ከሳምንት በፊት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ውስጥ በተከሰተ “ግጭት እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች” ሳይሞቱ እንዳልቀረ ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ዘገበ።

ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣናት ባለፉት ቀናት እንደተናገሩት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊ አቶ እንዳለ ኃይሌ ለሮይተርስ እንደተናገሩት “ከተፈናቀሉ ሰዎች ያገኘነውን መረጃ መሠረት አድርገን እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች ከሁለቱም ዞኖች ሳይሞቱ አይቀሩም” ብለዋል።

ኃላፊ ጨምረውም ይህ የተጠቀሰው የሞቱ ሰዎች አሃዝን የበለጠ ማረጋገጥ እንደሚፈልግም አመልክተዋል። በቅርብ ጊዜ በተከሰተው ጥቃት ክፉኛ ከተጎዱት አካባቢዎች መካከል ዋነኛዋ በሆነችው በአጣዬ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ቤቶች ውስጥ ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆኑት በእሳት መጋየታቸውን አቶ እንዳለ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከሰሜን ሸዋ ዞን 250 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንዲሁም 78 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። ሮይተርስ እንደዘገበው በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ የምትገኝ አንዲት ትንሽ ከተማ በመጋቢት ወር ሙሉ ለሙሉ መውደሟን አቶ እንዳለ እንደተናገሩ ጠቅሶ ነገር ግን ስለደረሰው ጉዳት ተጨማሪ ዝርዝር እንዳልሰጡ አመልክቷል።

ጥቃቱን ተከትሎ የክልሉና የዞኖቹ ባለሥልጣናት ለተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን፤ ትክክለኛ አሃዝ እንደሌላቸው ነገር ግን በሰውና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን መረዳታቸውን ገልጸው ነበር። ባለፈው ሳምንት በጥቃቱ በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ከሰሜን ሸዋ ዞኑ አስተዳደር መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ በሞከረበት ጊዜ የአካባቢው ኃላፊዎች በቀዳሚነት የተፈናቀሉትን በመርዳት ወደመኖሪያቸው ለመመለስ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ጎን ለጎንም መረጃ እያሰባሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር በአካባቢው በተከሰተ ጥቃትና ግጭት ተመሳሳይ ከባድ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በክስተቱ ከ300 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ኤኤፍፒ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋምን ባለስልጣንን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

ሰሜን ሸዋ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ ቀደም ሲል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ አርብ ሚያዝያ 08/2013 ዓ.ም በተፈጸሙ ጥቃቶች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። በወቅቱ የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ኃላፊ አቶ አበራ መኮንን ለቢቢሲ እንደገለጹት ጥቃቱ የተፈፀመው በዞኑ ውስጥ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ላይ ሲሆን “በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የታጠቀ ኃይል ወረራ” ፈጽሞ ጉዳት አድርሷል ብለው ነበር።

በጥቃቱ ወቅት የታጣቂው ኃይል በሰዎችና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አመልክተው ክስተቱ በአካባቢው ከነበረው የፌደራልና የክልሉ የጸጥታ ኃይል “አቅም በላይ” መሆኑንና በጸጥታ አካላት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ተቋም እንደተናገሩት በጥቃቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰና ለጥቃቱም “ኦነግ-ሸኔ እና ሌላ ተከታይ” ያሉትን አካል ተጠያቂ አድርገዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኙት አጣዬ፣ አንጾኪያና በኤፍራታ የሚባሉት ሲሆኑ፤ የአጣዬ ከተማ ከሁሉም በከፋ ሁኔታ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባት ከጥቃቱ በኋላ የሚወጡ ምስሎች አመልክተዋል። በወቅቱ በታጠቁ ኃይሎች የተፈጸመውን ጥቃት በመሸሽ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያቸውን በመተው ወደ ገጠር መንደሮችና በዙሪያቸው ወዳሉ ከተሞች መሄዳቸው መነገሩ ይታወሳል።

የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ተሰማርቶ ችግሩን ከተቆጣጠረ በኋላ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉት ነዋሪዎች የእለት ደራሽ እርዳታ ለማቅረና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ተገልጾ ነበር። ከሦስት ሳምንታት በፊት በአካባቢዎቹ በተፈፀመ ጥቃትና ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ክልከላ

በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እና በደቡብ ወሎ ውስጥ በሚገኙ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን መከልከሉን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቋል። በአማራ ክልል ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ የተከሰተውን የሠላም መደፍረስ ለመቆጣጠር የዕዝ ማዕከል [ኮማንድ ፖስት] መመስረቱን የገለጸው መከላከያ ሚኒስቴር ፤ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ውስጥ በታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸሙ ጥቃትን ለመከላከል የተወሰደ እርምጃ መሆኑም ገልጿል።

በዚህም መሠረት የዕዝ ማዕከሉ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ ባለው መስመር አዋሳኝ ወረዳዎች ከመንገድ ግራና ቀኝ ባለው 20 ኪሎ ሜትር ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል አሳውቋል። በተጨማሪም በአካባቢዎቹ መንገድ መዝጋት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የግለሰብ መኖሪያና ንብረት ማውደም ወይም “ለዚህ ተግባር በተናጠልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ” መሆኑን ገልጿል።

ጥቃት በተፈጸመባቸውና የተቋቋመው የዕዝ ማዕከል መረጋጋትን ለማስፈን በሚንቀሳቀስባቸው በእነዚህ አካባቢዎች የተጣሉትን ክልከላዎች ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም አካል ላይ “ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት” ጨምሮ አስታውቋል። በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶችና ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ ሲሆን አሁን የተፈጸመው ግን እስካሁን ካጋጠሙት መካከል ሰፊ ቦታዎችን ከማዳረሱ በተጨማሪ ባስከተለው ጉዳት ቀደም ካሉት የከፋ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የአካባቢው ባለስልጣናት በአሁኑ ጊዜ የተፈናቀሉትን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስና ቀሪውን ነዋሪ ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ባለፉት ቀናት በተፈጸመው ጥቃት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ዝርዝር ለማወቅ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

የተቃውሞ ሰልፎች በአማራ ክልል

በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ከተሞች የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ይህንን ጥቃት በመቃወምና መንግሥት በሌሎች ክልሎች በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችናና ማፈናቀሎችን እንዲያስቆም የሚጠይቁ ሰልፎች ሲካሄዱ ሰንበተዋል። ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችና በተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ መስተዳደርና የፌደራል መንግሥቱ በአማራ ብሔር አባላት ላይ ባለፉት ዓመታት እየተፈጸሙ ናቸው ያሏቸውን ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።

የተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በርካታ ሕዝብ የተሳተፈባቸው ሲሆኑ በተለያዩ ቀናት ሲካሄዱ ቆይተዋል። በተጨማሪም በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ በተለያዩ ቀናት በተደጋጋሚ ተካሂደዋል። ሰልፉ በሰሜን ሸዋ ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት መነሻ ያደረገ ቢሆንም በተለያየ ጊዜያት በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀመውን ጥቃትም የሚያወግዝ እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሰልፉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *