የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ

ቦርዱ አብንንና ብልፅግና ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎቹንም አስጠነቀቀ

የመራጮች ምዝገባ እስከ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ተራዘመ

እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 .ም. ድረስ 18,427,239 ዜጎች ተመዝግበዋል

ብልፅግና ፓርቲ ሰሞኑን በአማራ ብሔራዊ ክልል የተካሄዱትን የተለያዩ ትዕይነተ ሕዝቦች በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ መጠራታቸውንና በእነዚህም ሠልፎች ላይ የብልፅግና ፓርቲ ቢልቦርድና ባነሮች መቀደዳቸውን ገልጾ በላከው የቅሬታ ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድለት ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ቦርዱ ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓርብ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ ኢትዮጵያ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሒደት ተግባራት መካከል ትገኛለች። የምርጫ ሒደት ከፍተኛ እንቅስቃሴ፣ ፉክክርና ክርክር እንደሚኖረው ይታወቃል። በዚህም መሠረት የፓለቲካ ፓርቲዎች በነፃ የአየር ሰዓት፣ በአደባባይ ቅስቀሳዎች እንዲሁም፣ በምርጫ ክርክሮች እየተሳተፉ እንደሆነ ይታወቃል። ሰሞኑን በአማራ ብሔራዊ ክልል የተለያዩ ትዕይነተ ሕዝቦች መከናወናቸው አስታውሶ፣ የብልፅግና ፓርቲ ከሠልፉ ጋር በተያያዘ ለቦርዱ ቅሬታ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ለቦርዱ በላከው የቅሬታ ደብዳቤ፣ ሠልፎቹ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ መጠራታቸውንና በእነዚህም ሠልፎች ላይ የብልፅግና ፓርቲ ቢልቦርድና ባነሮች መቀደዳቸውን ገልጾ፣ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድለት ጥያቄ ማቅረቡንም አውስቷል፡፡

ቦርዱ አቤቱታውን መሠረት በማድረግ ሁኔታውን መመርመሩን ገልጾ፣ ብልፅግና ፓርቲ ባቀረበው አቤቱታ ላይ አብን ለሠልፎቹ ጥሪ ማድረጉን ቢገልጽም፣ በተያያዘው ደብዳቤም ሆነ በቀረቡት ማስረጃዎችም ሆነ ቦርዱ ባከናወነው የሚዲያና የማኅበራዊ ሚዲያ ማጣራት፣ ሠልፎቹ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መጠራታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘት አለመቻሉን ተናግሯል።

በዚህም የተነሳ ሠልፎቹ ከምርጫ ወይም ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላገኘባቸው በተከናወኑት ሠልፎች ላይ የተንፀባረቁ ሐሳቦች፣ መፈክሮችና ተያያዥ ጉዳዮችን መመርመር አላስፈለገውም። ነገር ግን ሁነቶቹን አስመልክቶ በሚዲያና በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጩ ከሠልፉ ጋር የተያያዙ የፓለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎችን እንቅስቃሴዎችን ክትትል ሥራ በቦርዱ መከናወኑን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሠልፎቹን ተከትሎ ባወጣቸው መግለጫዎች ጥላቻ አዘል ንግግሮችን፣ ግጭትን ሊያባብሱ የሚችሉ አገላለጾችን የሚጠቀሙ ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ከምርጫ ፉክክር መንፈስና ሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ፣ በሕግ የተቀመጡ በምርጫ ወቅት ተቀባይነት የሌላቸው አገላለጾችን (ንግግር) መጠቀሙን አስረድቷል፡፡

ፓርቲው ሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋዊ ፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ‹‹የኢሕአዴግ አማራ ጠል ትርክትና የዚሁ ውሉድ የሆኑ የጥላቻ ፖሊሲዎች፣ አሠራሮች፣ ሕግጋትና መዋቅሮች ቀጥተኛ ወራሽ የሆነው ፋሺስታዊ ተረኛ ኃይል በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች…›› የሚል በተፎካካሪ አካላት ላይ የሚደረግ ጥላቻን ያዘለ፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆነና ሰብዕናን የሚነካ ንግግር ማስተላለፉን ጠቁሟል፡፡

አብን ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ‹‹በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ባልተቋረጠ መልኩ የሚፈጸሙት መንግሥት መራሽ የዘር ፍጅቶች በገለልተኛ ኮሚሽን በጥልቀት ተጣርተው…›› የሚል ግጭትን የሚያነሳሳ ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ክስ መቅረቡንም አክሏል፡፡ ሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ፣ ‹‹መላው የአማራ ሕዝብም የተከፈተበትን አጠቃላይ የህልውና አደጋ በመገንዘብና ለደኅንነቱ የሚያስብለት መንግሥት እንደሌለው በመረዳት፣ ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲሠራበት አብን በአጽንኦት ያሳስባል›› የሚል ኃይል መጠቀምንና ግጭትን የሚያነሳሳ ንግግር ማስተላለፉን ጠቁሟል፡፡

ከላይ የተገለጹት የአብን አገላለጾች የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/20111 አንቀጽ 132 (2ሀ እና ለ) ላይ የተቀመጡትን ማንኛውም ውድድር ውስጥ ያለ አካል ግጭት ቀስቃሽ የሆነ ወይም የግል ስብዕናን የሚነካ ቋንቋ ማስወገድ አለበትና በማንኛውም መልኩ ለአመፅ የሚጋብዝና በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ሥጋትን የሚጭር የቋንቋ አጠቃቀም ማስወገድ አለበት የሚሉትን ድንጋጌዎች ባወጣቸው መግለጫዎች ጥሷል።

ከዚህም በተጨማሪ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ስላለው የቋንቋ አጠቃቀምን የሚደነግገው የምርጫ ሥነ ምግባር መመርያ አንቀጽ 20(8) ላይ የተጠቀሰው፣ ‹‹የምርጫ ውድድር ቅስቀሳ በሚያደርግበት ጊዜ በማንኛውም ሰው ላይ ጥላቻን ወይም የኃይል ተግባር እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ንግግር ወይም ጽሑፍ በበራሪ ወረቀት፣ በፖስተር ወይም በፎቶግራፍ ከማስተላለፍ መቆጠብ አለበት›› የሚለውን ድንጋጌ ተቃራኒ የሆኑ መግለጫዎችንም አውጥቷል።

በመሆኑም እነዚህ መግለጫዎች በምርጫ ዘመቻ መካከል መደረጋቸው የምርጫውን ሰላማዊነት ከመጉዳቱም ባሻገር ያልሠለጠነ ፉክክርን ያበረታታል፡፡ ይህም ቦርዱን በእጅጉ አሳስቦታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ከዚህ ዓይነት ተግባር እንዲቆጠብ በአጽንኦት እያሳሰበ፣ ተመሳሳይ መልዕክቶች ሥርጭት የሚቀጥል ከሆነ ዕጩ እስከ መሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል። በሌላ በኩል በዚሁ ሁነት ዙሪያ ንግግርና መግለጫ የሰጡት ኢዜማ፣ ብልፅግና፣ ኦፌኮና ሌሎች ፓርቲዎች ዕጩዎች ንግግሮችን ላይም ክትትል ማድረጉን ተናግሯል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች በምርጫ ሕጉና በምርጫ ዘመቻ ሥነ ምግባር ደንቡ እንደሚገዙ እየታወቀ፣ በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ጥላቻን ያዘሉ ንግግሮችን እንዳያስተጋቡ ቦርዱ ማስተዋሉን ጠቁሟል፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ዕጩና ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በይፋ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ሲገልጹ፣ ‹‹ዋነኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ካንሰር የሆነው አብን ትናንት ባህር ዳር ላይ …›› በሚል አገላለጽ የተጠቀሙ ሲሆን፣ ፓለቲካ ፓርቲውን ‹‹…ወንድማማቾችን ያገዳደለው ራሱ አብን መሆኑን በትክክል ይረዳል…›› በማለት ያልተረጋገጠ ክስም መቅረባቸውን ጠቁሟል፡፡

ይህም ከተወዳዳሪ ዕጩዎች የሚጠበቀውን ‹‹ግጭት ቀስቃሽ የሆነ ወይም የግል ስብዕናን የሚነካ ቋንቋ ማስወገድ አለበትና ‹‹በማንኛውም መልኩ ለአመፅ የሚጋብዝና በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ሥጋትን የሚጭር የቋንቋ አጠቃቀም ማስወገድ አለበት፤›› የሚሉትን ድንጋጌዎች የጣሰ ነው። በተለይ ዕጩዎች በመሰል ንግግሮች የምርጫ ሒደቱን ሥጋት ላይ መጣል አግባብ አለመሆኑን መረዳት እንደሚገባቸው ቦርዱ በአጽንኦት ተናገሯል፡፡

ዕጩዎች በግልም ሆነ በፓርቲ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት መከተል ያለባቸውን ሥነ ምግባር ደንቦች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ አሳስቦ፣ ተመሳሳይ ጥሰት በሚፈጽሙ ዕጩዎችም ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን እስከ መውሰድ ሊደርስ እንደሚችል ያሳውቃል።

በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጩ ምሥሎችና ቪዲዮዎች እንደሚያስረዱት፣ በብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮች ተቀደዋል። ይህ ተግባር በማንም አካል ቢፈጸም በምርጫ ሕጉ 1162/2011 መሠረት የምርጫ ወንጀል ነው። ዜጎች በተለያየ መልኩ ሐሳባቸውን በሚገልጹበት ወቅት የምርጫ ሒደቱን ከሚያውኩ የሥነ ምግባር ጥሰቶችና ተመሳሳይ ወንጀሎች እንዲቆጠቡ፣ ፓርቲዎችም ዕጩዎቻቸው፣ አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ እንዲያስተምሩና እንዲያሳስቡ ቦርዱ አስገንዝቧል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት የመራጮች ምዝገባ ዓርብ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ የተከናወነው የመራጮች ምዝገባ ሒደት በተለያዩ ክልሎች በተለያየ ደረጃ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡  በሶማሌና በአፋር ክልል የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ ሲጀመር በሌሎች ክልሎች ደግሞ ቀደም ብሎ ሲከናወን መቆየቱን በምሳሌነት ጠቁሟል፡፡

የመራጮች ምዝገባ ቀደም ባሉት ሳምንታት ቦርዱ ካሳወቀበት ደረጃ በላይ በከፍተኛ ደረጃ የተሻሻለ ሲሆን፣ የምርጫ ጣቢያዎች ያልተከፈቱባቸው የአፋር ብሔራዊ ክልልና የሶማሌ ብሔራዊ ክልልም የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባን ማከናወን ጀምረዋል። በጥቅሉ ሲታይም እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 .ም. ድረስ 18 ሚሊዮን 427,239 ዜጎች (18,427,239) የተመዘገቡ ሲሆን፣ በ41,659 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡

ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ቀን ማጠናቀቂያ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በሥራ ሒደቱ ያጋጠሙትን ችግሮች መርምሯል። በዚህም መሠረት የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ በመጀመሩ፣ በጊዜው በተጀመረባቸውም ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ መረጃዎች ዕጦትና በሌሎች ምክንያቶች ለመመዝገብ ጊዜ በመውሰዱ፣ የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቁ በቀሩት ጥቂት ቀናት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1,500 ሰው ብቻ መመዝገብ በመቻሉ የተነሳ፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ በመቋረጡና ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች በመክፈት ሒደት ክፍተት በመፈጠሩ፣ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም ወስኗል።

የመራጮች ምዝገባ እጅግ ዘግይቶ በጀመረባቸው በአፋርና በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ለሦስት ሳምንት መራዘሙን አስታውቋል፡፡ ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ የመራጮች ምዝገባ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በተስተጓጎሉባቸው ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ለሁለት ሳምንት መራዘሙን ተናግሯል፡፡ በመሆኑም የመራጮች ምዝገባ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ መሆኑንም አክሏል፡፡

የመራጮች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸውና የፀጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩና ቄለም ወለጋ የመራጮች ምዝገባን የማስጀመር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝና አሊቦ – ሆሮ ጉድሩ፣ ኮምቦልቻ – ሆሮ ጉድሩ፣ ጊዳም – ሆሮ ጉድሩ፣ አያና – ምሥራቅ ወለጋ፣ ገሊላ – ምሥራቅ ወለጋ፣ ቤጊ – ምዕራብ ወለጋ፣ ሰኞ ገበያ – ምዕራብ ወለጋ የመራጮች ምዝገባ አሁንም የማይጀመር መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ ውጪ ባሉት ወረዳዎች የመራጮች ምዝገባን ለመጀመር የቁሳቁስ ሥርጭት እየተከናወነና የአስፈጻሚዎች ሥልጠናም እየተሰጠ መሆኑን፣ በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከማሽ ዞን ከሰጎን ወረዳ ውጪ የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ የቁሳቁስ ሥርጭትና የአስፈጻሚዎች ሥልጠና እየተከናወነ እንደሆነ ተናግሯል።

በመሆኑም በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም አማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን ያሉ የምርጫ ሥራ የቆመባቸው ቦታዎችን ጨምሮ እንደየሁኔታው በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ የሚጀመርበትን ሁኔታና ቀናት ቦርዱ እንደሚያሳውቅ ጠቁሟል፡፡ 1,500 ሰዎችን መዝግበው በጨረሱ ምርጫ ጣቢያዎች ተጨማሪ ንዑስ ምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *