ተልዕኳቸው የተጠናቀቀ 120 የሠላም አስከባሪ ኃይሎች ወደ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ በሱዳን ጥገኝነት ጠይቀዋል ብሏል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት። ለዚህ ምክንያቱ በሰሜን ትግራይ ክልል የተፈጠረው ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱት ውጥረቶች ጋር የተቆራኘ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

ኤፒ የዜና ወኪል በበኩሉ ወደ አገራችን አንመለስም ካሉ የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት መካከል ከ30 በላይ የሚሆኑት ወደ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን የሱዳን ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል። የሰሜን ዳርፉር ግዛት የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ የሆኑት አል-ፋቴህ ኢብራሂም ሞሐመድ ወደ መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ ከተደረጉት መካከል ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ፍቃደኛ ያልሆኑት ይገኙበታል ብለዋል።

የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ክስ ይጠብቀናል በሚል ፍራቻ ለመመለስ ፈቃደኛ ካልሆኑት መካከል 14ቱ ሴት የሠላም አስከባሪ አባላት ናቸው ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃክ ባለፈው ወር ለኤፒ እንደገለጹት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አገራቸው እየተመለሱ መሆኑን ተከትሎ በድርጅቱ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ስር የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን “ዓለም አቀፍ ጥበቃን እየጠየቁ” ነው።

የሱዳን የስደተኞች ኃላፊው ሞሐመድ በበኩላቸው ሱዳን እሁድ በትንሹ 33 የሠላም አስከባሪ ኃይሎችን ከሰሜን ዳርፉር ግዛት በማስወጣት ኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ወደሚገኘው ምስራቃዊው የካሳላ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ አስገብታለች ብለዋል። ተጨማሪ 31 ሌሎች የሠላም አስከባሪ ኃይሎች ሰኞ ከሰሜን ዳርፉር ይወጣሉ ብለዋል። በዚህም የሠላም አስከባሪ ኃይሎቹ ከትግራይ ግጭት ሸሽተው ወደ ጎረቤት ሱዳን የተሰደዱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ይቀላቀላሉ።

ቀደም ሲል አንመለስም ስላሉት የሠላም አስከባሪ አባላት ምን ተባለ?

ከወራት በፊት 15 የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ አባላት ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አንፈልግም ማለታቸውን መዘገቡ ይታወሳል። እንደ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ከሆነ ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሠላም ማስከበር ላይ ተሰማርተው የነበሩ 169 ወታደሮች በሌሎች ተተክተው ወደ አዲስ አበባ መመለስ ነበረባቸው። ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደማይፈልጉ ያሳወቁት 15ቱ የሠላም አስከባሪው ኃይል አባላት የትግራይ ተወላጅ መሆናቸውም ተገልጿል።

ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፌስቡክ ገጽ የሠራዊቱን የኢንዶክትርኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ተሰማን በመጥቀስ ባወጣው ዜና ወደ አገር አንመለስም ያሉት የ15ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ አባላት መሆናቸውን አመልክቷል።

እንደሜጀር ጀነራል ተሰማ ከሆነ ሻለቃው በደቡብ ሱዳን የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ለተተኪው ኃይል ኃላፊነቱን በማስረከብ በመመለስ ላይ እንዳለ አስራ አምስት የሠራዊቱ አባላት ወደ አገር ቤት አንመለስም ብለዋል። “የጁንታው ተላላኪዎች ወደ አገራችን አንሄድም በማለት ጁባ አየር ማረፊያ ላይ በመንከባለልና በመጮህ ሁከት ለመፍጠር ሞክረዋል” ሲሉ ሜጀር ጀኔራል መሐመድ በወቅቱ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ግዳጅ አኩሪ ተግባር እየፈፀመ እንደሚገኝ በመግለጽ በግለሰቦቹ የተፈጸመው ድርጊት “የሠራዊቱን አባላት የማይወክል አሳፋሪ ተግባር” መሆኑን ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ ገልጸው ነበር።

የዳርፉር ሠላም ማስከበር ተልዕኮ

በተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ስር ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮችንና የፖሊስ ኃይል ያሰማራችበት የዳርፉር ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ከወራት በፊት ተጠናቋል። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ስር በተለያዩ አገራት ውስጥ ለሚደረጉ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ የሚባለውን ከ8,300 በላይ ሠራዊት ታበረክታለች። ከእዚህም ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው በሱዳን ውስጥ በሚገኙት ዳርፉርና በአብዬ ግዛት ውስጥ የተሰማሩ ናቸው።

ዩናሚድ በሚባል የአንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል የሚታወቀው የዳርፉር ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች ካበረከቱ ቀዳሚ ሦሰት አገራት አንዷ ናት። በምዕራባዊ ሱዳን ለ13 ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት ሠላም ለማስከበር ተሰማርቶ ለቆየው ሠራዊት በርካታ የዓለም አገራት ወታደሮቻቸውን አዋጥተዋል ከእነዚህም ውስጥ በርካታ የሠራዊቱ አባላትን በማበርከት ሩዋንዳ፣ ፓኪስታንና ኢትዮጵያ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

በምጽሀረ ቃል ‘ዩናሚድ’ (UNAMID) ተብሎ የሚታወቀው በዳርፉር ሰላም ለማስከበር የተሰማራው ኃይል ከዚህ በኋላ በሱዳን እንደማይቀጥል የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ በሱዳን እና በዳርፉር ያለውን አንጻራዊ ሰላም፣ የሽግግር መንግሥቱ ከአማጺያን ጋር ያደረጋቸውን የሰላም ስምምነቶች እንዲሁም አጠቃላይ ለውጦችን ከግምት በማስገባት እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *