ነገሩ ግራ ይመስላል። ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተቃራኒ ምርጫን የተመለከተ እንቅስቃሴ በአካባቢው አይስተዋልም። የእጩዎች ምዝገባ አልተካሄደም። የመራጮች ምዝገባም የለም። ወደ ማህበረሰቡ ቀርቦ “ምረጡኝ” የሚል ፓርቲም የግል ተወዳዳሪም አይታይም።
ይህ ዘንድሮ ብቻ የሆነ አይደለም። ባለፉት አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ምንም ተሳትፎ አልነበራቸውም። የሀገሪቱ ህገ መንግስት 18 ዓመት የሞላው ማንኛውም ዜጋ በህግ መሰረት የመምረጥ መብት አለው ቢልም በአላጌ ይህ መብት ተተግብሮ አያውቅም። ለምን?
አስተዳደር አልባው ማህበረሰብ
ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ 194 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቡልቡላ የተሰኘች ከተማ አለች። ከቡልቡላ ከተማ አቅራቢያ ወደ ቀኝ ከሚታጠፍና 32 ኪሎ ሜትር ከሚሸፍን አስቸጋሪ መንገድ በኋላ የአላጌ ግብርና ቴክኒክ ሙያ ኮሌጅ ይገኛል። ኮሌጁን ማዕከል አድርገው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በአካባቢው ኑሯቸውን መስርተዋል ።
በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች መካከል የሚገኘው ቦታው በየትኛውም ክልል አስተዳደር ውስጥ አልተጠቃለለም። የዚህ መነሻ ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ የክልሎች ወሰን ሲቀመጥ ሁለቱ ክልሎች [በደቡብ በኩል የቀደሞ የሃላባ ልዩ ወረዳ] አካባቢው ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳታቸው እንደሆነ ይገለጻል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሶስት ዓመታት በፊት በሰራው ዘገባ 44 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈው ስፍራው በፌዴራሉ መንግስት ስር እንደሚተዳደርና ከ10 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳሉት ጠቁሟል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የፖሊስ አገልግሎቶችን በደቡብ ክልል- የህግና የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ደግሞ በስልጤ ዞን በኩል ይቀርቡለታል። ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተናን የኦሮሚያ ክልል ሲሰጥ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን የተመለከቱ አገልግሎቶችን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያመቻቻል – አገልግሎቶቹ በሙሉ በትብብር የሚቀርቡ መሆናቸው ሳይዘነጋ። በአካባቢው ባለፈው ዓመት የመሰናዶ ትምህርት ቤት ስራ ጀምሯል። ይህም የአላጌ ተማሪዎች መሰናዶ ሲደርሱ ‘የዚህ ክልል ተማሪ ስላልሆናችሁ አናስተናግድም’ ከሚል እንግልት ታድጓቸዋል ይላሉ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች።
ሆኖም ወደ መሰናዶ መሸጋገር ያልቻሉ ወይም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያላመጡ የአካባቢው ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን ለመቀላቀል ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ ይጠብቃቸዋል። “አዲስ አበባ ያለው ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ [ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ] ነው በተወሰነ ደረጃ የሚረዳን። የኮሌጁ ዲን [የአላጌ] ደብዳቤ ተጻጽፎ ክልል እንደሌለን ተረጋግጦ በየዓመቱ ተማሪዎችን ይቀበልልናል።” በማለት ያስረዳሉ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሹሜ። ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ኮተቤ ካላገኘ ሌላ ዕድል የለውም። መሃይም ሆኖ መቅረት ነው ይላሉ።”
ከምርጫ ጋር የማይተዋወቀው አካባቢ
አቶ ሹሜ አሰፋ በአካባቢው 41 ዓመታት ኖረዋል። አምስት ልጆችንም አፍርተዋል። በስፈራው በተለያዩ ወቅቶች በነበሩ መንግሥታዊ ተቋማትም ሰርተዋል። ሆኖም አንድም ጊዜ ምርጫ ላይ አልተሳተፉም። ” ምርጫ እዚህ አካባቢ ተካሄደ እዛ አካባቢ ተካሄደ ሲባል እንሰማለን [ግን] ምን ይሁን ምን አናውቅም” ሲሉ ይናገራሉ። ሌላኛው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ወጣት ነዋሪ ደግሞ “ታዛቢ ሆነን የሚደረገውን ማየት ነው። ሀገራችን ላይ ምን እየተከናወነ ነው የሚለውን ማየት ነው እንጂ ተሳታፊ ሆነን እንደመብት የምንጠቀመው ነገር የለም።…እንደዚህ መሆናችን ያሳዝነኛል” ይላል።
ከዚህ ቀደም የኮሌጁ ተማሪዎች የየመጡበትን አካባቢዎች ተወካዮች የሚመርጡበት እድል ተመቻችቶ እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። በአላጌ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የኖሩትና ስማቸውን እንዲጠቀስ የማይሹ ሌላ አስተያየት ሰጪ በምርጫ የመሳተፍ ፍላጎት ቢኖራቸም አንድም ጊዜ ለዚህ አለመታደላቸውን ገልፀዋል። “ዜግነት እንዳለን እንደማይቆጠር ነው የሚሰማን” ብለዋል።
በተለያዩ ወቅቶች በነበሩ ስብሰባዎች የምርጫን ጉዳይ “ሳናነሳ አናልፍም” የሚሉት ነዋሪዎቹ ‘ጠብ’ የሚል ነገር ግን የለም ሲሉ ይደመጣሉ። ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የኖሩት አስተያየት ሰጪያችን ነገሩ ተስፍ አስቆርጦናል ሲሉ ይገልጻሉ። በፌዴራል “ስር ስላላችሁ መምረጥ አትችሉም” የሚል ምላሽ ስለመሰጠቱም አስረድተዋል። “ለመጣ ባለስልጣን እንናገራለን። ምላሽ ስለሌለ ሰው ተሰላችቶ ትቶታል…መምረጥ ነበረባችሁ በሚቀጥለው እንነጋገራለን ብሎ የሚሄድ እንጂ ይሄን እናደርጋለን የሚል ሰው የለም” የሚሉት ደግሞ አቶ ሹሜ ናቸው።
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገባ ላይ ተካትተው የነበሩት የኮሌጁ ዲን ከበደ በዬቻ (ዶ/ር) “ስለምርጫውም ለእርሻና ተፈጥሮ ሃብትም [የአሁኑ ግብርና ሚኒስቴር] አሳውቀናል። አንድ ኢትዮጵያዊ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ አለበት – መብቱም ስለሆነ” ብለዋል። ሆኖም ተጨማሪ መረጃዎችን ለመጠየቅ ቢቢሲ ዲኑን፣ ምክትል ዲኖችንና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ለማግኘት ከሁለት ሳምንት በላይ (17 ቀን) የፈጀ ተደጋጋሚ ጥረት ፍሬ አላፈራም።
የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበራ ለማ “ተቋሙ [ኮሌጁ] ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ነው። የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ የማውቀው ነገር የለም…ግብርና ሚንስቴር የሚያስተዳድረው ህዝብ የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል ከምርጫ ቦርድም ምላሽ ለማግኘት ላለፉት ሁለት ሳምንታት በስልክ፣ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እንዲሁም በኢሜል ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገናል – ነገር ግን ምላሻቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የፎቶው ባለመብት,RESIDENTS
ከህጻናት አምባ እስከ እስከ ግብርና ኮሌጅነት
መስከረም 4 1973 ዓ.ም ከኢፌዴሪ መንግስት ምስረታ በፊት በነበረው የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ መዋቅር በሸዋ ክፍለ ሃገር ሀይቆችና ቡታጀራ አውራጃ በሃላባ ቁሊቶ ወረዳ አላጌ በተባለ ስፍራ የአብዮታዊ ህጻናት አምባ የተሰኘ ተቋም ተመረቀ። በጦርነትንና በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን የማሳደግ አላማ የያዘው ተቋሙ በአምስት መንደሮች የተከፋፈለ ነበር። ተቋሙ ግዙፍ ነበር የሚሉት አቶ ሹሜ እያንዳንዱ መንደር አስተዳዳሪ እንደነበረው ይናገራሉ።
ሞግዚትነት፣ ምግብ ዝግጅት ህክምናና ሌሎች ተግባሮችን ለመከወን ደግሞ አቶ ሹሜ [በምግብ ቤት ተቆጣጣሪነት]ና ሌላኛው ስሜ አይጠቀስ ያሉትን አዛውንት ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰባሰቡ። እናም የተሰባሰቡት ሰዎች ቀስ በቅስ እየተግባቡ ሄዱ። አንዳንዶቹም ተጋቡ። ተዋለዱ።
“ሁሉም ከተለያየ አቅጣጫ የመጣ ነው። ትንሿ ኢትዮጰያ ማለት ይቻላል የሌለ ብሄረሰብ የለም” ይላሉ አቶ ሹሜ። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣም በኋላ አምባው እስከ 1989 ዓ.ም ቆየ። በ1989 ዓ.ም ህጻናቱም ወደ ተለያየ ማዕከላት እንዲዘዋወሩ ተደርጎ አምባው ተዘጋ። የአካባቢው እንቅስቃሴ ተቀዛቀዘ። የተሰወኑ ሠራተኞች ተቀነሱ። ከአመታት በኋላ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር አላጌ የጦር ጉዳተኞች መንከባከቢያ ማዕከል ሆነ።
በህጻናት አምባው ሲሰሩ የነበሩና ኑሯቸውን ያቀኑ ዜጎች በማዕከሉ በተለያዩ መደቦች ስራ ጀምረው ኑሮ ቀጠለ። በ1994 ዓ.ም ደግሞ ማዕከሉ ወደ ግብርና ኮሌጀነት ተቀየረ። አሁንም የተለያዩ ሰራተኞች ቢቀነሱም ቀድሞ በህጻናት አምባና በጦር ጉዳተኞች ማዕከል ሲሰሩ የነበሩ እንዲሁም አዳዲስ ሠራተኞች ስራ ጀመሩ። በሰፋፊ እርሻዎች ላይ በተለያየ ሙያ እንዲሁም የከብት፣ የዶሮና የአሳማ ርባታ ከተሰማሩባቸው መስኮች የሚጠቀሱ ናቸው።
አቶ ሹሜ በሶስቱም ተቋማት ከሰሩ ሰዎች መካከል ናቸው። ጡረታ ወጥተው አሁንም በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችም አሉ። በዚህ ሁሉ መሃል ግን በምርጫና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች የሚጋፈጧቸው ችግሮች መልክ ሳይዙ ድፍን 30 ዓመታት ተቆጥሯል። ታዲያ ይህ ነዋሪዎችን ከመምረጥ መብት የገታና ለውጣ ውረድ የዳረገ አስተዳደራዊ ገጽታ በነዋሪዎቹ ላይ የተለየ ስሜት እየፈጠረ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።
አራት አስርት አመታት የኖሩት ግለሰብ “እንደሮ ዕቃ አስታዋሽ የለንም” ሲሉ ሰሜ አይጠቀስ ያለው ወጣት ደግሞ “እንደ ዜጋ እንዴት ይህን መብት አጣለሁ እያልኩ እቆጫለሁ። መፍትሄው መራቁ ደግሞ በጣም ይሰማል” ይላል። ኑሮ በአላጌ በዚህ መልክ ቢቀጥልም ለነዋሪዎች ያልተመቸው አስተዳደራዊ እንቅፋት ግን መቼ መልስ እንደሚያገኝ ማንም ‘ርግጠኛ የሆነ አይመስልም።
ምንጭ – ቢቢሲ