በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ታጣቂዎች በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣን ገለጹ።

በጥቃቱ በሰው ላይ የደረሰ የጉዳት መጠንን እስካሁን እንዳልታወቀ የገዢው ፓርቲ የአካባቢው ባለስልጣን አቶ አማረ ኪሮስ የተናገሩ ሲሆን፤ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪ ግን 16 ሰዎች መገደላቸውን እንደሚያውቁ ገልጸዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው የአማራ ክልል ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰንበት የዋግ ኽምራ ዞን ውስጥ በምትገኘው የአበርገሌ ወረዳ ኒሯቅ ከተማ ላይ ነው።

የአበርገሌ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ ለቢቢሲ እንደገለጹት ጥቃቱ ሰኞ ዕለት ሚያዝያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ማለዳ 11፡00 ሰዓት አካባቢ የተፈጸመ ሲሆን፤ በጥቃቱ የሰላማዊ ነዋሪዎች እና የጸጥታ ኃይል አባላት ሕይወት አልፏል። ጎህ ከመቅደዱ በፊት በታጣቂዎቹ የተከፈተውን ጥቃት ተከትሎ የተካሄደው የተኩስ ልውውጥም ለሰዓታት ቆይቶ እስከ ቀኑ 8፡00 ድረስ ቀጥሎ እንደነበር ኃላፊው ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው በህወሓት ታጣቂ ኃይሎች መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ “ወደ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤትም የገቡ ስለነበሩ አሰሳ እየተደረገ ነው” በማለት በጥቃቱ የደረሰው የጉዳት መጠን ገና እየተጣራ መሆኑን አስረድተዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ስሜ አይጠቀስ ያሉ የኒሯቅ ከተማ ነዋሪም እንዳሉት ጥቃቱ እሁድ ለሰኞ ንጋት 11፡30 ገደማ መፈጸሙን ጠቅሰው 16 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ በነዋሪዎች ላይ ከፈጸሙት ጥቃት በተጨማሪ በንብረት ላይ ውድመትና ዘረፋ እንደፈጸሙ አቶ አማረ ገልጸዋል። በዚህም “አራት የመንግሥት መኪና፣ ሦስት አምቡላንስ፣ እንዲሁም ሌላ የግል መኪና ተቃጥሏል፤ የመድኃኒት ዘረፋም ተፈጽሟል።” ብለዋል። የዓይን እማኙም በንብረት ላይ ስለደረሰው ጉዳት “በአንድ ቦታ ላይ ቆመው የነበሩ 5 የመንግሥት የጤና አምቡላንስና መኪኖችን በቦምብ ተቃጥለዋል” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በአካባቢው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በመኖሩ ጥቃቱን መመከት በመቻሉ የከፋ ጉዳት አለመድረሱን የገለጹት አቶ አማረ፤ አስክሬናቸውን ቶሎ በማንሳታቸው ቁጥራቸው በውል አይታወቅ እንጂ ጥቃቱን ከፈጸሙት “የህወሓት ታጣቂዎች መካከል በርካቶቹ ሞተዋል” ብለዋል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ኢላማቸው ምን እንደሆነ በውል ባይታወቅም ቀደም ብለው የአመራር ቤቶችን እየጠየቁ ስም ዝርዝር ይይዙ እንደነበር ኃላፊው ገልጸዋል።

ነገር ግን “ጥቃቱን የመፈጸሙት ታጣቂዎች በሄዱበት ቦታ የፈለጓቸውን የአካባቢውን አመራሮች አላገኙም። በሁለት ንፁሃን ዜጎች ላይ ግን ቤት ውስጥ በመግባት ጉዳት አድርሰዋል” ብለዋል። አበርገሌ ከተማ ከትግራይ ክልል ጋር የምትዋሰን ከተማ ስትሆን ከአበርገሌ አልፎ በትግራይ ክልል ውስጥ ወደሚገኝ የገጠር አካባቢ ለመድረስ ሰባት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት አለው።

የከተማው ነዋሪ ጥቃቱ ስለተፈጸመበት ሁኔታ ለቢቢሲ እንዳስረዱት ታጣቂው ኃይል በቡድን ተከፋፍሎ በሦስት አቅጣጫ ወደ ከተማው መግባቱን ተናግረዋል። በዚህም “ከከተማው በምሥራቅ በኩል [በገበያው በኩል]፣ ከትግራይ ጋር በሚዋሰነው ቦታ እና በምዕራብ በኩል ባለው የቤተክርስቲያኑ አቅጣጫ በኩል በመግባት ጥቃቱን አድርሷል።” ብለዋል። የዓይን እማኙ እንዳሉት ጥቃት ፈጻሚዎቹ ታጣቂዎች “የመገናኛ ራዲዮ የያዙ ናቸው።”

“የመጀመሪያ ኢላማ ያደረጉት በከተማዋ ውስጥ ያሉ አመራሮችን ማጥቃት ነበር” የሚሉት ነዋሪው፤ “የአንድ አመራር የቅርብ ጓደኛ እንዲሁም አንዲት ሴት ከነልጆቿ ቤት ውስጥ ሳሉ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል” ብለዋል። በአካባቢው የአማራ ልዩ ኃይል ስለነበር ጥቃቱን ተከትሎ ውጊያ በመከፈቱና አመራሮቹም በወቅቱ ቤታቸው ስላልነበሩ ሊተርፉ እንደቻሉ ነዋሪው አስረድተዋል።

ነዋሪው ቁጥሩን በውል አይወቁት እንጂ በጥቃቱ የአካባቢው ሚሊሻ አባላትም መገደላቸውንና ከህወሓት ታጣቂ ኃይሎችም በርካቶች መገደላቸውን ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ “ታጣቂዎቹ በሥፍራው ከነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ጋር በከፈቱት ተኩስ የሞቱባቸውንና የቆሰሉባቸውን ሰዎች ወደ በርሃ አድርሱ ተብለው የተገደዱ የአካባቢው ነዋሪዎችም እስካሁን አልተመለሱም” ብለዋል።

እነዚህ በታጣቂዎቹ ተገደው የተወሰዱት ነዋሪዎች “እስካሁን የት እንዳሉ አይታወቅም፤ ተገድለዋል ይባላል። ተርፈን መጣን ያሉ ሰዎችም ቀሪዎቹ እንደተገደሉ ነው የሚያወሩት” ሲሉም የሟቾቹ ቁጥር እርሳቸው ከጠቀሱት በላይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። በዕለቱ እስከ 5 ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ውጊያ ነበር ያሉት ነዋሪው፤ ታጣቂዎቹ እንዲወጡ መደረጉንና ከዚያ በኋላ ተኩስ መቆሙን ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት አበርገሌ መግባቱንም ነዋሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ ከትግራይ ክልል ፊናርዋ ከሚባል ቦታ የሚመጣውን የመከላከያ ሠራዊት መንገድ ዘግተው ውጊያ ከፍተው እንደነበር የገለጹት ነዋሪው፤ ሠራዊቱ ወደ አበርገሌ መግባት የቻለው ረቡዕ ዕለት መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን በአካባቢው የጸጥታው ሁኔታ የተረጋጋ ቢሆንም ነዋሪዎች ግን ስጋት አላቸው። የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ አማረ በአካባቢው የመከላከያ ኃይል መግባቱን በመግለጽ፤ አካባቢው መረጋጋቱንና ከዚያ በኋላ ያጋጠመ ግጭትም ሆነ ጥቃት አለመኖሩን ተናግረዋል።

በዚሁ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፃግብጂ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ወር መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በታጣቂዎች በተፈጸመ ተመሳሳይ ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች ደግሞ የመቁስል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል።የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሄኖክ ነጋሽ በወቅቱ በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጥቃት የ76 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ እንደተረጋገጠ ገልጸው ሰላማዊ ሰዎችም በጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

በአማራ ክልል የሚገኘው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፤ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ላይ “ሕግን ማስከበር” ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ ካካሄደበት የትግራይ ክልል ጋር በቅርብ ርቀት የሚጎራበት አካባቢ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *