በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ግድያዎችን፣ መፈናቀሎችና የንብረት መውደምን በተመለከተ መንግሥት የሚወስደውን ቀጣይ እርምጃ እንዲያብራራ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ጠየቀ።
ኢሰመጉ “የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በማስቆም አገርን እንታደግ” በሚል ሚያዝያ 13/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ መንግሥት ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከልና ማስቆም ያልቻለበትን ምክንያት እንዲሁም ቀጣይ እርምጃዎችን በተመለከተ ይፋዊ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል። ኢሰመጉ በአገሪቱ ላይ በተለያዩ ወቅቶች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ይፋ በማውጣት መንግሥት ከመባባሳቸው በፊት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ካልሆነ ግን ተጠያቂነት የማይቀር መሆኑን እንዲሁ በቅርቡ ማሳሰቡን በመግለጫው አስፍሯል።
ኢሰመጉ በቅርቡ በአጣዬ ከተማና አካባቢው ስለተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መግለጫዎችን አውጥቶ ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን አስታውሶ “ነገር ግን አስፈላጊው ጥንቃቄ አልተደረገም” ብሏል። “የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሰለባዎች ከጉዳታቸው ሳያገግሙ እንዲሁም የአካባቢው የፀጥታ ስጋተ እንዳለበት ታውቆ” አስፈላጊው ጥንቃቄ መወሰድ ሲገባው ባለመሆኑ ከሚያዝያ 6/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በከባድ መሳሪያ በታገዘ ነዋሪዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሰዎች ሞተዋል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል ብሏል።
ከዚህ ቀን ቀደም ባሉት ተከታታይ ቀናትም እንዲሁ በአጣዬ ዙሪያ ባሉት በማጀቴ፣ ቆሪና ሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁና በከባድ ጦር መሳሪያ በታገዙ ታጣቂዎች በማጀቴ በርካታ ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ በካራ ቆሬ የጸጥታ ኃይሎች መቁሰላቸውንና በርካታ ነዋሪዎች አካባቢውን ጥለው መሰደዳቸውን ኢሰመጉ መረጃ ደርሶኛል ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ አጣዬ፣ ቆሪሜዳ፣ ዙጢ፣ ካራቆሬ የተባሉ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ እንደወደሙ ድርጀቱ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ በመግለጫው አስፍሯል።
በኦሮሚያ ክልል እንዲሁ “በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ግድያዎች፣ የአርሶ አደሮች ቤቶችና የእህል ጎተራ እንደሚቃጠል እና በርካቶችም ቀያቸውን ለቀው እንደሸሹ” በዚህ መግለጫ ዳስሷል። ጥቅምት 24/2013 ግጭት በተነሳባት ትግራይ ክልለ ነዋሪዎች ለችግር መጋለጣቸውንና አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ኢሰመጉ አሳስቦ የፀጥታ ሁኔታው አሁንም ያልተሻሸለና ለመንቀሳቀስም ምቹ አለመሆኑን መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ነዋሪዎች በታጣቂዎች እንደሚገደሉ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን በጉማይዴና አማሮ ልዩ ወረዳ የነዋሪዎች ግድያ መበራከቱንና የሕገ ወጥ እስር መጨመሩን ኢሰመጉ የደረሱትን አቤቱታዎች ዋቢ አድርጎ አስፍሯል። በአፋር ክልል በዜጎች ላይ የሚፈፀመው ግድያና የንብረት መውደም አስከፊ መሆኑን በዚህ መግለጫው አካቷል።
ኢሰመጉ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ያለው “የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ወደ ከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን” ጠቁሞ “የአገሪቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ አሳሳቢ” እንደሆነም አመላክቷል። “በአገራችን ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰና እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ሰብአዊ መብቶች ምንም ዋስትና የላቸውም ማለት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ብሏል።
ኢሰመጉ በዚህ መግለጫው ላይ እንደ መፍትሔ ብሎ ያቀረባቸው በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥሰቶች ተስፋፍተው ሰዎችን ለእልቂት ከመዳረጉ በፊት የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት፣ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በአገሪቱ ሰላም የሚወርድበትን ሁኔታ እንዲወያዩና የሰብዓዊ መብቶች ዋስትና ስለሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመክሩ ብሏል።
በተጨማሪም የጸጥታ ስጋት ያለባቸውን እንዲሁም መሰል ጥቃቶች ሲፈጸሙባቸው የነበሩ አካባቢዎችን በመለየት የተለየ ጥበቃ የሚደረግበትን ስልት በአፋጣኝ መዘርጋት የሚሉት እንደ መፍትሔ ኢሰመጉ ከጠቆማቸው መካከል ናቸው።
ምንጭ – ቢቢሲ