የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
ባሳላፍነው ሳምንት የሚንስትሮች ምክር ቤት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የውሳኔ ሃሳብ አስተላልፎ እንደነበረ ይታወሳል። ዛሬ ስብሰባውን እያደረገ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለቱ ቡድኖች በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ምክር ቤቱ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስታውቋል።
በአሸባሪነት የተፈረጁት ‘ሸኔ’ እና ህወሓት ማን ናቸው?
ሸኔ
የሚንስትሮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ እንዲፈረጅ ሃሳብ ያቀረበው “ሸኔ” ቡድንን ነው።በአሁኑ ወቅት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በስፋት ስለሚንቀሳቀሰው እና የመንግሥት ባለስልጣናት፤ ‘ኦነግ ሸኔ’ ብለው ስለሚጠሩት ታጣቂ ቡድን የሚታወቀው የሚከተለውን ነው። መንግሥት በተለይ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ‘ኦነግ ሸኔ’ በሚል የሚጠሩት ታጣቂ ኃይል ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” በማለት ይጠራል።’የኦሮሞ ነጻነት ጦር’ ለበርካታ አስርት ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ የጦር ክንፍ ሆኖ ቆይቷል።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህምድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የኦነግ አመራሮች ወደ አገር ከገቡ በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው ቡድን) ከፓርቲው ተገንጥሎ በትጥቅ ትግሉ እንደሚቀጥል ይፋ አደረገ። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ኦነግ ሸኔ) በእርሳቸው እንደማይታዘዝ ይፋ አድርገው ነበር።
ሸኔ የሚለው መጠሪያ ከየት መጣ?
ሸኔ- ማለት ‘ሸን’ ከሚለው የኦሮምኛ ቃል የመጣ ነው። ‘ሸን’ ማለት አምስት ማለት ነው። ‘ሸኔ’ ማለት ደግሞ አምስቱ እንደማለት ነው። በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ አምስት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‘ጉሚ ሸኔ’ ተብሎ ይጠራል። ጉሚ ሸኔ ማለት ‘አምስት አባላት ያሉት ጉባኤ’ እንደማለት ነው። ፓርቲው ግን ከ5 በላይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሊኖረው ይችላል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን መሪ እንደሆነ የሚታመነው ኩምሳ ድሪባ በትግል ስሙ በስፋት የሚታወቀው ጃል [ጓድ] መሮ፤ ለኦሮሞ ነጻነት እንታገላለን ይላል። በተለያዩ ወቅቶች መንግሥት በዚህ ቡድን ላይ በሳምንታት ውስጥ ‘እርምጃ’ እወስዳለሁ ቢልም፤ በቡድኑ አባላት ተፈጽመዋል በሚባሉ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ተገድለዋል በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ቡድን በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የፖሊስ አባላት ላይ ግድያ እና የባንክ ዝርፊያ መፈጸሙን ይገልጻል። መንግሥት ከዚህ ቀደም ይህ ቡድን በህወሓት ድጋፍ እንደሚደረግለት እና በትግራዩ ግጭትም ለህወሓት ወግነው ሲዋጉ ነበሩ ያላቸውን ‘የኦነግ ሸኔ’ ታጣቂዎችን መማረኩን አስታውቆ ነበር።
ኦነግ-ሸኔ የሕዝብ ‘ጠላት ነው’
የቦረና አባ ገዳ የሆኑት ኩራ ጃርሶ ኦነግ-ሸኔን የሕዝብ ጠላት ነው ሲሉ ቡድኑን ማውገዛቸው ይታወሳል። አባ ገዳ ኩራ በታጣቂ ቡድኑ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሠላማዊ ሰዎች በመገደላቸው ቡድኑን ጠላት ብሎ መፈረጁ እንዳስፈለጋቸው ተናግረዋል። የቦረና አባ ገዳ በማኅበረሰባቸው ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሲሆኑ የሚያስተላልፉትም መልዕክት ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው።
ህወሓት
ህወሓት በሽምቅ ውጊያ ወደ አገር መሪነት ከዛም ወደ የክልል አስተዳዳሪነት በመጨረሻም ወደ ሽምቅ ወጊያ ተመልሷል። ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛው ተዋናይ ሆኖ የቆየው ህወሓት ባለፈው ጥቅምት ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱን አጥቶ እንዲሰረዝ ተደርጓል።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የንጉሡ አስተዳደር ወድቆ ወታደራዊው መንግሥት ወደሥልጣን መውጣቱን ተከትሎ ነበር የካቲት 11/1967 ዓ.ም የትጥቅ ትግል መጀመሩን ያስታወቀው። ለህወሓት የትጥቅ ትግል መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) የተባለው መደበኛ ያልሆነ ቡድን ነበር።
ማገብት በስምንት አባላት የተመሠረተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሪሁ በርሀ (አረጋዊ በርሄ ዶ/ር)፣ አምባዬ መስፍን (ስዩም መስፍን) እና አመሃ ፀሃዬ (አባይ ፀሃዬ) ተጠቃሽ ናቸው። ከደርግ ጋር የሚደረገው ጦርነት ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሲሸጋገር በየአካባቢዎቹ ያሉትን ሕዝቦች ይወክላሉ የተባሉ ድርጅቶችን ማቀፍ እንዲሁም ሊወክሉ ይችላሉ የሚባሉ እንዲቋቋሙ ህወሓት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን)፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጋር በመጣመር ኢሕአዴግ የተባለውን ግንባር ፈጠረ። በህወሓት የበላይነት ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ የደርግ መንግሥትን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ ለ27 ዓመታት አገር መምራት ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን በግንባሩ ውስጥ ለዓመታት የቆየው ቅሬታ ስር እየሰደደና እየጎላ መጣ። በመጨረሻም ኢህአዴግ ከስሞ የብልጽግና ፓርቲ ሲተካው ህወሓት በአዲሱ ስብስብ ውስጥ ላለመግባት ከመወሰኑ ባሻገር “ውህደቱ ሕጋዊ አደለም” በማለት ተቃውሞውን አስምቶ ነበር።
ህወሓት ከፍተኛ አመራሮቹን ይዞ ወደ ትግራይ ካቀና በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ከመሻከር አልፎ ወደ ግጭት አምርቷል። ከ6 ወራት በፊት በተጀመረው ጦርነት የፌደራሉ መንግሥት ‘ህወሓት አብቅቶለታል’ ሲል አውጇል።
የቡድኑ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በተለያዩ ከፍተኛ ወንጀሎች ተጠርጥረው የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ወራት ተቆጥረዋል። በርካታ የህወሓት አመራሮች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ሌሎች ደግሞ መገደላቸው የአገሪቱ ሠራዊት መገለጹ ይታወሳል።
ምንጭ – ቢቢሲ