በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ከተሞች በንፁኃን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት፣ ማፈናቀልና የንብረት ውድመት የሚያወግዙና ‹‹ሞት ይብቃ›› የሚሉ የተቃውሞ ሠልፎች በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ተካሄዱ፡፡ ሰሞኑን የተካሄዱት ሠልፎች በባህር ዳር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ሐይቅና ሌሎቸ ከተሞች ሲሆን፣ ‹‹በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያና መፈናቀል ይቁም›› የሚሉ ናቸው፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸው የተቃውሞ ሠልፈኞ ‹‹የአማራ ክልል አመራሮች አማራን አይወክሉም፣ በአማራዎች ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም፣ አትንኩን ስትነኩን እንበዛለን፣ ተላላኪዎች ልብ ግዙ፣ ሕፃናትን መግደልና ከተማ ማፍረስ ጀግንነት አይደለም፤›› የሚሉና ሌሎች መፈክሮቸን ማሰማታቸው ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹አማራን ማሳደድ ይቁም፣ በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያና መፈናቀል መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል፣ አማራ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ እንጂ ሥጋት ሆኖ አያውቅም፣ አማራ ባንዲራ አንጂ ሰው ሰቅሎ አያውቅም፣ ለአማራ መሳደድ መነሻ የሆነው ሕገ መንግሥት በአስቸኳይ ይሻሻል›› የሚሉ መፈክሮችም ተሰምተዋል፡፡

ሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎና በኦሮሞ ልዩ ዞን በሚገኙ በተለይም በአጣዬ፣ አንጾኪያ፣ ቀወት፣ ኤፍራታ ግድም፣ ሸዋሮቢት፣ ካራቆሬ፣ ጨፋ ሮቢት፣ ማጀቴና ሌሎች ከተሞች በሚገኙ ቀበሌዎች በሦስት ዓመታት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ ተከሰተ በተባለውና ማንነታቸው በግልጽ ባልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች አማካይነት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም ምንም እንኳ እስካሁን ከመንግሥት አካላት በኩል በደረሰው አደጋ የሞቱ ሰዎችና የንብረት ውድመት መጠን በግልጽ ባይነገርም፣ በወቅቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች ወደ ከተማ በገቡበት ወቅት አንዳንዶቹን በጥይት ለመንቀሳቀስና ሮጠው ለማምለጥ ያልቻሉት ደካሞች ደግሞ በቤታቸው ውስጥ ተቃጥለው መሞታቸውን  ከግድያው ያመለጡ የአጣዬ አካባቢ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአጣዬና በሸዋሮቢት ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚኖሩ በርካታ ዜጎች ወደ ደብረ ብርሃንና መሀል ሜዳ እንደሸሹ፣ ከሰኞ ጀምሮ አንዳንዶቹን ወደ ተረጋጋው አካባቢ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ታደሰ ገብረ ፃዲቅ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው በየዓመቱ ግጭቶች እንደሚከሰቱና ለዚህም ኦነግ ሸኔን ተጠያቂ ያደረጉት ዋና አስተዳደሪው፣ አሁን ግን ለተከሰተው ሞትና መፈናቀል በተጨባጭ መሬት ላይ በመውረድ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ከተጠቀሱት ከተሞች ጥቃቱን ፈርተው ወደ ተለያዩ አካቢዎች የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፣ ትክክለኛ ቁጥሩን ለመናገር ግን አልቻሉም፡፡

የተፈናቀሉ ዜጎችንና እየተደረገ ያለውን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ አስመልክቶ ወደ ብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኃላፊዎች በመደወል ለማጣራት የተደረገው ጥረት ‹‹መረጃ አልደረሰንም›› በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአጣዬ አካባቢ ነዋሪ ለሪፖርተር አንደተናገሩት፣ ‹‹ታጣቂ ኃይሎቹ ወደ ከተማው ሲገቡ መኪና ይዘው ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡  ወደ ሕዝቡ ገብተው ንብረት በመዝረፍ በመኪና ጭነው እስከመሄድ ያደረሰ ድፍረት ማን እንደሰጣቸው እንቆቅልሽ ሆነብኛል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ጥፋት አድራሹን ኃይል ምንም እንኳ አንዳንዶች አማራን የማጥፋት ዓላማን ያዘለ ‹‹ኦነግ ሸኔ›› እያሉ ስም ቢሰጡትም፣ አብረውኝ ያደጉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ጭምር ተገድለዋል፣ በዚህም ምክንያት ማን እንደሚገድለን አናውቅም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተለይ በሰሜን ሸዋ ዞን ሥር የሚገኘውና የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና መቀመጫ የሆነው የአጣዬ ከተማ አስተዳደር፣ በታጣቂዎች በተፈጸመበት ጥቃት ሙሉ በሙሉ መውደሙንና ከሞት ያመለጡት ነዋሪዎች ወደ አቅራቢያ ከተሞች ሸሽተው መሄዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ ለተፈጸሙት ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች፣ ብሔራዊ ዕውቅና እንዲሰጥና ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብሏል፡፡

በአማራ ሕዝብ ላይ ባልተቋረጠ ሁኔታ የሚፈጸሙት መንግሥት መራሽ የዘር ፍጅቶች በገለልተኛ ኮሚሽን በጥልቀት ተጣርተው በቀጥታ በጥቃቱ ውስጥ የተሳተፉ፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ መንግሥታዊ መዋቅርን ለጥቃት ማስፈጸሚያነት ያዋሉ፣ ያስተባበሩና የተመሳጠሩ አካላት ማንነት ለሕዝብ በይፋ እንዲገለጽና ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ አጠቃላይ ተጎጂዎችን በተመለከተ ተጣርቶ ዝርዝር ሪፖርት እንዲደረግ ሲል ፓርቲው ጠይቋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በሰሜን ሸዋና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች የተከሰተውን የፀጥታ ችግር አስመልክቶ፣ የክልልና የፌዴራል የፀጥታ ተቋማትን ጨምሮ፣ ሦስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት ማቋቋሙን ሚያዚያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡

በዚህም የፀጥታ ችግር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር የማዋልና መሣሪያ ይዘው በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ የከፈቱ፣ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ የገደቡ ፀረ ሰላም ኃይሎች ላይ ሠራዊቱ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን በመግለጽ፣ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የኅብረሰተሰቡን ሰላም በማወክ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

የተቋቋመው ኮማንድ ፖሰት ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን፣ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትንና የመንግሥት ተቋማትን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤትንና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጠልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ እንደሆነ አስጠንቅቋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *