የህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ግብፅ እያሳየችው ያለው የአፍሪካ ኅብረትን የአደራዳሪነት ሚና አለመቀበሏና ከአፍሪካ ውጭ የመውሰድ ፍላጎት ማሳየቷ፣ ኅብረቱን የመናቅና ያለ ማክበር የቆየ ፍላጎት ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎት ‹‹የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን መፍታት ይቻላል›› የሚለው ዕሳቤ በዋነኝነት 11 የተፋሰሱ አገሮች አፍሪካውያን በመሆናቸውና ወንዙም በአፍሪካ ምድር የሚፈስ በመሆኑ መፍትሔው በአፍሪካ ምድር ነው በሚል እንደሆነ፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ሐሙስ ሚያዚያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበራቸው ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
ከሳምንት በፊት በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር በሆነችው በኮንጎ ኪንሻሳ አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ከግብፅ በኩል የአራት አገሮች አደራዳሪዎች ይግቡ ሲባል፣ በኢትዮጵያ በኩል በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ድርድሩ ይካሄድ የሚል አቋም በመራመዱ ያለ ስምምነት መለያየታቸው ይታወሳል፡፡ ቃል አቀባዩ ይህንን አፍሪካዊ ጉዳይ ወደ ውጭ መውሰድና ከአፍሪካ አኅጉር እንዲወጣ ማድረግ የአፍሪካ ማዕቀፍ እንዳይሳካ የማድረግ ፍላጎት ግብፅ የኅብረቱ ሊቀመንበር ከሆነበችበት ጊዜ ጀምሮ ሲስተዋል የነበረ፣ በወቅቱም ጉዳዩን ከአፍሪካ ኅብረት የድርድር ማዕቀፍ አውጥተው ወደ አሜሪካ መውሰዷ የቆየ ፍላጎት እንዳላት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚያ በመቀጠልም ሊቀመንበርነቱን ደቡብ አፍሪካ በተረከበችበት ማግሥት በኅብረቱ የተጀመረው ድርድር እንዳይሳካ፣ በተለያዩ ሰበቦች ሰባት ጊዜ ያህል ከድርድሩ ትወጣና ትገባ ነበር በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡ ዲና (አምባሳደር) አክለው በተያዘው ዓመትም በኮንጎ ተጀምሮ የነበረው ድርድር ገና ይሳካ አይሳካ ሳይታወቅ፣ ከጅምሩ ኅብረቱ የሚመራውን ሒደት ለማደናቀፍ ባላት የቆየ ፍላጎት እንዳይሳካ እንዳደረገች ወቀሳ አቅርበዋል፡፡
ግብፆች በኮንጎ ኪንሻሳ በነበረው ውይይት ይዘውት የመጡት አጀንዳ አራት አገሮች ይግቡ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ የፈለጓቸው አገሮች ከአፍሪካ ኅብረት ጋር እኩል ሚና ይኑራቸው የሚል እንደነበር፣ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ሲደመርም ሆነ ሲቀነስ ግልጽ በሆነ መንገድ ለአፍሪካ ኅብረት አክብሮትና እምነት የለንም ማለት እንደሆነ ማሳያ ነው ሲሉ ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የተያዘው አቋም በተለይም በመጀመሪያው ሙሌትና በሙሌት አስተዳደሩ ላይ ስምምነት ቅድሚያ ይሁን የሚል እንደሆነ፣ ሌሎች ስምምነቶች በተለይም በውኃ አጠቃቀምና በረዥም ጊዜ ሒደቶች ላይ በመነጋገር ድንበር ተሸጋሪ ወንዞች በሚፈቱበት ሕግ መሠረት፣ በምክንያታዊነትና በፍትሐዊነት መንፈስ ሌላውን ለማስያዝ ጥረት መደረጉን አብራርተዋል፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ማብራሪያ ግድቡን በተመለከተ ከሱዳን በኩል አብዘኛው ጉዳይ እንዳለቀና ምንም አከራካሪ ጉዳይ እንደሌለ በመግለጽ፣ ሱዳኖች የሚፈልጉት የመረጃ ጥያቄ ከዚህ በፊት መረጃን እናንተ ስተሰጡን እኛ እንሰጣችኋለን የሚለው አካሄድ ቀርቶ፣ የግድቡን ደኅንነትም ሆነ አሞላልን በተመለከተ ከፈለጋቹህ እንፈርምላቸኋለን ቢባሉም የራሳቸው መከራከሪያ ነጥብ ሳይኖራቸው የውክልና አጀንዳ እያስፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡
ሱዳኖች ከኢትዮጵያ በላይ ግድቡ ለእነሱ እንደሚጠቅም ከተከዜ ግድብ ግንባታ ወዲህ በድንብ እያወቁ፣ የሱዳን መንግሥት በተለይም ወታራዊ ክንፉ የሌሎችን መልዕክትና ተልዕኮ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው ሲል ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካን ወንዝ የዓረብ ጉዳይ ማድረጉ ዋጋ ቢስ መሆኑን፣ ምንም በማይመለከታቸው የዓባይን ወንዝ አጉል በረሃ ለመውሰድ የሚያደረገው እንቅስቃሴ ደግሞ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ዲና (አምባሳደር) አስረድተዋል፡፡