አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሰሞኑን ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተባለ

የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ የሆኑት አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በትግራይ ክልል ቀውስና በሌሎች የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ መወያየታቸውና የትግራይ ክልል ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም መጠየቃቸው ተገለጸ። አንቶኒ ብሊንከንና ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ትኩረት እንደተሰጠው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

በውይይቱ ወቅትም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ አንቶኒ ብሊንከን፣ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንደሚወጣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት የገቡት ቃል በፍጥነትና ሊረጋገጥ በሚችል መልኩ መተግበር እንዳለበት ማሳሰባቸውን መግለጫው ያመለክታል።በትግራይ ክልል እየተባባሰ ነው ላሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰብዓዊ ቀውስ፣ የኤርትራ ጦርና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሚና እንዳላቸው በመጥቀስ፣ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በፍጥነት መቆም እንደሚገባው ለጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ (ዶ/ር) ማሳወቃቸው ተገልጿል።

ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እንደሆኑና በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የፖለቲካ አለመረጋጋት አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ ወደ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሊሻገር እንደሚችል መግለጻቸውንም መረጃው ያመለክታል።በዚህ አካባቢ ያለው ቀውስ የአሜሪካ መንግሥትን በእጅጉ የሚያሳስብ ጉዳይ በመሆኑ፣ ለአካባቢው ልዩ መልዕክተኛ መመደባቸውንና ልዩ መልዕክተኛውም ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ አስታወቀዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት በተለያዩ አገሮች የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ፌልማን ሲሆኑ፣ ልዩ መልዕከተኛው የአሜሪካ መንግሥት ማሳሰቢያዎች በፍጥነት የማይተገበሩ ከሆነ ሊወሰድ የሚችለውን ውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በግለጽ እንደሚያሳውቁ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ቢሮ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

ልዩ መልዕከተኛው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለረዥም ጊዜ በዲፕሎማትነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ የካበተ ልምድ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።ከአንድ ወር በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚስተዋለውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አስመልክቶ በተደረገ የበይነ መረብ ውይይት ላይ ተናጋሪ የነበሩት አምባሳደር ፌልማን (ልዩ መልዕክተኛው) በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት ከአፍሪካ ቀንድ ጋር ካልተሳሰረ ውጤታማነቱ የተሟላ እንደማይሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በመሆኑም የመካከለኛው ምሥራቅ ችግርን ለመፍታት በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትን ማስፈን አስፈላጊ እንደሆነና በአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ ሁኔታን ለመፍጠርም ግብፅና ቱርክን ማሳተፍ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።አምባሳደር ፌልማን የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሰየሙት ከአንድ ሳምንት በፊት ሲሆን፣ በዚህ ተልዕኳቸው በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ያለውን አለመረጋጋት ለመፍታት እንዲሁም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያለው ውዝግብ መፍትሔ እንዲያገኝ ዲፕሎማሲያዊ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *