ከምሰል ማኅደር የተገኘ ፎቶ

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎችን መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ጥቃቱ አርብ ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም ሊሙ ኮሳ ወረዳ፣ ቀጮ ክርክራ እና ጋሌ በተባሉ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈጸመ ሲሆን ቢያንስ 20 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ለቢቢሲ ገልጿል። ኮሚሽኑ አክሎም ይህንን ቁጥር በገለልተኛ ወገን አለማጣራቱን ጠቅሶ አካባቢው አስተዳደር መረጃውን ማግኘቱን አመልክቷል። በተመሳሳይ እንዲሁ ሐሙስ ሚያዝያ 14/2013 ዓ.ም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ፣ ዳኖ ቀበሌ ውስጥ በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን ኮሚሽኑ ጨምሮ አመልክቷል።

የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ኢማድ ቱኔ እንደተናገሩት በጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች የደረሱት ታጣቂዎቹ ጥቃት ፈጽመው በስፍራው በርካታ ንፁሃን ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው። ቢሆንም ግን ከዚያ ክስተት በኋላ በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ ለመከላከል መቻላቸውን ጠቅሰው ባለፉት ቀናት የፀጥታ ኃይሎች በተለይም በጅማ ዞን ተሰማርተው ጥቃቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ ጥቃቶቹን ተከትሎ ወደ አካባቢዎቹ ባለሞያዎችን ለማሰማራትና የደረሰውን ጉዳት በትክክል ማጣራት አለመቻሉን አቶ ኢማድ ቱኔ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ከአካባቢው ባሰባሰበው መረጃ በጅማ ዞን የተፈጸመው ጥቃት የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የሚያመለክት መረጃ እንዳገኘ አቶ ኢማድ ገልጸዋል። ቢቢሲ ጥቃት ከተፈጸመበት አካባቢ ነዋሪዎች፣ ከዞኑ እንዲሁም ከወረዳው አስተዳዳሪዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

በተመሳሳይ ኮሚሽኑ ጥቃት እንደተፈጸመበት የተገለጸው የአማሮ ልዩ ወረዳ የሰላም እና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኤሊያስ ይልማ ጉዳትና ዝርፊያ መፈጸሙን አረጋግጠዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ በጥቃቱ ከብት ጥበቃ ላይ የነበረ አንድ ግለሰብ መገደሉን እንዲሁም ከ70 በላይ ከብቶች በታጣቂዎቹ ተነድተው መወሰዳቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።ይህን ጥቃት የፈፀሙትም ከአጎራባች ቀበሌ የተነሱ ሽፍቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ጨምረውም ባለፉት አራት ዓመታት በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በአጎራባች የቡሌ ሆራ ዞን ሲያጋጥም የነበረው ጥቃት ከታጠቁ ኃይሎች ወደ ኅብረተሰቡ አድጓል ሲሉም አብራርተዋል። አቶ ኤልያስ አንደሚሉት የአማሮ ወረዳ 17 ቀበሌዎች በእነዚህ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች መጎዳታቸውን አመልክተው፤ “ከሁለት ቀበሌዎች ደግሞ የመንግሥት መዋቅርን ጨምሮ ነዋሪዎች ጥለው መውጣታቸውን” በመጥቀስ በአጠቃላይ በአካባቢው ስላለው የጸጥታ ሁኔታ አብራርተዋል።

በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር አራት ዓመት እንዳስቆጠረ የሚናገሩት ኃላፊው፤ ከዚህ ቀደም የሁለቱም የወረዳ አመራሮች ችግሩን ለመፍታት ተወያይተው እርቀ ሰላም መፈጸማቸውን አስታውሰዋል። ባለፉት አራት ዓመታት በአማሮ ወረዳ ከ150 በላይ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን እንዲሁም 158 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አክለው ተናግረዋል። በየካቲት ወር በዚሁ የአማሮ ልዩ ወረዳ ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የወረዳው የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊና አንድ የፖሊስ ባልደረባን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ሰዎቹ የተገደሉት ልዩ ወረዳውን ከኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂ ዞን በሚዋስነውና ዳኖ በተባለ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነበር። ጥቃቱ የፈጸመው የአማሮ እና የጉጂ ተጎራባች ነዋሪዎች በእርቅ ጉዳይ ላይ ለመምከር ከአገር ሽማግሌዎች እና ከሁለቱ አካባቢዎች የተወጣጡ አመራሮች በተሰበሰቡበት ወቅት ነው። በጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ የተፈጸመውን ጥቃት በዝርዝር ለማወቅ እየጣረ ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍተኛ አማካሪ ጥቃት ፈጻሚው ኃይል በውል አለመለየቱን ገልጸዋል።

ጥቃቶቹ በታጠቁ ኃይሎች የተፈጸሙ መሆናቸውን አመልክተው መንግሥት ተጣያቂው ኦነግ-ሸኔ ነው እንደሚል ነገር ግን ኢሰመኮ ግን በገለልተኛ ወገን የተጣራ መረጃ እንደሌለው አቶ ኢማድ ተናግረዋል። ጥቃቱን የፈጸመው “ማንም ይሁን ማን አንድም ንጽህ ሰው መገደል የለበትም” ብለዋል። ከዚህ በፊት በሊሙ ኮሳ ወረዳ ተመሳሳይ ጥቃት ስለመኖሩ መረጃው እንደሌላቸው የተናገሩት ኃላፊው፤ ነገር ግን በጅማ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ወረዳዎች ታጣቂ ኃይሎች መንቀሳቀስ መጀመራቸውን እና ጥቃቶች እንደነበሩ ከሦስት ሳምንት በፊት መረጃ እንደነበራቸው ገልጸዋል።

የኢትዯጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርብ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ በተመሳሳይ ጥቃቶች የተከሰቱ ሞቶችን፣ የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት መውደምን ደጋግሞ ይፋ አድርጓል። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት እነዚሀ ጥቃቶች እየተባባሱ ሲሄዱ እንጂ መሻሻል አለመታየቱን አቶ ኢማድ ጠቅሰው፤ “መፍትሄው መንግሥት ችግሮችን ከዚህ ቀደም ለመፍታት ከሞከረበት መንገድ የተለየ መንገድ መሞከር ይኖርበታል” ሲሉ መክረዋል።

ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የብሔር ማንነትን የለዩ በታጣቂዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ሲደርሱ የተስተዋሉ ሲሆን በተለይ በዚህ ዓመት ባለፉት ጥቂት ወራት እየከፉ መምጣታቸውን ሲወጡ የነበሩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ ቤኒሻልጉልና በደቡብ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ ባለፉት ወራት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል።

በቅርቡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ውስጥ በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች 500 የሚደርሱ ሰዎች ህይወት ማለፉንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኤኤፍፒ እና ሮይተርስ የዜና ወኪሎች በተለያዩ ጊዜያት ያወጥዋቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በተጨማሪም መጠኑ በትክክል እስካሁን ያልታወቀ በመኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ተቋማት፣ በተሽከርካሪዎችና በሌሎች ንበረቶች ላይ ከባድ የሚባል ውድመት መድረሱን የአካባቢዎቹ ኃላፊዎች ይናገራሉ። እነዚህ ጥቃቶች አገሪቱ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ጥቂት ወራት በቀሯት ጊዜ ከሌላው ወቅት በተለየ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ይገኛል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *