የፊታችን ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ፣ እንዲሁም ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚታዘብ ልዑክ የመላክ ዕቅዱን መሰረዙን የአውሮፓ ኅብረት አስታወቀ፡፡ የኅብረቱ ምክትል ኮሚሽነር ጆሴፍ ቦሬል ሰኞ ሚያዚያ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹መሠረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ባለመድረሳችን ታዛቢ የመላክ ዕቅዱ ተሰርዟል፤›› በማለት የኅብረቱን አቋም ይፋ አድርገዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳን ኅብረቱ የምርጫ ታዛቢዎችን ለማሰማራት ሊሟሉ ይገባቸዋል ያላቸውን መሠረታዊ መሥፈርቶች አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ከስምምነት ላይ ለመድረስ ኅብረቱ የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርግም፣ መሠረታዊ መሥፈርቶቹ ባለመሟላታቸው የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ቡድን የመላክ ዕቅዱን ሰርዟል፤›› ሲል ኅብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኅብረቱ በዋነኛነት አልተሟሉም በማለት በመግለጫው የገለጻቸው መሥፈርቶች፣ ‹‹የታዛቢ ልዑኩ ነፃነትና ኅብረቱ የራሱ የመገናኛ ዘዴ ይኑረው፤›› የሚለው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የመገናኛ መሣሪያዎቹም በተለይ የታዛቢ ልዑክ ቡድኑን ደኅንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነም አክሎ ገልጿል፡፡

ኅብረቱ ምርጫውን ለመታዘብ ያስፈልጉኛል ባላቸው መሠረታዊ መሥፈርቶችን አስመልክቶ ማረጋገጫ ባለማግኘቱ የተነሳ፣ ‹‹ዴሞክራሲን ለሚሻው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ሊያደርግ ባለመቻሉ ቅር ተሰኝቷል፤›› በማለት ከመግለጽ ባለፈ፣ ‹‹ኅብረቱ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊና የሲቪል መብቶቻቸውን  እንዲያረጋግጡ ዋስትና እንዲሰጥ ያበረታታል፤›› በማለትም መግለጫው ያትታል፡፡

የኅብረቱ ውሳኔን አስመልክተው ማክሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ ‹‹ኅብረቱ ሉዓላዊነት የሚዳፈር ሥራ እንዲያከናውን ስላልተፈቀደለት የመታዘብ ዕቅዱን ሰርዟል፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኅብረቱ ምርጫ ሲታዘብ መጠቀም በሚፈልገው የመረጃ ቴክኖሎጂና የምርጫ ውጤትን ከምርጫ ቦርድ ቀድሞ ይፋ ላድርግ የሚሉ ፍላጎቶች እንደነበሩት የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ እንዲህ ያለው አካሄድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ስለሚፈታተን ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

ኅብረቱ ያቀረባቸው ሁለቱ ቅድመ ሁኔታዎች ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች አለመቅረባቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የእኛ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ሥርዓት የማይቆጣጠረውን መሣሪያ ይዤ ልግባ ማለት ላስተዳድራችሁ ማለት ነው፤›› በማለት፣ ኅብረቱ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያ መንግሥት የምርጫ ታዛቢዎችን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ በምርጫ 97 ወቅት የኅብረቱ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መሪ በነበሩት ፖርቱጋላዊቷ አና ጎሜዝና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ከፍተኛ አለመግባባት መፈጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ የኅብረቱን ሪፖርት ያጣጣለው መንግሥት የኅብረቱን ታዛቢ ቡድን ገለልተኝነት ጥያቄ አንስቶበት ነበር፡፡ በተመሳሳይ የኅብረቱ መንግሥትን በምርጫው ዕለትና በድኅረ ምርጫ በወሰዳቸው ኢዴሞክራሲያዊ አሠራሮች መወንጀሉ አይዘነጋም፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር