የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በትግራይ ክልል እየተደረገ ላለው ድጋፍ ገለጻ ሲያደርጉ

ኮሚሽነሩ በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራው ዓለም አቀፍ ሕግጋት የሆኑትን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ፣ ክብርን የጠበቀ፣ በቂ ዝግጅት የተደረገበት፣ የደኅንነት ሥጋት የሌለበትና ዘላቂነት ያለው ይሆናል ብለዋል፡፡

በክልሉ በ12 መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ተፈናቃዮች ሙሉ ሰላም ወደ ተረጋገጠባቸው ሥፍራዎች ሲመለሱ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እንደሚደረጉ፣ ሙሉ ሰላም ባልተረጋገጠባቸው ቦታዎች መመለስ ለማይችሉት ዘመድ ዘንድ ተጠግተው እንዲኖሩ የማመቻቸት፣ በሁለቱ መንገድ ከጣቢያዎቹ ሊወጡ የማይችሉ ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያ የሚቆዩ መሆኑንም ኮሚሽነር ምትኩ ተናግረዋል፡፡

ወደ ቀዬአቸው መመለስ ለማይችሉት በመቀሌ የካምፕ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን፣ በቀጣይ በሽሬና በሌሎች ከተሞችም ይሠራል ብለዋል፡፡

ዝናብ ከመምጣቱ በፊት ተፈናቃዮች ተመልሰው ወደ እርሻ ሥራ እንዲገቡ፣ ቤተ ዘመድ ጋ የሚሄዱት ደግሞ እንዲሄዱና ወደ ሁለቱም መመለስ የማይችሉት በመጠለያ እንዲቆዩ ለማድረግ ከፍተኛ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ስለሚያስፈልጉ ይህንን ለማሟላት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ወቅቱ የዝናብና ከ90 በመቶ በላይ የግብርና ምርት የሚገኘው በክረምት ከሚዘራው በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ከ126 ሺሕ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደብ እያጓጓዘ መሆኑን፣ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችና በሰብል የሚሸፈነው መሬት መለየቱን፣ 5.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 5,580 ኩንታል ያህል የምርጥ ዘር አቅርቦት እየተዘጋጀ መሆኑንና እያንዳንዱ አርሶ አደር በ2014 ዓ.ም. ተረጂ እንዳይሆን ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ በአንደኛው ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ መሠራጨቱን፣ በሁለተኛው ዙር ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ዕርዳታው እንዲደርሳቸው መደረጉንና ለሁለቱ ዙሮች ዕርዳታም 3.7 ቢሊዮን ብር ወይም 94.6 ሚሊዮን ዶላር እንደወጣ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የዕርዳታ አሸፋፈኑ 70 በመቶ በኢትዮጵያ መንግሥት፣ 27 በመቶ በዩኤስኤአይዲ ድጋፍ የሚደረግለት አገር በቀሉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሬስት፣ እንዲሁም ሦስት በመቶ በዓለም ምግብ ፕሮግራም የተሸፈነ መሆኑን፣ ለሦስተኛው ዙር ዕርዳታ ግን የአካሄድ ለውጥ ተደርጓል ተብሏል፡፡

ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት የገቡ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትግራይ ክልል ውስጥ በስፋት ለመሥራት ፍላጎት በማሳየታቸው፣ መንግሥት ይህንን ፍላጎት ተከትሎ በመንግሥትና በሬስት በኩል ይሸፈን የነበረውን የዕርዳታ አቅርቦት ሰፋ በማድረግ አራት ተጨማሪ ዕርዳታ አቅራቢ ማለትም የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ አገር በቀሉ ሬስት፣ ኬር ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ ወርልድ ቪዥንና ፉድ ፎር ሃንገር የተባሉ ድርጅቶች በትግራይ የዕርዳታ አቅርቦቱን እንዲሠሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የዕርዳታ ሽፋኑን በስፋት የያዘው መንግሥት የነበረ ቢሆንም፣ በአዲሱ አካሄድ 86 በመቶውን ሽፋን ረጂ ድርጅቶቹ እንዲሠሩና በክልሉ ካሉት 92 ወረዳዎች ውስጥ 86 በመቶውን እንዲሸፍኑ ቀሪውን 14 በመቶ ደግሞ መንግሥት የሚሸፍን ይሆናልም ተብሏል፡፡

ከዚህ በኋላ የመንግሥት አብዛኛው ሥራ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ዕርዳታው በአግባቡ መድረሱን መከታተል ይሆናል ያሉት ኮሚሽነር ምትኩ፣ ከ4.5 ሚሊዮን ዕርዳታ ፈላጊዎች መካከል 2.2 ሚሊዮን አካባቢ ምግብ ነክ ያልሆነ ዕርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን፣ በዚህ መሠረት ትልቅ ድርሻ ይዞ እየሠራ ያለው መንግሥት መሆኑን የአጋር አካላት ድርሻ እስካለፈው ሳምንት መገባደጃ 33 በመቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ተደራሽነትን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም በአጋር ድርጅቶች ይነሳ የነበረው ችግር ተፈትቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ሥፍራው የሚሄድ አጋር ድርጅት ለእያንዳንዱ ጉዳይ ከሰላም ሚኒስቴር ሰርተፊኬት እየያዘ ይሄድ እንደነበር፣ አሁን ይህንን አሠራር በመቀየር ወደ ክልሉ የሚሄድ አንድ አጋር የጉዞውን ዓላማ፣ የሚሄዱ ሰዎች ማንነትና የቆይታ ጊዜ ከመሄዳቸው ከ48 ሰዓት በፊት በኢሜይል አሳውቀው መሄድ ይችላሉ ተብሏል፡፡

የቪዛ ጥያቄን በተመለከተ ይነሳ የነበረውን ችግር የሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊዎች ሲመጡ ይሰጥ የነበረው የአንድ ወር ቪዛ አጭር ጊዜ ነው የሚል የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ አሠራር እስከ ሦስት ወራት የሚራዘም መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኮሙዩኒኬሽን (የመገናኛ) ቁሳቁስን በተመለከተ በአገሪቱ የደኅንነት ሕግ መሠረት የሚፈቀዱና የተከለከሉ መኖራቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ የአገሪቱን ሕግ በማክበር እያንዳንዱ ተቋም እንዲስተናገድ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *