በምዕራብ ኢትዮጵያ ቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ካማሺ ዞን ውስጥ የሚገኘው ሴዳል የተባለው ወረዳ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሰር መዋሉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ ታጣቂዎቹ ከሰኞ ሚያዝያ 11/2013 ዓ.ም ጀምሮ የሴዳል ወረዳን “ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መቆጣጠራቸውን” ደረሱኝ ያላቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ገልጿል። የካማሺ ዞን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደቡባዊ ክፍል ውስጥ የሚገኝ አካባቢ ሲሆን በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ወድቃለች በተባለችው የሴዳል ወረዳ ውስጥ ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

ታጣቂዎቹ በወረዳው ላይ በሰነዘሩት ጥቃትም የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች አካባቢውን ጥለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመሸሽ መገደዳቸውን ጨምሮ አመልክቷል። በጥቃቱም ወረዳውን የተቆጣጠረው ታጣቂ ቡድን የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የወረዳውን እንዲሁም የዞን አመራሮችን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞችን የገደለና ያገተ መሆኑን እንዲሁም የመንግሥት እና የግለሰብ ንብረቶችን ማውደሙን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ስለሁኔታው ያነጋገራቸው የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች የታጣቂው ኃይል በአቅራቢያ ካለው የመንግሥት ኃይል አቅም በላይ መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፍ ለመስጠት ተልኳል የተባለው ተጨማሪ የፀጥታ ኃይልም ወደ ስፍራው እንዳልደረሰ ተናግረዋል ብሏል። ኢሰመኮ በዚህ መግለጫው ላይ ጥቃት ፈጽሞ ወረዳዋን በመቆጣጠር ግድያና የተለያዩ ጥፋቶችን ስለፈጸመው ታጣቂ ኃይል ማንነት ያለው ነገር የለም።

የቤኒሻንጉል ክልል መንግሥት ረቡዕ እለት ባወጣው መግለጫ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች ሲከሰቱ “የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተባባሪዎቻቸው ወደ ባሰ ውጥንቅጥ እና የቀውስ አዙሪት ሊከቱን ጥረት ማድረግ ጀምረዋል” ብሏል። ጨምሮም እነዚህ አገሪቱን ወደ ባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ ለመክተት የሚጥሩ ያላቸው ነገር ግን ስማቸውን ያልገለጸው “የጥፋት ቡድኖች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል” ገልጿል።

የፌዴራል መንግሥቱም ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ “ጽንፈኛ ኃይሎች የሚያራምዱትን የጥፋትና የብጥብጥ አጀንዳ ሥርዓት እንዲያስይዝ” ጠይቋል። ነገር ግን ይህ የክልሉ መግለጫ በካማሺ ዞን ስለተፈጸመው ጥቃት በተለይ ያለው ነገር የለም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥት በአፋጣኝ የአካባቢውና የክልሉን የፀጥታ ኃይል በማጠናከር ተጨማሪ የሰዎች ሞትና የከፋ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት እንዲከላከል ጥሪውን አቅርቧል። :

ኮሚሽኑ እንዳለው “ይህ ክስተት በክልሉ የቆየው የጸጥታ ችግር እየተባባሰና መልኩን እየቀየረ መምጣቱን የሚያሳይ” መሆኑን ጠቅሶ ይህም ከፍተኛ ስጋት የሚያሳድር ክስተት መሆኑን አመልክቷል። ጨምሮም በአካባቢው የተከሰተውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንና ከሚመለከታቸው የፌዴራል እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ መንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን ገልጿል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚዋሰነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሦስት ዞኖች የሚገኙ ሲሆን እነሱም መተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ የሚባሉ ናቸው። በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰዎች ለሞትና ለመፈናቀል ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል። ከእነዚህም መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት የቆየው የመተከል ዞን በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ ይህንንም ለመቆጣጠር በሚል የክልሉና የፌደራል መንግሥት የጸጥታ አካላት በጥምረት የሚመሩት የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) በዞኑ ውስጥ ከተቋቋመ ወራት ተቆጥረዋል።

ከአራት ወራት በፊት ታኅሣሥ 14/2013 ዓ.ም በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ኢሰመኮን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ይህንና ሌሎች በሰላመዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ በክልልና በፌደራል መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በርካታ የታጠቁ ሽፍቶች እንደተገደሉ ተገልጾ ነበር።

የክልሉ መስተዳደር ጥቃቱን የሚፈጽሙት ጸረ ሰላም ኃይሎችና ሽፍቶች ናቸው ከማለት ውጪ ጥቃቱን የሚፈጽመው ኃይል ምን አይነት ቡድን አላማው ምን እንደሆነ አስካሁን በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን በበርካታ አካባቢዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚገደሉና የሚፈናቀሉ ሰዎችን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ድርጊቱ የብሔር ማንነትን የለየ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለእርሻ የሚውል ሰፊ ለም መሬት ያለበት አካባቢ ሲሆን ለዓመታት የዘለቀው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽን እያወዘገበ ያለው በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግዙፉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ክልል ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ ወደ 1.1 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይገኛል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *