ጋዜጠኞች ለሰላም ማስከበር፣ ለሰላም  ግንባታ እና ሰላም  መፍጠር እንዴት ሊያግዙ እንደሚችሉ ፥ ክፍል 2

2.2 ጋዜጠኞች የተለያዩ ወገኖች ግጭቶችን ለመቆጣጠር እና ለመፍታት የሚያስችሉ ብልሕ ውሳኔዎችን  ማሳለፍ የሚያስችሉ መረጃዎችን ሊሰጡ ይችላሉ

በግጭት ጊዜያት ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ብልሕ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እንዲችሉ በዘገባችን ላይ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ጋዜጠኞች የምንጫወታቸው ቢያንስ ሁለት ወሳኝ ሚናዎች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በግጭት ላይ ያሉ ወገኖች በቀላሉ ሊያውቋቸው የማይችሉ በርካታ ግጭቶች በመኖራቸው ውሳኔዎችን ለማሳለፍ በቂ መረጃ የላቸውም። ከግጭት በስተጀርባ ያለውን ታሪክ ባለመረዳት አንድ ወገን ስለ አንድ ጉዳይ ለምን የጠነከረ ስሜት እንደሚሰማው ግንዛቤ አይኖራቸውም።

ብዙ ትልልቅ ግጭቶች ውስጥ ያሉ ቡድኖች አንደኛቸው ሌላኛቸው መረጃ እጥረት አለባቸው፣ አልያም የግጭቱን አስኳል በተመላከተ በቂ መረጃ የላቸውም። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የተገናዘበ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችላቸውን ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ጠቃሚ ሚና መጫወት እንችላለን። ሰዎች አንድ ወገን በተሳሳተ መንገድ የተረዳው ነገር እንዳለ ወይም ባልተሟላ መረጃ ላይ በመንተራስ እርምጃ እየወሰደ እንዳለ እንዲገነዘቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በዚህ መንገድ ጋዜጠኞች እነዚህን የመረጃ ክፍተቶች ለመሙላት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

ጋዜጠኞች የኅብረተሰቡን የመረጃ ፍላጎቶች በመገምገም ከእነዚህ ፍላጎቶች ውስጥ የተወሰኑትን ለማሟላት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ምርጫን እና ከመራጮችን ምዝገባ ጋር የተያያዘ ምሳሌ ልናነሳ እንችላለን። በአግባቡ ምዝገባ ያላከናወኑ ሰዎች ከምርጫው በመገለላቸው ሊቆጡ እና መብታቸው እንደተጣሰ ተሰምቷቸው ወደ ነውጥ ሊያመሩ ይችላሉ። ጋዜጠኞች ችግር እንደሚኖር መተንበይ ከቻሉ እና ብዛት ያላቸው ሰዎች የመራጮች ምዝገባ መሥፈርቶችን እንዳልተረዱ መገንዘብ ከቻሉ፣ መራጮችን በማስተማር እንዲሁም የመራጮችን ግዴታ መማሪያ ተደራሽነት በተመለከተ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ተጠያቂነትን እንዲወስዱ በማድረግ ረገድ ሚና ሊኖራቸው ይችላል።

በተመሳሳይም፣ ሰዎች ስለ ፖለቲካ እና ፖሊሲ ማሻሻያዎች አጠቃላይ ግንዛቤ እንዲያገኙ ጋዜጠኞች ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። አዳዲስ ፖሊሲዎች በሚተዋወቁበት ጊዜ እነዚህን ፖሊሲዎች የሚቃወሙ ወገኖች ከራሳቸው ጥቅም ጋር የሚያያዙትን ጉዳዮችን መርጠው በማጉላት ሰዎች እንዲያውቁት ማድረግ የተለመደ ነው። ብዙውን ጊዜ የእነሱን አቋም የማያንፀባርቁ መረጃዎችን ችላ ይላሉ፣ ይዘሉታል ወይም አዛብተው ያቀርቡታል። ሰዎች የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ መርዳት የተሻሉ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንዲችሉ እና አጀንዳ ባላቸው ሰዎች እንዳይሳሳቱ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል ብናይ፣ ትላልቅ ፋብሪካዎች እና የማዕድን ማውጫ ፋብሪካዎች ለማኅበረሰቡ ስለሚያደርጉት ጥቅም ለሰዎች የመንገር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ነገር ግን ሥራቸው በአካባቢያቸው እና በሰዎች ጤና ላይ ስለሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከመናገር ይቆጠባሉ። ጋዜጠኞች ምርምር በማካሔድ እና ሰዎች የእነዚህን ፋብሪካዎች ተፅዕኖ እንዲገነዘቡ በመርዳት የአከባቢው ማኅበረሰብ ተገቢ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ እንዲሁም ተደራጅተው መብታቸውን እና አካባቢያቸውን ለማስጠበቅ እርምጃ መወሰዱን ማረጋገጥ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎች በኋላ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከባድ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ይከላከላል።

እንደ ባርባራ አሞንግ አስተሳሰብ መረጃ የማድረስ ዋናው ጥቅም የተለያዩ ቡድኖች ቃል አቀባዮች መረጃ ላይ ከመተማመን ይልቅ ስለ ክስተቱ ዘገባዎችን የሚያጠናቅሩ ጋዜጠኞችን በቦታው እንዲገኙ ማድረግን ይጨምራል። እንደሷ አገላለጽ የአንድ ወገን መገለጫ የሆኑ “የተደራጁ መረጃዎችን እንዲሰጡ የሠለጠኑ ቃል አቀባዮች”ን መረጃ ልናልፈው ይገባል ምክንያቱም ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ የተሰኘው የሽብር ቡድንን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች የሚወክሏቸው ሰዎች እንዳሏቸው በማብራራት የሚከተለውን ሐሳብ ታቀርባለች::

ከቃል አቀባዮች የምታገኟቸው መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጋዜጠኞችን ቦታው ላይ በመላክ እውነቱን ማወቅ ይኖርባችኋል። በብዙ ሁኔታዎች መረጃ የማቅረብ ሒደት ሰዎች የመረጃ ክፍተት ያለባቸውን አካባቢዎች መለየት እና ውሳኔዎች ለምን እንደተላላፉ እንዲሁም የተላለፉት ውሳኔዎች ብልሕ ውሳኔዎች መሆን ወይም አለመሆናቸውን ሊያስረዱ ከሚችሉ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ ማድረግ ማለት ነው። ጋዜጠኞች አማራጭ ውሳኔዎች የበለጠ ጠቃሚ ላይሆኑ እንደሚችሉ ሰዎች እንዲገነዘቡ ሊረዱ የሚችሉ ባለሙያዎችን መለየት አለባቸው።

እንዲሁም ወደታች ወርዶ ሰዎች ስለግጭቱ የሚያውቁትን እና የማያውቁትን ነገር ማነጋገር ጠቃሚ ነው። ጋዜጠኞች ስለጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤ በተመለከተ ከሰዎች ጋር በመነጋገር ጊዜ በሚያሳልፉበት ወቅት፣ ሰዎቹ መረዳት ያቃታቸውን የግጭቱን ቁልፍ ጉዳይ ሊደርሱበት ይችላሉ። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ መሪዎች ሆን ብለው መረጃን እየደበቁ እና እያዛቡ መሆናቸውንም ማጋለጥ ይችላሉ።

2.3 ጋዜጠኞች የተለያዩ ወገኖችን ስለ ግጭት መቆጣጠር እና አፈታት መንገዶች ሊያስተምሩ ይችላሉ

ልክ እንደ አሸማጋዮች በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትን ግጭት ለመፍታት ወይም ሰላማዊ አማራጮችን ለመፈለግ የሚያስችሏቸው የተለያዩ ሒደቶችን በማስተማር ልንረዳቸው እንችላለን። በሌላ አካባቢ ውጤታማ የሆኑ የሰላም ሒደቶችን በመዘገብ በግጭት ተሳታፊ አካላትን ፍላጎት በሚያሟላ ሁኔታ ግጭቶች ሊፈቱ እንደሚችሉ ማሳየት እንችላለን። እንዲሁም እነዚህ ሒደቶች እንዴት መከናወን እንደሚችሉና እና በግጭት ውስጥ ላሉ አካላት ከነውጥ ባሻገር ያሉ አማራጮችን ማሳየት ይቻላል።

ባርባራ አሞንግ እንዲህ ትላለች:

 …. ከበፊት ተሞክሮ እያነሱ ማሳያዎችን ማቅረብ ጥሩ ነው፤ ማለትም የተገኘው ውጤት ምንድን ነው? እነማን ተሳትፈው ነበር? ምን ዓይነት ሚና ነበራቸው? ከተለያዩ አገሮች ምሳሌዎች በማምጣት በውጤቱን መሠረት ምላሽ ይስጡ። ሌላ አካባቢ ግጭትን እንዴት እንደተቆጣጠሩ መመርመር አለብን።

ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ1994 ወደ ዲሞክራሲ ከተሸጋረች በኋላ በሰዎች ላይ የደረሱ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ መፍትሔ ለመስጠት በተቋቋመው ሐቅ እና ዕርቅ ኮሚሽን ብዙ አገራት ተማርከውበታል። ከነዚህም ውስጥ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ኮሎምቢያ፣ ቺሊ፣ ፊጂ፣ ጋና፣ ኬኒያ፣ ላይቤሪያ፣ ሞሮኮ፣ ፔሩ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲሪላካ እና ዩናይትድ ስቴትስ ይገኙበታል። እነዚህ አገራት የሐቅ እና ዕርቅ ኮሚሽኑን ሙሉ በሙሉ የመተግበር ዕድላቸው አነስተኛ ቢሆንም፥ ትምህርት ከወሰዱት ነገር ተነስተው ለራሳቸው ሁኔታ እንዲስማማ አድርገው ይጠቀሙታል።

ለተደራሾቻችን በሌሎች አካባቢ ስለሚካሔዱ የሰላም ተነሳሽነቶች በማስተማር መፍትሔ የሚፈልጉበትን አድማስ እንዲያሰፉ እንዲሁም ግጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሰላማዊ መንገዶችን እንዲያስቡ እናበረታታቸዋን። ግጭት ሰፊ በሆነባቸው ብዙ አካባቢዎች ውስጥ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንዳይገቡ መቆጣጠር የቻሉ ማኅበረሰቦችን ማግኘት ይቻላል። ይህ የሚሆነው በብዛት አነስተኛና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች ማኅበረሰብ ዐቀፍ ድርጅቶች ዕርዳታ አማካኝነት ነው። እነዚህ አካላት ለማኅበረሰባቸው ያስገኙትን ውጤት በማሳየት ጋዜጠኞች ሌሎች ማኅበረሰቦች በግጭት ሳቢያ የሚነሱ ነውጦችን ለመከላከል ስልቶችን እና ሒደቶችን እንዲለዩ ይረዷቸዋል። ጋዜጠኞች እነዚህ ቁልፍ አጋጣሚዎች ወሳኝ ታሪኮች መሆናቸውን በመገንዘብ በአግባቡ መዘገብ ይጠበቅባቸዋል። በተቃራኒ ቡድን ተሰልፈው የነበሩ ወጣቶችን ተቀራርበው እንዲሥማሙ ያስቻለ የወጣቶች እንቅስቃሴ ታሪክ በሌላ አካባቢም ሊደገም ይችላል።

በግጭት አፈታት ሒደት የሚሳተፉ ሰዎች ያለማቋረጥ ከሌሎች ልምድ በመቅሰም ከራሳቸው ሁኔታ ጋር በማሥማማት አስተካክለው ይጠቀሙበታል። ጋዜጠኞችም ይህን መንገድ የማይከተሉበት ምንም ምክንያት የለም። ሰዎች በአካባቢያቸው ተሞክሮ ካጋጠማቸው ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ግጭቶችን እንዴት እንደሚይዙ በመፈለግ ጋዜጠኞችን ኅብረተሰቡ ሊጠቀምባቸው ለሚችላቸው የተለያዩ ስልቶች ሊያስተዋውቁ ይችላሉ። በእነሱ አካባቢ ካለው ግጭት ጋር የሚመሳሰል ግጭትን ሌሎች ሰዎች አንዴት ሊቆጣጠሩት እንደቻሉ በመረዳት ጋዜጠኞች ለማኅበረሰባቸው ሊጠቅሙ የሚችሉ የተለያዩ ስልቶችን ሊያመላክቱ ይችላሉ።

የማስተማር ሚናችን ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ሰላማዊ ውጤቶችን የሚያስገኙ ስልቶችን እንዲተገብሩ ከማስቻል መሻገር እንዳለበት ልብ ማለት ያለብን ጉዳይ ነው። ይህ በውሳኔ ማሳለፍ ሒደት ውስጥ ሊረዳቸው የሚችል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም አካባቢያዊ ሒደቶችን የሚመለከት መረጃ መስጠትን ሊያካትት ይችላል። ለምሳሌ የአየር ንብረት ለውጥ በአካባቢያቸው የውሃ አቅርቦት ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ማሳየት በግጭቱ ዙሪያ መነጋገር እንዲጀምሩ እና የጋራ ችግራቸውን በአንድነት ሆነው መፍትሔ እንዲያገኙለት ይረዳል።

ይህ ለጋዜጠኞቹ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰት ግጭትን በንቃት በመከታተል ግጭቶችን በመፍታት ሐደት የተገኘውን መሻሻል መቆጣጠር ማለት ነው። እንዲሁም የግጭት መንስዔዎች መስለው ከሚታዩት ነጥቦች በማለፍ ግጭቶች እንዴት ሊወገዱ እንደሚችሉ የተገናዘበ የባለሙያ ምክር መጠየቅ ማለት ሊሆን ይችላል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *